በዚህ ጊዜ በከነዓን ላይ በተደረጉት ጦርነቶች ተሳትፈው የማያውቁትን እስራኤላውያን ለመፈተን፥ ጌታ ባሉበት የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው። ይህን ማድረጉ ቀደም ሲል በጦር ሜዳ ውለው የማያውቁትን የእስራኤል ልጆች የጦርነት ልምድ እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ ነው። እነዚህም አሕዛብ አምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች፥ ከነዓናውያን በሙሉ፥ ሲዶናውያንና ከበኣል አርሞንዔም ተራራ እስከ ሐማትስ መግቢያ ባሉት የሊባኖስ ተራሮች የሚኖሩ ኤዊያውያን ነበሩ። እነርሱም ጌታ በሙሴ አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻቸው የሰጣቸውን ትእዛዞች እስራኤላውያን ያከብሩ ወይም አያከብሩ እንደሆነ ለማወቅ ለእስራኤል መፈተኛዎች ነበሩ። ስለዚህ እስራኤላውያን ከከነዓናውያን፥ ከኬጢያውያን፥ ከአሞራውያን፥ ከፌርዛውያን፥ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን ጋር አብረው ኖሩ። እስራኤላውያን የእነዚህን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ የራሳቸውንም ሴቶች ልጆች ለእነርሱ ወንዶች ልጆች ዳሩ፤ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ። እስራኤላውያን በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ አምላካቸውን ጌታንም ረሱ፤ በኣልንና አስታሮትን አመለኩ። ጌታ በእስራኤላውያን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ስለዚህ ለመስጴጦምያ ንጉሥ ለኩሽን-ሪሽዓታይም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እስራኤላውያንም ለኩሽን-ሪሽዓታይም ስምንት ዓመት በባርነት ተገዙለት። እስራኤላውያን ወደ ጌታ በጮኹ ጊዜ ግን፥ ጌታ የካሌብን ታናሽ ወንድም የቄኔዝን ልጅ ዖትኒኤልን ታዳጊ አድርጎ አስነሣላቸው። የጌታም መንፈስ በእርሱ ላይ ዐደረ፤ በእስራኤልም ላይ መሪ ሆነ፤ ለጦርነት በወጣ ጊዜ ጌታ የመስጴጦምያውን ንጉሥ ኩሽን ሪሽዓታይምን አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ኩሽን-ሪሽዓታይምን ድል አደረገው። የቄኔዝ ልጅ ዖትኒኤል እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ምድሪቱ ለአርባ ዓመት ሰላም አገኘች።
መጽሐፈ መሳፍንት 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 3:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos