ትንቢተ ኢሳይያስ 44
44
ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ
1አሁንም ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማ። 2የፈጠረህ ከማኅፀንም የሠራህ የሚረዳህም እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፥ “ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ወዳጄ እስራኤል ሆይ፥ አትፍራ። 3በደረቅ መሬት ላይ ለሚሄድና ለተጠማ ውኃን እሰጣለሁ፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ፥ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አኖራለሁ፤ 4በውኃ መካከል እንዳለ ቄጠማ በፈሳሾችም አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች ይበቅላሉ። 5ይህ፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ይላል፤ ያም በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ ይህም፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእጁ ይጽፋል፤ በእስራኤልም ስም ይጠራል።”
6የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እንዲህ ይላል፥ “እኔ ፊተኛ ነኝ፤ እኔም ኋለኛ ነኝ፤ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም። 7እንደ እኔ ያለ አዳኝ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ፤ ይናገርም፤ ሰውን ከፈጠርሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘለዓለሙ የሚሆነውን ያዘጋጅልኝ፤ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይናገር። 8ራሳችሁን አትደብቁ፤ ከጥንት ጀምሮ አልሰማችሁምን? አልነገርኋችሁምን? ከእኔ ሌላ አምላክ እንደ ሌለ ምስክሮች ናችሁ።”
ስለ ጣዖት አምልኮ ከንቱነት
9ጣዖታትን የሚቀርጹ ያንጊዜ አይኖሩም፤ የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩም ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፤ የማይረባቸውን የራሳቸውን ፍላጎት የሚያደርጉ ሁሉ ያፍራሉ። 10ጣዖታትን የሚሠሩ፥ የማይጠቅማቸውን ምስል የሚቀርጹና በእነርሱም የተሠሩ ሁሉ ይደርቃሉ። 11ከሰዎች መካከል ደንቆሮዎች ሁሉ ይሰብሰቡ፤ በአንድነትም ይቁሙ፤ በአንድነትም ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉም።
12ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይስላል፤ ጣዖቱን በመጥረቢያ ይቀርጸዋል፤ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሰጠዋል፤ በክንዱም ኀይል ይሠራዋል፤ እርሱም ይራባል፤ ይደክምማል፤ ውኃም አይጠጣም። 13ጠራቢውም እንጨት ቈርጦ በልኩ ያቆመዋል፤ በማጣበቂያም ያያይዘዋል፤ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ያስመስለዋል፤ በቤትም ውስጥ ያቆመዋል። 14እግዚአብሔር ያበቀለውን፥ በዝናምም ያሳደገውን ዛፍ ከዱር ይቈርጣል። 15ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፤ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም የተረፈውን ጣዖታትን አበጅቶ ይሰግድላቸዋል።#ዕብራይስጥ ይጨምራል። 16ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፤ በዚያም በግማሹ ሥጋ ይጠብሳል፤ ጥብሱንም ይበላና ይጠግባል፤ ይሞቃልና፥ “እሰይ ሞቅሁ፥ እሳቱን አይቻለሁ” ይላል። 17የቀረውንም እንጨት ጣዖት አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግዳል፤ ወደ እርሱም እየጸለየ፥ “አምላኬ ነህና አድነኝ” ይላል።
18አያውቁም፤ አያስቡም፤ እንዳያዩ ዐይኖቻቸው፥ እንዳያስተውሉም ልቦቻቸው ተጋርደዋል። 19ማንም በልቡ አያስብም፥ “ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፤ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፤ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፤ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን? እንዲልም ዕውቀትና ማስተዋል የለውም። 20እንግዲህ ልባቸው አመድ እንደ ሆነና እንደ በደሉ፥ ከእነርሱም ነፍሱን ለማዳን የሚችል ማንም እንደሌለ ዕወቁ፤ በቀኝ እጄ ሐሰት አለ” የሚልም እንደሌለ ተመልከቱ።
የእግዚአብሔር አዳኝነት
21ያዕቆብ ሆይ፥ አንተም እስራኤል፥ አገልጋዬ ነህና ይህን ዐስብ፤ እኔ ፈጥሬሃለሁ፤ አንተም ባሪያዬ ነህ፤ እስራኤል ሆይ፥ አትርሳኝ። 22መተላለፍህን እንደ ደመና፥ ኀጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፤ ተቤዥችሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ። 23እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ምሕረትን አድርጎአልና ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና የምድር መሠረቶች መለከትን ይንፉ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በውስጣቸው ያሉ ዛፎች ሁሉ፥ እልል ይበሉ።
24ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሁሉን ለብቻዬ የፈጠርሁ፥ ሰማያትን የዘረጋሁ፥ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ 25በሟርት ሙት እናስነሣለን የሚሉትን፥ ከልባቸውም አንቅተው ሐሰት የሚናገሩትን ሰዎች ምልክት#ግእዝ “ምክር” ይላል። የሚለውጥ ማን ነው? ጥበበኞቹንም ወደ ኋላ ይመልሳል፤ ምክራቸውንም ስንፍና ያደርጋል። 26የባርያውን ቃል ያጸናል፤ የመልእክተኞቹንም ምክር ይፈጽማል። ኢየሩሳሌምን፦ የሰው መኖሪያ ትሆኛለሽ፤ የይሁዳንም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የኤዶምያስንም” ይላል። ከተሞች ትታነጻላችሁ፤ ምድረ በዳዎችዋም ይለመልማሉ፤” ይላል፤ 27ቀላይዋንም፥ “ደረቅ ሁኚ ፈሳሾችሽም ይድረቁ” ይላል፤ 28ቂሮስንም፥ “ብልህ ሁን፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን፦ ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስንም እመሠርታለሁ ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል” ይላል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 44: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ