የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መሳፍንት 6:11-27

መሳፍንት 6:11-27 NASV

የእግዚአብሔር መልአክ ዖፍራ ወደምትባል መንደር መጥቶ፣ በአቢዔዝራዊው በኢዮአስ ዕርሻ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን፣ ምድያማውያን እንዳያዩበት ደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴውን ይወቃ ነበር። የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ፣ “አንተ ኀያል ጦረኛ እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎን መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፣ “ሂድ፤ ባለህ ኀይል እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን?” አለው። ጌዴዎንም፣ “ጌታ ሆይ፤ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተ ሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ። እግዚአብሔርም፣ “በርግጥ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው። ጌዴዎን እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “አሁን በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ በርግጥ የምታነጋግረኝ አንተ ራስህ ለመሆንህ ምልክት ስጠኝ፤ ተመልሼ እስክመጣ፣ መሥዋዕቴንም አምጥቼ በፊትህ እስካቀርብ ድረስ እባክህ አትሂድ።” እግዚአብሔርም፣ “እስክትመለስ እጠብቅሃለሁ” አለው። ጌዴዎን ወደ ቤቱ ሄደ፤ የፍየል ጠቦትም ዐረደ፤ አንድ ኢፍ መስፈሪያ ዱቄት ወስዶ እርሾ ያልገባበት ቂጣ ጋገረ። ሥጋውን በቅርጫት፣ መረቁን በምንቸት ይዞ በመምጣት በባሉጥ ሥር ለተቀመጠው አቀረበለት። የእግዚአብሔር መልአክ፣ “ሥጋውንና ዕርሾ ያልገባበትን ቂጣ ወስደህ፣ በዚያ ዐለት ላይ አኑር፤ መረቁንም በሥጋውና በቂጣው ላይ አፍስስ” አለው፤ ጌዴዎንም እንደ ታዘዘው አደረገ። መልአኩም በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና ቂጣውን ነካ፤ ከዐለቱም እሳት ወጥቶ ሥጋውንና ቂጣውን በላ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ተሰወረ። ጌዴዎን ያየው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና ወዮልኝ” አለ። እግዚአብሔርም፣ “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው። ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም “እግዚአብሔር ሰላም ነው” ብሎ ጠራው፤ ይህ መሠዊያ የአቢዔዝራውያን ይዞታ በሆነው በዖፍራ ዛሬም ቆሞ ይታያል። በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ከአባትህ መንጋ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን ወይፈን ውሰድ፤ አባትህ ለበኣል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ የአሼራን ዐምድ ሰባብረህ ጣል። በዚህ ፍርስራሽ ጕብታ ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የሚገባውን መሠዊያ ሥራ። ሰባብረህ በጣልኸው የአሼራ ምስል ዐምድ ሁለተኛውን ወይፈን ወስደህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርበው።” ጌዴዎን ከአገልጋዮቹ ዐሥር ሰዎች ወስዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተ ሰቡንና የከተማውን ሰው ስለ ፈራ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን ሌሊት ነበር።