ኢሳይያስ 44:9-20
ኢሳይያስ 44:9-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጣዖታትን የሚቀርጹ ያንጊዜ አይኖሩም፤ የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩም ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፤ የማይረባቸውን የራሳቸውን ፍላጎት የሚያደርጉ ሁሉ ያፍራሉ። ጣዖታትን የሚሠሩ፥ የማይጠቅማቸውን ምስል የሚቀርጹና በእነርሱም የተሠሩ ሁሉ ይደርቃሉ። ከሰዎች መካከል ደንቆሮዎች ሁሉ ይሰብሰቡ፤ በአንድነትም ይቁሙ፤ በአንድነትም ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉም። ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይስላል፤ ጣዖቱን በመጥረቢያ ይቀርጸዋል፤ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሰጠዋል፤ በክንዱም ኀይል ይሠራዋል፤ እርሱም ይራባል፤ ይደክምማል፤ ውኃም አይጠጣም። ጠራቢውም እንጨት ቈርጦ በልኩ ያቆመዋል፤ በማጣበቂያም ያያይዘዋል፤ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ያስመስለዋል፤ በቤትም ውስጥ ያቆመዋል። እግዚአብሔር ያበቀለውን፥ በዝናምም ያሳደገውን ዛፍ ከዱር ይቈርጣል። ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፤ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም የተረፈውን ጣዖታትን አበጅቶ ይሰግድላቸዋል። ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፤ በዚያም በግማሹ ሥጋ ይጠብሳል፤ ጥብሱንም ይበላና ይጠግባል፤ ይሞቃልና፥ “እሰይ ሞቅሁ፥ እሳቱን አይቻለሁ” ይላል። የቀረውንም እንጨት ጣዖት አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግዳል፤ ወደ እርሱም እየጸለየ፥ “አምላኬ ነህና አድነኝ” ይላል። አያውቁም፤ አያስቡም፤ እንዳያዩ ዐይኖቻቸው፥ እንዳያስተውሉም ልቦቻቸው ተጋርደዋል። ማንም በልቡ አያስብም፥ “ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፤ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፤ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፤ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን? እንዲልም ዕውቀትና ማስተዋል የለውም። እንግዲህ ልባቸው አመድ እንደ ሆነና እንደ በደሉ፥ ከእነርሱም ነፍሱን ለማዳን የሚችል ማንም እንደሌለ ዕወቁ፤ በቀኝ እጄ ሐሰት አለ” የሚልም እንደሌለ ተመልከቱ።
ኢሳይያስ 44:9-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጣዖት የሚሠሩ ሁሉ ከንቱዎች፣ የሚሠሩባቸውም ነገሮች ዋጋ ቢስ ናቸው፤ የሚናገሩላቸው ዕውሮች ናቸው፤ ዕውቀት የላቸውም ያፍራሉም። ለምንም የማይጠቅመውን አምላክ የሚቀርጽ፣ ጣዖትን የሚያበጅስ ማነው? ጣዖት የሚሠራ ሰው እንጂ ሌላ አይደለም፤ እርሱና መሰሎቹም ያፍራሉ፤ ሁሉም ተሰብስበው በአንድ ላይ ይቁሙ፤ ይደነግጣሉ፤ ይዋረዳሉም። ብረት ቀጥቃጭ መሥሪያን ይይዛል፤ በከሰል ፍም ላይ ይሠራዋል፤ ጣዖትን በመዶሻ ቅርጽ ይሰጠዋል፤ በክንዱም ኀይል ያበጀዋል። ከዚያም ይራባል፤ ጕልበት ያጣል፤ ውሃ ይጠማል፤ ይደክማል። ጠራቢ በገመድ ይለካል፤ በጠመኔ ንድፍ ያወጣል፤ በመሮ ይቀርጸዋል፤ በጸርከል ምልክት ያደርግበታል። በሰው አምሳል ይቀርጸዋል፤ የሰውንም ውበት ያለብሰዋል፤ በማምለኪያም ስፍራ ያስቀምጠዋል። ዝግባ ይቈርጣል፤ ሾላ ወይም ዋንዛ ይመርጣል፤ በደን ውስጥ ካሉት ዛፎች ጋር እንዲያድግ ይተወዋል፤ ወይም ጥድን ይተክላል፤ ያንንም ዝናም ያሳድገዋል። ሰው ለማገዶ ይጠቀምበታል፤ ከዚያም ጥቂት ወስዶ በማንደድ ይሞቀዋል፤ እንጀራም ይጋግርበታል። ከዚሁ ጠርቦ አምላክ ያበጃል፤ ያመልከዋል፤ ጣዖትን ይሠራል፤ ወድቆም ይሰግድለታል። ግማሹን ዕንጨት ያነድደዋል፤ በላዩ ምግቡን ያበስልበታል፤ ሥጋ ጠብሶበት እስኪጠግብ ይበላል፤ እሳቱን እየሞቀ እንዲህ ይላል፤ “ዕሠይ ሞቀኝ፤ እሳቱም ይታየኛል።” በቀረው ዕንጨት የጣዖት አምላኩን ይሠራበታል፤ ወድቆ ይሰግድለታል፤ ያመልከዋል፤ ወደ እርሱም እየጸለየ፣ “አንተ አምላኬ ነህ፤ አድነኝ” ይላል። ምንም አያውቁም፤ አያስተውሉም፤ እንዳያዩ ዐይናቸው ተሸፍኗል፤ እንዳያስተውሉ ልባቸው ተዘግቷል። ማንም ቆም ብሎ አላሰበም፤ ዕውቀት ወይም ማስተዋል ስለሌለው እንዲህ ማለት አልቻለም፤ “ግማሹን በእሳት አቃጥዬዋለሁ፤ በፍሙ እንጀራ ጋግሬበታለሁ፤ ሥጋ ጠብሼበት በልቻለሁ፤ ታዲያ፣ በቀረው እንዴት ጸያፍ ነገር እሠራለሁ? ለግንድስ መስገድ ይገባኛልን?” ዐመድ ይቅማል፤ ተታላይ ልብ አስቶታል፤ ራሱን ለማዳን አይችልም፤ “ይህ በቀኝ እጄ ያለው ነገር ሐሰት አይደለምን?” ለማለት አልቻለም።
ኢሳይያስ 44:9-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ከንቱዎች ናቸው፥ የወደዱትም ነገር አይረባቸውም፥ ምስክሮቻቸውም አያዩምና አያውቁም፥ ስለዚህ ያፍራሉ። አምላክን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባ ምስልን የቀረጸ ማን ነው? እነሆ፥ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፥ ሠራተኞቹም ከሰዎች ወገን ናቸው፥ ሁላቸው ተሰብስበው ይቁሙ፥ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ። ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፥ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፥ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሠጠዋል፥ በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፥ እርሱም ይራባል ይደክምማል፥ ውኃም አይጠጣም ይታክትማል። ጠራቢውም ገመድ ይዘረጋል በበረቅም ያመለክተዋል በመቅረጫም ይቀርጸዋል በመለኪያም ይለከዋል፥ በቤትም ውስጥ ይቀመጥ ዘንድ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ያስመስለዋል። የዝግባን ዛፎች ይቈርጣል፥ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል፥ ከዱር ዛፎችም መካከል ይጠነክር ዘንድ ይተወዋል፥ የጥድንም ዛፍ ይተክላል ዝናብም ያበቅለዋል። ለሰውም ማገዶ ይሆናል፥ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፥ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፥ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፥ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል። ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፥ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል፥ ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል፥ ይሞቃልና፦ እሰይ ሞቅሁ፥ እሳቱን አይቻለሁ ይላል። የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፥ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግድበታል፥ ወደ እርሱም እየጸለየ፦ አምላኬ ነህና አድነኝ ይላል። አያውቁም፥ አያስቡም፥ እንዳያዩ ዓይኖቻቸውን፥ እንዳያስተውሉም ልቦቻቸውን ጨፍነዋል። በልቡም ማንም አያስብም፦ ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፥ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፥ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፥ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን? እንዲልም እውቀትና ማስተዋል የለውም። አመድ ይበላል፥ የተታለለ ልብ አስቶታል፥ ነፍሱን ለማዳን አይችልም፥ ወይም፦ በቀኝ እጄ ሐሰት አለ አይልም።
ኢሳይያስ 44:9-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጣዖቶችን የሚሠሩ ሁሉ ከንቱ ናቸው፤ ከፍተኛ ግምት የሚሰጡአቸው ጣዖቶቻቸውም ዋጋቢሶች ናቸው፤ በዚህም ኀፍረት ይደርስባቸዋል። አንድ ሰው ምንም የማይጠቅም ጣዖትን ወይም ምስልን ይሠራል? እነርሱንም የሚያመልኩ ሁሉ ያፍራሉ፤ ጣዖትን የሚሠሩ ሰዎች እንጂ ሌላ አይደለም፤ ሁሉም ይሰብሰቡና በፊቴ ይቁሙ፤ ሁሉም በፍርሃት ይዋጣሉ፤ ያፍራሉም። አንጥረኛ ጣዖትን ለመሥራት ብረትን ወስዶ በእሳት ያቀልጠዋል። ለብረቱም ቅርጽ ለመስጠት በብርቱ ክንዱ በመዶሻ ይቀጠቅጠዋል፤ ይህንንም በሚሠራበት ጊዜ ይራባል፥ ይጠማል፥ ይደክማልም። አናጢ በእንጨቱ ላይ መስመርን ያሰምራል፤ ንድፍም ይነድፋል፤ በመላጊያ ያለሰልሰዋል፤ በማስተካከያ መሣሪያም ትክክልነቱን ያረጋግጣል፤ ውበት ያለው የሰው ቅርጽ እንዲኖረው ያደርጋል። ከዚያም በጣዖት ቤት ያኖረዋል። ይህን ለማድረግ የሊባኖስ ዛፍ ወይም ዝግባ ዛፍ ወይም ዋርካ ከጫካው ይመርጣል፤ አለበለዚያም በአናጢው ተተክሎ የዝናብ ውሃ እየጠጣ የሚያድገውን የኮምበል ዛፍ ይተክላል። ሰው ከአንድ ዛፍ ግማሹን ለማገዶ፥ ግማሹንም ጣዖት ለመሥራት ይጠቀምበታል፤ ግማሹን እሳት አንድዶ ለመሞቅና እንጀራ ለመጋገር ይጠቀምበታል፤ በሌላው ጒማጅ ጣዖት ሠርቶ በፊቱ እየሰገደ ያመልከዋል። ግማሹን እሳት አንድዶ ምግቡን ያዘጋጅበታል፤ ሥጋም ጠብሶ እስከሚጠግብ ይመገባል፤ ከሞቀውም በኋላ “ግሩም እሳት ነው! እንዴት ይሞቃል!” ይላል። የቀረውንም ጒማጅ ጣዖት አድርጎ ይሠራና በፊቱ ተደፍቶ በመስገድ ያመልከዋል፤ “አንተ አምላኬ ነህ፤ አድነኝ!” እያለ ወደ እርሱ ይጸልያል። እንደዚህ ያሉት ሰዎች ዐይኖቻቸው ስለ ተሸፈኑ ማየት አይችሉም። “የዚህን እንጨት ግማሹን አነደድኩት፤ በፍሙም ዳቦ ጋገርኩበት፤ ሥጋም ጠብሼበት በላሁ፤ አሁን እንግዲህ ቀሪውን ቊራጭ እንጨት ለጣዖት ላውለውን? በአንድ ቊራጭ እንጨት ፊት ወድቄ ልስገድን?” ብሎ የሚያስብ ዕውቀት ወይም ማስተዋል ያለው አንድም ሰው የለም። ተቃጥሎ ዐመድ የሚሆነውን እንጨት እስከ ማምለክ ድረስ ሰው እንዴት ሞኝ ይሆናል? የሞኝነት አስተሳሰቡ አሳስቶታል፤ ራሱን ማዳን አይችልም፤ ወይም “ይህ በቀኝ እጄ ያለው ነገር ጣዖት እንጂ አምላክ አይደለም።” ብሎ መናገር አይችልም።
ኢሳይያስ 44:9-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ከንቱዎች ናቸው፤ የወደዱትም ነገር አይጠቅማቸውም፤ ምስክሮቻቸውም አያስተውሉም ደግሞ አያውቁም፥ ስለዚህ ያፍራሉ። ጣዖትን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባን ምስልን የቀረጸ ማን ነው? እነሆ፥ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፥ ባለሙያዎቹም ከሰው ወገን ናቸው፤ ሁሉም ተሰብስበው ይቁሙ፤ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ። ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፥ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፥ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሠጠዋል፤ በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፥ እርሱም ይርበዋል ይደክማልም፤ ውኃም ለመጠጣት ይታክታል። ጠራቢው ገመድ ይዘረጋል፥ በጠመኔም ምልክት ያኖራል፥ በመሮም ይቀርጸዋል፥ በመለኪያም ይለከዋል፤ በቤትም ውስጥ እንዲቀመጥ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ይቀርጸዋል። የዝግባን ዛፎች ይቈርጣል፤ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል፥ ከዱር ዛፎችም መካከል እንዲጠነክር ይተወዋል፤ የጥድንም ዛፍ ይተክላል፥ ዝናብም ያበቅለዋል። ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፥ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፤ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል። ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፥ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል፤ ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል፤ ይሞቃልና፦ “እሰይ ሞቅሁ፥ ሙቀት ተሰማኝ” ይላል። የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግድበታል፤ ወደ እርሱም እየጸለየ፦ አምላኬ ነህና አድነኝ ይላል። አያውቁም፥ አያስቡም፤ እንዳያዩ ዐይኖቻቸውን፥ እንዳያስተውሉም ልቦቻቸውን ጨፍነዋል። በልቡም ማንም አያስብም፦ “ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፥ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፥ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፤ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን?” ለማለት እንኳን እውቀትና ማስተዋል የለውም። አመድ ይበላል፥ የተታለለ ልብ አስቶታል፥ ነፍሱን ለማዳን አይችልም፥ ወይም፦ “በቀኝ እጄ ሐሰት አለ?” ብሎም አይጠይቅም።