ትንቢተ ኢሳይያስ 32
32
በጽድቅ የሚያስተዳድር ንጉሥ
1እነሆ፥ ጻድቅ ንጉሥ ይነግሣል፤ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ። 2ሰውም ቃሉን ይሰውራል፤ በውኃ እንደሚጠልቅም ይሰወራል፤ ክብሩም በደረቅ ምድር እንደሚፈስስ ውኃ በጽዮን ይገለጣል። 3እንግዲህ በሰው አይታመኑም፤ በጆሮአቸው ያዳምጣሉ እንጂ። 4የደካሞች ሰዎች ልብ ዕውቀትን ትሰማለች፤ የተብታቦችም ምላስ ፈጥና የሰላምን ነገር ትማራለች። 5ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍን አለቃ ይሆን ዘንድ ግድ አይሉትም፤ ከእንግዲህ ሎሌህ ዝም በል አይልህም።#ዕብ. “ሰነፍ ከበርቴ ተብሎ አይጠራም፥ ንፉግም ለጋስ አይባልም” ይላል። 6ሰነፍ ግን ስንፍናን ይናገራል፤ ልቡም ዐመፅን ያደርግ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ላይ ስሕተትን ይናገር ዘንድ፥ የተራበችውንም ሰውነት ይበትን ዘንድ፥ የተጠማችንም ነፍስ ባዶ ያደርግ ዘንድ ከንቱን ያስባል። 7በዐመፃቸው ነገር ድሃውን ይገድሉት ዘንድ፥ የድሆችንም ፍርድ ይገለብጡ ዘንድ የክፉዎች ሕሊና ዐመፅን ትመክራለች። 8ጻድቃን ግን ጥበብን ይመክራሉ፤ ምክራቸውም ትጸናለች።#ዕብ. “ከበርቴ ሰው ግን ለመክበር ያስባል ፤ በመከበርም ጸንቶ ይኖራል” ይላል።
9እናንተ ባለጸጎች ሴቶች ሆይ፥ ተነሡ፤ ድምፄንም ስሙ፤ እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ልጆች ሆይ፥ ንግግሬን አድምጡ። 10በየዓመቱ የኀዘን በዓል መታሰቢያ አድርጉ፤ ወይን መቍረጥ አልፎአል፤ ፍሬ ማከማችትም አልቆአል፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይመጣም። 11እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ደንግጡ፤ ሴቶች ሆይ፥ እዘኑ፤ ልብሳችሁንም አውልቁ፤ ዕራቁታችሁንም ሁኑ፤ ወገባችሁንም በማቅ ታጠቁ። 12ስለ ተወደደችዉ እርሻ ስለሚያፈራውም ወይን ደረታችሁን ድቁ። 13በሕዝቤ ምድር ላይ በእርሻቸውም ላይ እሾህና አሜከላ ይበቅላሉ፤ ደስታም ከቤታቸው ሁሉ ይጠፋል። 14የበለጸገች ከተማና ቤቶችዋ ምድረ በዳ ይሆናሉ። የከተማውን ሀብትና ያማሩ ቤቶችን ይተዋሉ፤ አንባዎችም ለዘለዓለም ዋሻ፥ የምድረ በዳም አህያ ደስታ፥ የመንጎችም ማሰማሪያ ይሆናሉ። 15ይህም፥ መንፈስ ከላይ እስኪመጣላችሁ፥ ምድረ በዳውም ፍሬያማ እርሻ እስኪሆን፥ ፍሬያማውም እርሻ ዱር ተብሎ እስኪቈጠር ድረስ ይሆናል።
16ከዚያ በኋላ ፍርድ በምድረ በዳ ይኖራል፤ ጽድቅም በፍሬያማው እርሻ ያድራል። 17የጽድቅም ሥራ ሰላም ይሆናል፤ ጽድቅም የዕረፍት ቦታን ይይዛል፤ ለዘለዓለምም ይታመኑበታል። 18ሕዝቤም በሰላም ከተማ ይኖራል። ተዘልሎም በውስጥዋ ያድራል፤ በብልጽግናም ያርፋል። 19በረዶ ቢወርድ አይደርስባችሁም፤ በዛፍ ሥር የሚኖሩ ሰዎች በበረሃ እንደሚኖሩ ሰዎች ታምነው ይኖራሉ። 20ውኃ ባለበት፥ በሬና አህያም በሚረግጠው ቦታ የሚዘሩ ብፁዓን ናቸው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 32: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ