መሳፍንት 11:30-34
መሳፍንት 11:30-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዮፍታሔም፥ “በእውነት የአሞንን ልጆች በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፥ ከአሞን ልጆች ዘንድ በደኅና በተመለስሁ ጊዜ፥ ከቤቴ ደጅ ወጥቶ የሚቀበለኝን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አደርገዋለሁ” ብሎ ለእግዚአብሔር ስእለት ተሳለ። ዮፍታሔም ሊዋጋቸው ወደ አሞን ልጆች ተሻገረ፤ እግዚአብሔርም በእጁ አሳልፎ ሰጣቸው። ከአሮዔርም እስከ ሚኒትና እስከ አቤልክራሚም ድረስ ሃያ ከተሞችን በታላቅ ሰልፍ አጠፋቸው። የአሞንም ልጆች በእስራኤል ልጆች ፊት ተዋረዱ። ዮፍታሔም ወደ መሴፋ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ እነሆም፥ ልጁ ከበሮ ይዛ እየዘፈነች ልትቀበለው ወጣች፤ ለእርሱም የሚወድዳት አንዲት ብቻ ነበረች። ከእርስዋም በቀር ወንድ ወይም ሴት ሌላ ልጅ አልነበረውም።
መሳፍንት 11:30-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዮፍታሔም እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር ተሳለ፤ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፣ አሞናውያንን ድል አድርጌ በምመለስበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊቀበለኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ እኔም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።” ከዚያም ዮፍታሔ አሞናውያንን ለመውጋት ወጣ፤ እግዚአብሔርም እርሱን በእጁ አሳልፎ ሰጠው። ከአሮዔር አንሥቶ እስከ ሚኒት አካባ፣ ከዚያም ዐልፎ እስከ ክራሚም የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ፈጽሞ አጠፋቸው፤ አሞናውያንም ለእስራኤል ተገዙ። ዮፍታሔ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ። እነሆ፤ ልጁ አታሞ እየደለቀች በመዝፈን ልትቀበለው ወጣች፤ እርሷም አንዲት ልጁ ብቻ ነበረች፤ ከእርሷ በቀር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም።
መሳፍንት 11:30-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዮፍታሔም፦ በእውነት የአሞንን ልጆች በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፥ ከአሞን ልጆች ዘንድ በደኅና በተመለስሁ ጊዜ፥ ሊገናኘኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ለእግዚአብሔር ይሆናል፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አቀርበዋለሁ ብሎ ለእግዚአብሔር ስእለት ተሳለ። ዮፍታሔም ሊዋጋቸው ወደ አሞን ልጆች አለፈ፥ እግዚአብሔርም በእጁ አሳልፎ ሰጣቸው። ከአሮዔርም እስከ ሚኒትና እስከ አቤልክራሚም ድረስ ሀያ ከተሞችን በታላቅ አገዳደል መታቸው። የአሞንም ልጆች በእስራኤል ልጆች ፊት ተዋረዱ። ዮፍታሄም ወደ ቤቱ ወደ ምጽጳ መጣ፥ እነሆም ልጁ ከበሮ ይዛ እየዘፈነች ልትገናኘው ወጣች፥ ለእርሱም አንዲት ብቻ ነበረች፥ ከእርስዋም በቀር ወንድ ወይም ሴት ሌላ ልጅ አልነበረውም።
መሳፍንት 11:30-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ለእግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ተሳለ፤ “በዐሞናውያን ላይ ድልን ብታቀዳጀኝ ድል አድርጌ ከዘመቻ ወደ ቤቴ በደኅና ስመለስ ከቤት ወጥቶ ሊቀበለኝ የሚመጣው ለአንተ ይሆናል፤ እርሱንም ለአንተ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።” ከዚህም በኋላ ዮፍታሔ ዐሞናውያንን ለመውጋት ወንዙን ተሻግሮ ሄደ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ድልን አጐናጸፈው። ከዓሮዔር ጀምሮ በሚኒት ዙሪያ እስካለው ስፍራ በአጠቃላይ ኻያ ከተሞችን፥ እንዲሁም እስከ አቤል ከራሚም ድረስ ያሉትን ሁሉ ደመሰሳቸው፤ በዚህም ዐይነት ዐሞናውያን በእስራኤላውያን ፊት ተዋረዱ። ዮፍታሔ በምጽጳ ወዳለው ቤቱ በተመለሰ ጊዜ ሴት ልጁ አታሞ ይዛ እየጨፈረች ልትቀበለው ወጣች፤ ያለ እርስዋም ሌላ ወንድ ወይም ሴት ልጅ አልነበረውም።
መሳፍንት 11:30-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዮፍታሔም እንዲህ ሲል ለጌታ ተሳለ፤ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፥ አሞናውያንን ድል አድርጌ በምመለስበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊቀበለኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ሰው ለጌታ ይሆናል፤ እኔም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።” ከዚያም ዮፍታሔ አሞናውያንን ለመውጋት ወጣ፤ ጌታ እነርሱን በእጁ አሳልፎ ሰጠው። ከአሮዔር አንሥቶ እስከ ሚኒት አካባቢ ከዚያም አልፎ እስከ ክራሚም የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ፈጽሞ አጠፋቸው፤ አሞናውያንም ለእስራኤል ተገዙ። ዮፍታሔ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ፤ እነሆ፤ ልጁ አታሞ እየደለቀች በመዝፈን ልትቀበለው ወጣች፤ እርሷም አንዲት ልጁ ብቻ ነበረች፤ ከእርሷ በቀር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም።