መሳፍንት 3:1-11
መሳፍንት 3:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በከነዓን ምድር ጦርነት ያልተለማመዱ እስራኤላውያንን ለመፈተን እግዚአብሔር በምድሪቱ የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው። ይህንንም ማድረጉ ቀድሞ የጦርነት ልምድ ያልነበራቸውን የእስራኤልን ትውልድ የጦርነት ስልት ለማስተማር ብሎ ብቻ ነው። በምድሪቱ ላይ የቀሩትም፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መሪዎች፥ ከነዓናውያን በሙሉ፥ ሲዶናውያንና ከባዓልሔርሞን ተራራ አንሥቶ እስከ ሐማት ድረስ በሊባኖስ ተራራዎች የሚኖሩት ሒዋውያን ነበሩ። እነርሱም እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻቸው የሰጣቸውን ትእዛዞች እስራኤላውያን ያከብሩ ወይም አያከብሩ እንደ ሆነ ለማወቅ ለእስራኤል መፈተኛዎች ነበሩ። በዚህም ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ በከነዓናውያን፥ በሒታውያን፥ በአሞራውያን፥ በፈሪዛውያን፥ በሒዋውያንና በኢያቡሳውያን መካከል ኖሩ። የእነርሱን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ እነርሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻቸው ሰጡ፤ አማልክታቸውንም አመለኩ። የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ አምላካቸውን እግዚአብሔርንም ትተው በዓልና አሼራን አመለኩ፤ ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር ቊጣ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ነደደ፤ ለመስጴጦምያው ንጉሥ ለኩሻን ፊሽዓታይም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለኩሻን ሪሽዓታይም ስምንት ዓመት ተገዙለት፤ ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ የካሌብ ታናሽ ወንድም ልጅ የሆነውን የቄኔዝን ልጅ ዖትኒኤልን አስነሣቸው። የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ ዐደረ፤ በእስራኤልም ላይ መሪ ሆነ፤ ለጦርነት በወጣ ጊዜ እግዚአብሔር የመስጴጦምያውን ንጉሥ ኩሻን ፊሽዓታይምን አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ኩሻን ሪሽዓታይምን ድል አደረገው። በምድሪቱም ላይ ለአርባ ዓመት ያኽል ሰላም ሰፍኖ ከቈየ በኋላ የቄኔዝ ልጅ ዖትኒኤል ሞተ።
መሳፍንት 3:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የከነዓናውያንንም ጦርነት ሁሉ ያላወቁትን እስራኤልን በእነርሱ ይፈትናቸው ዘንድ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ተዋቸው። ይህም ጦርነትን ያስተምሩአቸው ዘንድ ስለ እስራኤል ልጆች ትውልድ ብቻ ነው፤ ነገር ግን ከእነርሱ በፊት የነበሩት እነዚህን አላወቋቸውም ነበር፤ እነርሱም አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ ከነዓናውያንም ሁሉ ፥ ሲዶናውያንም፥ ከበዓልሄርሞን ተራራ ጀምሮ እስከ ኤማት መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ተራራ የሚኖሩትም ኤዌዎናውያን፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ለአባቶቻቸው ያዘዘውን ትእዛዝ መስማታቸው እንዲታወቅ እስራኤል ይፈተኑባቸው ዘንድ እነዚህ ቀሩ። የእስራኤልም ልጆች በከነዓናውያን፥ በኬጤዎናውያን፥ በአሞሬዎናውያን፥ በፌርዜዎናውያን፥ በኤዌዎናውያን፥ በኢያቡሴዎናውያንም መካከል ተቀመጡ። ሴቶች ልጆቻቸውንም አገቡአቸው፤ እነርሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻቸው ሰጡ፤ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ። የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረጉ፤ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተው በዓሊምንና አስታሮትን አመለኩ። ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ፈጽሞ ተቈጣ፤ በወንዞችም መካከል ባለች በሶርያ ንጉሥ በኩሳርሳቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የእስራኤልም ልጆች ለኩሳርሳቴም ስምንት ዓመት ተገዙለት። የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እግዚአብሔርም ለእስራኤል መድኀኒትን አስነሣላቸው። የካሌብ የታናሽ ወንድሙ የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያልም አዳናቸው፤ ለእርሱም ታዘዙለት። የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ አደረ፤ በእስራኤልም ላይ ይፈርድ ነበር፤ ለጦርነትም ወጣ፤ እግዚአብሔርም በወንዞች መካከል ያለች የሶርያ ንጉሥ ኩሳርሳቴምን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እጁም በኩሳርሳቴም ላይ በረታች። ምድሪቱም አርባ ዓመት ዐረፈች፤ የቄኔዝም ልጅ ጎቶንያል ሞተ።
መሳፍንት 3:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ በከነዓን ላይ በተደረጉት ጦርነቶች ተሳትፈው የማያውቁትን እስራኤላውያን ለመፈተን፣ እግዚአብሔር ባሉበት የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው፤ ይህን ማድረጉ ቀደም ሲል በጦር ሜዳ ውለው የማያውቁትን የእስራኤል ልጆች የጦርነት ልምድ እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ ነው፤ እነዚህም አሕዛብ ዐምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች፣ ከነዓናውያን በሙሉ፣ ሲዶናውያንና ከበኣል አርሞንዔም ተራራ እስከ ሐማት መግቢያ ባሉት የሊባኖስ ተራሮች የሚኖሩ ኤዊያውያን ነበሩ። እነዚህ፣ እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ለቀደሙ አባቶቻቸው የሰጠውን ትእዛዞች ማክበር አለማክበራቸውን ለማወቅ ለእስራኤል መፈተኛ እንዲሆኑ እዚያው የቀሩ ነበሩ። ስለዚህ እስራኤላውያን ከከነዓናውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከአሞራውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን ጋራ ዐብረው ኖሩ። እስራኤላውያን የእነዚህን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ የራሳቸውንም ሴቶች ልጆች ለእነርሱ ወንዶች ልጆች ዳሩ፤ አማልክታቸውንም አመለኩ። እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ እግዚአብሔር አምላካቸውንም ረሱ፤ የበኣልንና የአስታሮትን አማልክት አመለኩ። እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ስለዚህ ለመስጴጦምያ ንጉሥ ለኵስርስቴም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እስራኤላውያንም ስምንት ዓመት በባርነት ተገዙለት። እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ ግን የካሌብን ታናሽ ወንድም የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን ታዳጊ አድርጎ አስነሣላቸው። የእግዚአብሔር መንፈስ በርሱ ላይ ወረደ፤ የእስራኤል መስፍን ሆኖ ወደ ጦርነትም ወጣ። እግዚአብሔር የአራም ንጉሥ ኵስርስቴምን አሳልፎ ስለ ሰጠው ድል አደረገ። የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ምድሪቱ ለአርባ ዓመት ሰላም አገኘች።
መሳፍንት 3:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከከነዓናውያንም ጋር መዋጋት ያላወቁትን እስራኤልን በእነርሱ ይፈትናቸው ዘንድ፥ በፊትም ሰልፍን ያልለመዱ የእስራኤል ልጆች ትውልድ መዋጋትን ያውቁና ይማሩ ዘንድ እግዚአብሔር ያስቀራቸው አሕዛብ እነዚህ ናቸው፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ ከነዓናውያንም ሁሉ፥ ሲዶናውያንም፥ ከበኣልአርሞንዔም ተራራ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ተራራ የሚኖሩትም ኤዊያውያን። እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ለአባቶቻቸው ያዘዘውን ትእዛዝ መስማታቸው እንዲታወቅ እስራኤል ይፈተኑባቸው ዘንድ እነዚህ ቀሩ። የእስራኤልም ልጆች በከነዓናውያን በኬጢያውያንም በአሞራውያንም በፌርዛውያንም በኤዊያውያንም በኢያቡሳውያንም መካከል ተቀመጡ። ሴት ልጆቻቸውንም አገቡአቸው፥ እነርሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻቸው ሰጡ፥ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ። የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር አደረጉ፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተው በኣሊምንና አስታሮትን አመለኩ። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በመስጴጦምያ ንጉሥ በኩሰርሰቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ የእስራኤልም ልጆች ለኩሰርሰቴም ስምንት ዓመት ተገዙለት። የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ የካሌብን የታናሽ ውንድሙን የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን አስነሣላቸው። የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ መጣ፥ በእስራኤልም ላይ ይፈርድ ነበር፥ ለሰልፍ ወጣ፥ እግዚአብሔርም የመሰጴጦምያን ንጉሥ ኩሰርሰቴምን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፥ እጁም በኩሰርሰቴም ላይ አሸነፈች። ምድሪቱም አርባ ዓመት ዐረፈች፥ የቄኔዝም ልጅ ጎቶንያል ሞተ።
መሳፍንት 3:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚህ ጊዜ በከነዓን ላይ በተደረጉት ጦርነቶች ተሳትፈው የማያውቁትን እስራኤላውያን ለመፈተን፥ ጌታ ባሉበት የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው። ይህን ማድረጉ ቀደም ሲል በጦር ሜዳ ውለው የማያውቁትን የእስራኤል ልጆች የጦርነት ልምድ እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ ነው። እነዚህም አሕዛብ አምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች፥ ከነዓናውያን በሙሉ፥ ሲዶናውያንና ከበኣል አርሞንዔም ተራራ እስከ ሐማትስ መግቢያ ባሉት የሊባኖስ ተራሮች የሚኖሩ ኤዊያውያን ነበሩ። እነርሱም ጌታ በሙሴ አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻቸው የሰጣቸውን ትእዛዞች እስራኤላውያን ያከብሩ ወይም አያከብሩ እንደሆነ ለማወቅ ለእስራኤል መፈተኛዎች ነበሩ። ስለዚህ እስራኤላውያን ከከነዓናውያን፥ ከኬጢያውያን፥ ከአሞራውያን፥ ከፌርዛውያን፥ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን ጋር አብረው ኖሩ። እስራኤላውያን የእነዚህን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ የራሳቸውንም ሴቶች ልጆች ለእነርሱ ወንዶች ልጆች ዳሩ፤ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ። እስራኤላውያን በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ አምላካቸውን ጌታንም ረሱ፤ በኣልንና አስታሮትን አመለኩ። ጌታ በእስራኤላውያን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ስለዚህ ለመስጴጦምያ ንጉሥ ለኩሽን-ሪሽዓታይም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እስራኤላውያንም ለኩሽን-ሪሽዓታይም ስምንት ዓመት በባርነት ተገዙለት። እስራኤላውያን ወደ ጌታ በጮኹ ጊዜ ግን፥ ጌታ የካሌብን ታናሽ ወንድም የቄኔዝን ልጅ ዖትኒኤልን ታዳጊ አድርጎ አስነሣላቸው። የጌታም መንፈስ በእርሱ ላይ ዐደረ፤ በእስራኤልም ላይ መሪ ሆነ፤ ለጦርነት በወጣ ጊዜ ጌታ የመስጴጦምያውን ንጉሥ ኩሽን ሪሽዓታይምን አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ኩሽን-ሪሽዓታይምን ድል አደረገው። የቄኔዝ ልጅ ዖትኒኤል እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ምድሪቱ ለአርባ ዓመት ሰላም አገኘች።