ኢሳይያስ 32:1-20
ኢሳይያስ 32:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በጽድቅ የሚያስተዳድር ንጉሥ የሚነሣበት ጊዜ ይመጣል፤ ሹማምንቱም በትክክል ይፈርዳሉ። ከእነርሱ እያንዳንዱ ከነፋስ እንደሚከለሉበትና ከወጀብ እንደሚሰወሩበት መጠጊያ ይሆናል፤ በበረሓ እንደሚፈስሱ ጅረቶችና በምድረ በዳ እንደሚገኝ እንደ ትልቅ አለት መጠለያ ይሆናሉ። ከዚህ በኋላ የሚያዩ ሰዎች ዐይኖች አይጨፈኑም፤ ለመስማት የሚችሉ ሰዎች ጆሮዎችም ያዳምጣሉ። ችኲሎች የነበሩ በትዕግሥት የሚያመዛዝኑ ይሆናሉ፤ ተብታባ አንደበት የነበራቸው አንደበተ ርቱዖች ይሆናሉ፤ ንግግራቸውም ግልጥ ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲህ ሞኞች ጨዋዎች አይባሉም፤ ባለጌዎችም ክብር አይሰጣቸውም። ሞኞች የሞኝነትን ንግግር ይናገራሉ፤ አእምሮአቸውም በደልን ያሤራል፤ ስለ እግዚአብሔር ስሕተተኛ ንግግርን በማሠራጨት ክሕደትን ያስፋፋል። የተራቡትን አያጠግቡም። የባለጌዎች ሥራ ክፉ ነው፤ ምንም ያኽል የድኾች አቤቱታ ትክክል ቢሆን ውሸት በመናገር ድኾችን ለማጥፋት ክፉ ዕቅድ ያቅዳሉ። ጨዋ ሰው ግን የጨዋነት ሥራውን በታማኝነት ያቅዳል፤ በጨዋነቱም ጸንቶ ይኖራል። እናንተ በምቾት የምትኖሩ ሴቶች ተነሥታችሁ ድምፄን ስሙ፤ እናንተ በኑሮአችሁ የምትተማመኑ ሴቶች ንግግሬን አድምጡ። እናንተ በኑሮአችሁ የተማመናችሁ ሴቶች ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተስፋ የሚያስቈርጥ ጭንቀት ይደርስባችኋል፤ ከወይንም ሆነ ከሌላው ተክል ሁሉ በቂ ፍሬ አታገኙም። እስከ አሁን ከሐሳብና ከጭንቀት ነጻ ሆናችሁ በመቀማጠል ትኖሩ ነበር፤ አሁን ግን በፍርሃት ተንቀጥቀጡ! ልብሳችሁን አውልቃችሁ በወገባችሁ ላይ ማቅ ታጠቁ! ደስ የሚያሰኘው ለሙ መሬትና የወይን ቦታ ሁሉ ስለ ጠፋ ደረታችሁን እየደቃችሁ አልቅሱ። የእሾኽ ቊጥቋጦና ኲርንችት በሕዝቤ ምድር ላይ በቅሎአል፤ ሕዝቦች በደስታ ይኖሩባቸው ስለ ነበሩት ቤቶችና በደስታ ተሞልታ ስለ ነበረችው ስለዚህች ከተማ አልቅሱ! ቤተ መንግሥቱ ሳይቀር ወና ይሆናል፤ መናገሻ ከተማውም የተፈታ ምድረ በዳ ይሆናል፤ ቤቶችና የመጠበቂያ ማማዎች ይፈርሳሉ፤ የሜዳ አህዮች መራገጫና የመንጋ መሰማርያ ይሆናሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር መንፈሱን በእኛ ላይ የሚያፈስበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ምድረ በዳው ለም ይሆናል፤ ለሙም መሬት ብዙ ፍሬ ይሰጣል። በምድሪቱ ሁሉ ላይ እውነትና ፍትሕ ይሰፍናል። የጽድቅ ሥራ ሰላምን ያስገኛል፤ ውጤቱም ዘለዓለማዊ የሕይወቱ ዋስትና ነው። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከሐሳብና ከጭንቀት ነጻ ይሆናሉ፤ ቤቶቻቸውም በሰላምና በደኅንነት የተሞሉ ይሆናሉ። በበረዶ ዝናብ ደኑ ተጨፍጭፎ ከተማይቱ እስከ መበላሸት ብትደርስም፥ በየውሃው ምንጭ አጠገብ ዘራችሁን ስለምትዘሩና ለከብቶቻችሁና ለአህዮቻችሁ በቂ መሰማርያ ስለምታገኙ በበረከት የተሞላችሁ ትሆናላችሁ።
ኢሳይያስ 32:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እነሆ፥ ጻድቅ ንጉሥ ይነግሣል፤ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ። ሰውም ቃሉን ይሰውራል፤ በውኃ እንደሚጠልቅም ይሰወራል፤ ክብሩም በደረቅ ምድር እንደሚፈስስ ውኃ በጽዮን ይገለጣል። እንግዲህ በሰው አይታመኑም፤ በጆሮአቸው ያዳምጣሉ እንጂ። የደካሞች ሰዎች ልብ ዕውቀትን ትሰማለች፤ የተብታቦችም ምላስ ፈጥና የሰላምን ነገር ትማራለች። ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍን አለቃ ይሆን ዘንድ ግድ አይሉትም፤ ከእንግዲህ ሎሌህ ዝም በል አይልህም። ሰነፍ ግን ስንፍናን ይናገራል፤ ልቡም ዐመፅን ያደርግ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ላይ ስሕተትን ይናገር ዘንድ፥ የተራበችውንም ሰውነት ይበትን ዘንድ፥ የተጠማችንም ነፍስ ባዶ ያደርግ ዘንድ ከንቱን ያስባል። በዐመፃቸው ነገር ድሃውን ይገድሉት ዘንድ፥ የድሆችንም ፍርድ ይገለብጡ ዘንድ የክፉዎች ሕሊና ዐመፅን ትመክራለች። ጻድቃን ግን ጥበብን ይመክራሉ፤ ምክራቸውም ትጸናለች። እናንተ ባለጸጎች ሴቶች ሆይ፥ ተነሡ፤ ድምፄንም ስሙ፤ እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ልጆች ሆይ፥ ንግግሬን አድምጡ። በየዓመቱ የኀዘን በዓል መታሰቢያ አድርጉ፤ ወይን መቍረጥ አልፎአል፤ ፍሬ ማከማችትም አልቆአል፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይመጣም። እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ደንግጡ፤ ሴቶች ሆይ፥ እዘኑ፤ ልብሳችሁንም አውልቁ፤ ዕራቁታችሁንም ሁኑ፤ ወገባችሁንም በማቅ ታጠቁ። ስለ ተወደደችዉ እርሻ ስለሚያፈራውም ወይን ደረታችሁን ድቁ። በሕዝቤ ምድር ላይ በእርሻቸውም ላይ እሾህና አሜከላ ይበቅላሉ፤ ደስታም ከቤታቸው ሁሉ ይጠፋል። የበለጸገች ከተማና ቤቶችዋ ምድረ በዳ ይሆናሉ። የከተማውን ሀብትና ያማሩ ቤቶችን ይተዋሉ፤ አንባዎችም ለዘለዓለም ዋሻ፥ የምድረ በዳም አህያ ደስታ፥ የመንጎችም ማሰማሪያ ይሆናሉ። ይህም፥ መንፈስ ከላይ እስኪመጣላችሁ፥ ምድረ በዳውም ፍሬያማ እርሻ እስኪሆን፥ ፍሬያማውም እርሻ ዱር ተብሎ እስኪቈጠር ድረስ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ፍርድ በምድረ በዳ ይኖራል፤ ጽድቅም በፍሬያማው እርሻ ያድራል። የጽድቅም ሥራ ሰላም ይሆናል፤ ጽድቅም የዕረፍት ቦታን ይይዛል፤ ለዘለዓለምም ይታመኑበታል። ሕዝቤም በሰላም ከተማ ይኖራል። ተዘልሎም በውስጥዋ ያድራል፤ በብልጽግናም ያርፋል። በረዶ ቢወርድ አይደርስባችሁም፤ በዛፍ ሥር የሚኖሩ ሰዎች በበረሃ እንደሚኖሩ ሰዎች ታምነው ይኖራሉ። ውኃ ባለበት፥ በሬና አህያም በሚረግጠው ቦታ የሚዘሩ ብፁዓን ናቸው።
ኢሳይያስ 32:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እነሆ፤ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፤ ገዦችም በፍትሕ ይገዛሉ። እያንዳንዱ ሰው ከነፋስ መከለያ፣ ከወጀብም መጠጊያ ይሆናል። በበረሓም እንደ ውሃ ምንጭ፣ በተጠማም ምድር እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል። የሚያዩ ሰዎች ዐይን ከእንግዲህ አይጨፈንም፤ የሚሰሙም ጆሮዎች ነቅተው ያደምጣሉ። የችኵል አእምሮ ያውቃል፤ ያስተውላልም፤ የተብታባም ምላስ የተፈታ ይሆናል፤ አጥርቶም ይናገራል። ከእንግዲህ ሰነፍ ጨዋ አይባልም፤ ጋጠወጥም አይከበርም። ሰነፍ ስንፍናን ይናገራል፤ አእምሮው ክፋትን ያውጠነጥናል፤ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌለበትን አድራጎት ይፈጽማል፤ በእግዚአብሔርም ላይ የስሕተት ቃል ይናገራል፤ ለተራበ ምግብ ይከለክላል፤ ለተጠማ ውሃ አይሰጥም። የጋጠወጥ ዘዴ ክፉ ነው፤ የችግረኛም አቤቱታ ትክክል ቢሆን፣ ድኻን በሐሰት ለማጥፋት፣ ክፋት ያውጠነጥናል። ጨዋ ግን ሐሳቡም ጨዋ ነው፤ በጨዋነት ምግባርም ጸንቶ ይገኛል። እናንተ ትዕቢት የወጠራችሁ ሴቶች፣ ተነሡ፤ ድምፄን ስሙ፤ እናንተ ተደላድላችሁ የምትኖሩ ሴቶች ልጆች ሆይ፤ የምነግራችሁን አድምጡ! ዓመቱ ገና እንዳለፈ፣ ተደላድላችሁ የነበራችሁ ትንቀጠቀጣላችሁ፤ የወይን ተክል ፍሬ አይሰጥም፤ የፍራፍሬም ወቅት አይመጣም። እናንተ ትዕቢት የወጠራችሁ ሴቶች ተንቀጥቀጡ፤ እናንተ ተደላድላችሁ የምትኖሩ ሴቶች ልጆች፣ በፍርሀት ተርበትበቱ! ልብሳችሁን አውልቁ፤ ወገባችሁን በማቅ ታጠቁ። ስለ ለሙ መሬት ደረታችሁን ምቱ፤ ስለ ፍሬያማው የወይን ተክል ዕዘኑ፤ ስለ ሕዝቤ ምድር፣ እሾኽና አሜከላ ስለ በቀለበት ምድር፣ ስለ ፈንጠዝያ ቤቶች ሁሉ፣ ስለዚህችም መፈንጫ ከተማ አልቅሱ። ዐምባ ምሽጉ ወና ይሆናል፤ ውካታ የበዛበት ከተማ ጭር ይላል፤ ምሽጉና ማማው ለዘላለሙ ዋሻ፣ የዱር አህያ መፈንጫ፣ የመንጋም መሰማሪያ ይሆናል፤ ይህም የሚሆነው መንፈስ ከላይ እስኪፈስስልን፣ ምድረ በዳው ለም መሬት፣ ለሙ መሬትም ጫካ እስኪመስል ድረስ ነው። በምድረ በዳ ፍትሕ ይሰፍናል፤ በለሙም መሬት ጽድቅ ይኖራል፤ የጽድቅ ፍሬ ሰላም፣ የጽድቅ ውጤትም ጸጥታና ለዘላለም ያለ ሥጋት ይሆናል። ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ መኖሪያ፣ በሚያስተማምን ቤት፣ ጸጥ ባለም ስፍራ ዐርፎ ይኖራል። ደኑ በበረዶ ቢመታ፣ ከተማውም ፈጽሞ ቢወድም፣ በየወንዙ ዳር ዘር የምትዘሩ፣ በሬዎቻችሁንና አህዮቻችሁን በነጻነት የምታሰማሩ፣ ምንኛ ብፁዓን ናቸው።
ኢሳይያስ 32:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነሆ፥ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፥ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ። ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፥ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፥ በበረሃም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል። የሚያዩትም ሰዎች ዓይኖች አይጨፈኑም፥ የሚሰሙትም ጆሮዎች ያደምጣሉ። ጥንቃቄ የሌላቸው ሰዎች ልብ እውቀትን ታስተውላለች፥ የተብታቦችም ምላስ ደኅና አድርጋ ትናገራለች። ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍ ከበርቴ ተብሎ አይጠራም፥ ንፉግም ለጋስ አይባልም። ሰነፍ ግን ስንፍናን ይናገራል፥ ልቡም ዝንጉነትን ይፈጽም ዘንድ በእግዚአብሔርም ላይ ስህተትን ይናገር ዘንድ፥ የተራበችውንም ሰውነት ባዶ ያደርግ ዘንድ ከተጠማም ሰው መጠጥን ይቈርጥ ዘንድ በደልን ይሠራል። የንፉግም ዕቃ ክፉ ናት፥ ችግረኛ ቅን ነገርን በተናገረ ጊዜ እንኳን እርሱ በሐሰት ቃል ድሀውን ያጠፋ ዘንድ ክፉን አሳብ ያስባል። ከበርቴ ሰው ግን ለመከበር ያስባል፥ ለመከበርም ጸንቶ ይኖራል። እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፥ ተነሡ ድምፄንም ስሙ፥ እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ልጆች ሆይ፥ ንግግሬን አድምጡ። እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ሆይ፥ ወይንን መቍረጥ ይጠፋልና፥ ፍሬም ማከማቸት አይመጣምና ከዓመትና ከጥቂት ቀን በኋላ ትንቀጠቀጣላችሁ። እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፥ ተጠንቀቁ፥ ተማምናችሁም የምትቀመጡ ሆይ፥ ተንቀጥቀጡ፥ ልብሳችሁን አውልቁ፥ ዕራቁታችሁን ሁኑ፥ ወገባችሁንም በማቅ ታጠቁ። ስለተወደደችውም እርሻ ስለሚያፈራውም ወይን ደረታችሁን ድቁ። በሕዝቤ ምድር ላይ፥ በደስታ ከተማ ባሉት በደስታ ቤቶች ሁሉ ላይ እሾህና ኵርንችት ይወጣባቸዋል፥ አዳራሹ ወና ትሆናለችና፥ የብዙ ሰውም ከተማ ትለቀቃለችና፥ አምባውና ግንቡም ለዘላለም ዋሻ፥ የምድረ በዳም አህያ ደስታ፥ የመንጎችም ማሰማርያ ይሆናልና። ይህም፥ መንፈስ ከላይ እስኪፈስስልን፥ ምድረ በዳውም ፍሬያማ እርሻ እስኪሆን፥ ፍሬያማውም እርሻ ዱር ተብሎ እስኪቈጠር ድረስ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ፍርድ በምድረ በዳ ይኖራል፥ ጽድቅም በፍሬያማው እርሻ ያድራል። የጽድቅም ሥራ ሰላም፥ የጽድቅም ፍሬ ለዘላለም ጸጥታና መታመን ይሆናል። ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል። በረዶው ግን በዱር ላይ ይውርዳል፥ ከተማም ፈጽማ ትዋረዳለች። እናንተ የበሬና የአህያ እግር እየነዳችሁ በውሃ ሁሉ አጠገብ የምትዘሩ ብፁዓን ናችሁ።
ኢሳይያስ 32:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነሆ፥ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፥ መሳፍንትም በፍትህ ያስተዳድራሉ። ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፥ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፥ በበረሃም አገር እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል። የሚያዩትም ሰዎች ዐይኖች አይጨፈኑም፤ የሚሰሙትም ጆሮዎች ያደምጣሉ። ጥንቃቄ የሌላቸው ሰዎች ልብ እውቀትን ታስተውላለች፤ የተብታቦችም ምላስ ተፍታታና ደኅና አድርጋ ትናገራለች። ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍ ጨዋ ተብሎ አይጠራም፤ ሸንጋይ ሰው የተከበረ አይባልም። ሰነፍ ግን የስንፍናን ነገር ይናገራል፤ ልቡም በጌታም ላይ ስህተትን ለመናገር፥ የተራበችውንም ሰውነት ረሃቡን እንዳያስታግስ፥ የተጠማም ሰው ጥሙን እንዳይቆርጥ በደልን ለመሥራት ክፋትን ያቅዳል። የሸንጋይ ሽንገላ ክፉ ናት፤ የችግረኛም አቤቱታ ትክክል ቢሆንም እንኳን በሐሰት ቃል ድሀውን ለማጥፋት ክፉን አሳብ ያስባል። ከበርቴ ሰው ግን ለመከበር ያስባል፤ ለመከበርም ጸንቶ ይኖራል። እናንተ ዓለመኛ ሴቶች ሆይ፥ ተነሡ ድምፄንም ስሙ፤ እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴት ልጆች ሆይ፥ ንግግሬን አድምጡ። እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ሆይ፥ ወይንን መቁረጥ ይጠፋልና፥ ፍሬም ማከማቸት አይመጣምና ከዓመትና ከጥቂት ቀን በኋላ ትንቀጠቀጣላችሁ። እናንተ ዓለመኛ ሴቶች ሆይ፥ በፍርሃት ራዱ፤ ተማምናችሁ የምትቀመጡ፥ ተንቀጥቀጡ፤ ልብሳችሁን አውልቁ፥ ዕራቁታችሁን ሁኑ፥ ወገባችሁንም በማቅ ታጠቁ። ስለ ለሙ እርሻ፥ ስለፍሬያማውም ወይን ደረታችሁን ድቁ። በሕዝቤ ምድር ላይ፥ በደስታ ከተማ ባሉት በደስታ ቤቶች ሁሉ ላይ እሾህና ኩርንችት ይበቅልባቸዋል። አዳራሹ ወና ይሆናል፥ በሰው የተጨናነቀውም ከተማ ወና ይሆናል፤ ምሽጉና ግንቡም ለዘለዓለም ዋሻ፥ የምድረ በዳም አህያ ደስታ፥ የመንጎችም ማሰማርያ ይሆናል። መንፈስ ከላይ እስኪፈስልን፥ ምድረ በዳውም ፍሬያማ እርሻ እስኪሆን፥ ፍሬያማውም እርሻ ዱር ተብሎ እስኪቈጠር ድረስ ይህ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ፍትህ በምድረ በዳ ይኖራል፥ ጽድቅም በፍሬያማው እርሻ ያድራል። የጽድቅም ሥራ ሰላም፥ የጽድቅም ፍሬ ለዘለዓለም ጸጥታና መታመን ይሆናል። ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ፥ በታመነ ቤት፥ በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል። ደኑ ፈጽሞ ይጠፋል፤ ከተማም እንዳልነበረ ትፈራርሳለች። እናንተ የበሬና የአህያ እግር እየነዳችሁ በውሃ ዳርቻ የምትዘዋወሩ ምን ያህል ትደሰቱ!