የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መሳፍንት 11

11
1ገለዓዳዊው ዮፍታሔ ኀያል ጦረኛ ነበረ፤ አባቱ ገለዓድ ነበር፤ እናቱም ጋለሞታ ነበረች። 2እንደዚሁም የገለዓድ ሚስት ለገለዓድ ወንዶች ልጆች ወለደችለት፤ እነርሱም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን፣ “ከሌላ ሴት ስለ ተወለድህ ከቤተ ሰባችን ምንም ዐይነት ውርስ አይገባህም” በማለት አሳደዱት። 3ስለዚህም ዮፍታሔ ከወንድሞቹ ሸሽቶ መኖሪያውን ጦብ በተባለች ምድር አደረገ፤ እዚያም ወሮበሎች ተሰባስበው ተከተሉት።
4ከጥቂት ጊዜ በኋላም አሞናውያን በእስራኤል ላይ ጦርነት ባደረጉ ጊዜ፣ 5የገለዓድ አለቆች ዮፍታሔን ለማምጣት ወደ ጦብ ምድር ሄዱ። 6እነርሱም፣ “ከአሞናውያን ጋር መዋጋት እንችል ዘንድ መጥተህ ምራን” አሉት።
7ዮፍታሔም፣ “ምነው ጠልታችሁኝ ከአባቴ ቤት አሳድዳችሁኝ አልነበረምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ነው የምትፈልጉኝ?” አላቸው።
8የገለዓድ አለቆችም፣ “እንግዲህ አሁን ወደ አንተ መጥተናል፤ አሞናውያንን እንድንወጋ በል ተነሥና አብረን እንሂድ፤ በገለዓድ በምንኖረው በሁላችንም ላይ አለቃ ትሆናለህ” አሉት።
9ዮፍታሔም፣ “አሞናውያንን ለመውጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝና እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው በርግጥ አለቃችሁ እሆናለሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
10የገለዓድ አለቆችም፣ “እግዚአብሔር ምስክራችን ነው፤ ያልኸውንም በርግጥ እናደርጋለን” አሉት። 11ስለዚህ ዮፍታሔ ከገለዓድ አለቆች ጋር ሄደ፤ ሕዝቡም በላያቸው ላይ አለቃና አዛዥ አደረጉት፤ ዮፍታሔም የተናገረውን ቃል ሁሉ ምጽጳ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ደገመው።
12ከዚያም ዮፍታሔ ወደ አሞናውያን ንጉሥ፣ “ከእኔ ጋር ምን ጠብ ቢኖርህ ነው መጥተህ አገሬን የወጋኸው?” በማለት መልእክተኞች ላከ።
13የአሞናውያንም ንጉሥ ለዮፍታሔ መልእክተኞች፣ “ይህን ያደረግሁት እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ በአርኖንና በያቦቅ ወንዞች መካከል ያለውንና እስከ ዮርዳኖስ ያለውን አገሬን ስለ ወሰዱብኝ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ” አላቸው።
14ዮፍታሔም መልእክተኞቹን እንደ ገና ወደ አሞናውያን ንጉሥ ላካቸው፤ 15እንዲህም አላቸው፤ “ዮፍታሔ እንዲህ ይላል፤ እስራኤል የሞዓብንም ሆነ የአሞናውያንን ምድር አልወሰደም። 16እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ በምድረ በዳ አድርጎ ወደ ቀይ ባሕር#11፥16 ዕብራይስጡ ያም ሶውፍ ይላል፤ ይህም የዳንኤል ባሕር ማለት ነው። ከዚያም ወደ ቃዴስ ሄደ። 17እስራኤልም ወደ ኤዶም ንጉሥ፣ ‘በአገርህ እንዳልፍ እባክህ ፍቀድልኝ’ በማለት መልእክተኞችን ላከበት፤ የኤዶም ንጉሥ ግን አልሰማውም። ለሞዓብ ንጉሥም እንደዚሁ ላከበት፤ እርሱም አልተቀበለውም፤ ስለዚህ እስራኤል በቃዴስ ተቀመጠ።
18“ቀጥሎም የኤዶምንና የሞዓብን ምድር በመዞር፣ በምድረ በዳው ተጕዞ ከሞዓብ በስተ ምሥራቅ በኩል በማለፍ ከአርኖን ማዶ ሰፈረ፤ የሞዓብም ድንበር አርኖን ስለ ነበር ወደ ሞዓብ ክልል አልገባም።
19“ከዚያም እስራኤል በሐሴቦን ወዳለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞች ልኮ፣ ‘ወደ ገዛ ስፍራችን ለመሄድ በአገርህ እንዳልፍ ፍቀድልኝ’ አለው። 20ሴዎን ግን በግዛቱ እንዲያልፍ ለመፍቀድ እስራኤልን አላመነውም#11፥20 ወይም ከእስራኤል ጋር አልተስማማም፤ ሰራዊቱንም ሰብስቦ በያሃድ ከሰፈረ በኋላ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ።
21“ከዚያም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሴዎንንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ አሸነፏቸውም። እስራኤልም በዚያ አገር የሚኖሩትን የአሞራውያንን ምድር በሙሉ ወረሰ፤ 22ከአርኖን እስከ ያቦቅ፣ ከምድረ በዳው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ወረሱ።
23“እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አሞራውያንን ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሳድዶ ካስወጣቸው፣ አንተ ለመውሰድ ምን መብት አለህ? 24አምላክህ ካሞሽ የሰጠህን ይዞ ማቈየቱ ያንተ ፈንታ ነው፤ እኛም እንደዚሁ አምላካችን እግዚአብሔር የሰጠንን ሁሉ ርስት አድርገን እንወርሳለን። 25አንተ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ ትበልጣለህን? ለመሆኑ እርሱ ከእስራኤል ጋር ተጣልቷልን? ወይስ ተዋግቷልን? 26እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮቿ፣ በአሮዔርና በመንደሮቿ፣ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረበት በዚያን ጊዜ ስለ ምን አልወሰዳችኋቸውም ነበር? 27እኔ አልበደልሁህም፤ አንተ ግን በእኔ ላይ ዘምተህ በድለኸኛል፤ እንግዲህማ ፈራጁ#11፥27 ወይም መሪው እግዚአብሔር በእስራኤላውያንና በአሞናውያን መካከል ዛሬ ይፍረድ።”
28የአሞን ንጉሥ ግን ዮፍታሔ የላከውን መልእክት ከምንም አልቈጠረውም።
29ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤ ተነሥቶም ገለዓድንና ምናሴን አቋርጦ ሄደ። ገለዓድ ባለችው በምጽጳ በኩል አድርጎም በአሞናውያን ላይ ዘመተባቸው። 30ዮፍታሔም እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር ተሳለ፤ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፣ 31አሞናውያንን ድል አድርጌ በምመለስበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊቀበለኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ እኔም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።”
32ከዚያም ዮፍታሔ አሞናውያንን ለመውጋት ወጣ፤ እግዚአብሔርም እርሱን በእጁ አሳልፎ ሰጠው። 33ከአሮዔር አንሥቶ እስከ ሚኒት አካባ፣ ከዚያም ዐልፎ እስከ ክራሚም የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ፈጽሞ አጠፋቸው፤ አሞናውያንም ለእስራኤል ተገዙ።
34ዮፍታሔ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ። እነሆ፤ ልጁ አታሞ እየደለቀች በመዝፈን ልትቀበለው ወጣች፤ እርሷም አንዲት ልጁ ብቻ ነበረች፤ ከእርሷ በቀር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም። 35ባያትም ጊዜ ልብሱን በመቅደድ፣ “ወይኔ ልጄ ጕድ አደረግሽኝ! ጭንቅም ላይ ጣልሽኝ፤ ማስቀረት የማልችለውን ስእለት ለእግዚአብሔር ተስያለሁና” ብሎ በሐዘን ጮኸ።
36እርሷም እንዲህ አለች፤ “አባቴ ሆይ፤ መቼም አንዴ ለእግዚአብሔር ቃል ገብተሃል፤ ጠላቶችህን አሞናውያንን አሁን እግዚአብሔር ተበቅሎልሃልና ቃል የገባኸውን ፈጽምብኝ። 37ነገር ግን አንድ ነገር ብቻ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ፤ ከእንግዲህ ባል ስለማላገባ ከባልንጀሮቼ ጋር ወደ ተራሮች ወጥቼ እየዞርሁ ሁለት ወር እንዳለቅስ አሰናብተኝ።”
38እርሱም፣ “በይ ሂጂ” ብሎ ለሁለት ወር አሰናበታት፤ እርሷም ከእንግዲህ ባል ስለማታገባ ከልጃገረድ ጓደኞቿ ጋር ወደ ተራሮች ሄደው አለቀሱ። 39ከሁለት ወር በኋላ ወደ አባቷ ተመለሰች፤ እርሱም የተሳለውን አደረገ፤ ድንግልም ነበረች።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ በእስራኤል ልማድ ሆኖ፣ 40የእስራኤል ወጣት ሴቶች የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በማሰብ በየዓመቱ እየወጡ የአራት ቀን ሐዘን ያደርጉላታል።

Currently Selected:

መሳፍንት 11: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ