የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 44:9-20

ትንቢተ ኢሳይያስ 44:9-20 አማ54

የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ከንቱዎች ናቸው፥ የወደዱትም ነገር አይረባቸውም፥ ምስክሮቻቸውም አያዩምና አያውቁም፥ ስለዚህ ያፍራሉ። አምላክን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባ ምስልን የቀረጸ ማን ነው? እነሆ፥ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፥ ሠራተኞቹም ከሰዎች ወገን ናቸው፥ ሁላቸው ተሰብስበው ይቁሙ፥ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ። ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፥ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፥ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሠጠዋል፥ በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፥ እርሱም ይራባል ይደክምማል፥ ውኃም አይጠጣም ይታክትማል። ጠራቢውም ገመድ ይዘረጋል በበረቅም ያመለክተዋል በመቅረጫም ይቀርጸዋል በመለኪያም ይለከዋል፥ በቤትም ውስጥ ይቀመጥ ዘንድ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ያስመስለዋል። የዝግባን ዛፎች ይቈርጣል፥ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል፥ ከዱር ዛፎችም መካከል ይጠነክር ዘንድ ይተወዋል፥ የጥድንም ዛፍ ይተክላል ዝናብም ያበቅለዋል። ለሰውም ማገዶ ይሆናል፥ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፥ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፥ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፥ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል። ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፥ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል፥ ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል፥ ይሞቃልና፦ እሰይ ሞቅሁ፥ እሳቱን አይቻለሁ ይላል። የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፥ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግድበታል፥ ወደ እርሱም እየጸለየ፦ አምላኬ ነህና አድነኝ ይላል። አያውቁም፥ አያስቡም፥ እንዳያዩ ዓይኖቻቸውን፥ እንዳያስተውሉም ልቦቻቸውን ጨፍነዋል። በልቡም ማንም አያስብም፦ ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፥ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፥ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፥ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን? እንዲልም እውቀትና ማስተዋል የለውም። አመድ ይበላል፥ የተታለለ ልብ አስቶታል፥ ነፍሱን ለማዳን አይችልም፥ ወይም፦ በቀኝ እጄ ሐሰት አለ አይልም።