ትንቢተ ኢሳይያስ 31
31
እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንደሚጠብቃት
1ርዳታ ለመፈለግ ወደ ግብፅ ለሚወርዱ፥ በፈረሶችና በሰረገሎችም ለሚታመኑ ወዮላቸው! ፈረሰኞቹ ብዙዎች ናቸውና፤ በእስራኤልም ቅዱስ አልታመኑምና፤ እግዚአብሔርንም አልፈለጉምና። 2እርሱ ግን ጠቢብ ነው፤ ክፉንም ነገር በላያቸው ያመጣል፤ ቃሉንም አይመልስም፤ በክፉዎችም ሰዎች ቤት ላይ በከንቱ ተስፋቸውም ላይ ይነሣል። 3ግብፃውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ እጁን በዘረጋ ጊዜ፥ ረጂው ይሰናከላል፤ ተረጂውም ይወድቃል፤ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ።
4እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛልና፥ “አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል በንጥቂያው ላይ እንደሚያገሣ፥ ድምፁም ተራሮችን እስኪሞላ በእርሱ ላይ እንደሚጮህ፥ እረኞችም ሁሉ ሲጮሁበት ከብዛታቸው የተነሣ እንደማይፈራ፥ ከድምፃቸውም የተነሣ እንደማይደነግጥ፥ እነርሱም ከቍጣው ብዛት የተነሣ ድል እንደሚሆኑና እንደሚደነግጡ፥ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራና በኮረብታዋ ላይ ይዋጋ ዘንድ ይወርዳል። 5እንደሚበርር ወፍ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይጋርዳታል፤ ይከልላታልም፤ ይታደጋታል፤ አልፎም ያድናታል። 6ትበድሉ ዘንድ ጥልቅ ምክርን የምትመክሩ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ። 7በዚያም ቀን እያንዳንዳቸው እጆቻቸው የሠሩአቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቻቸውን ይጥላሉ። 8አሦርም ይወድቃል፤ የሚወድቀውም በሰው ሰይፍ አይደለም፤ የምትበላቸውም የሰው ሰይፍ አይደለችም፤ የሚሸሹም ከሰይፍ ፊት አይደለም ጐልማሶቻቸው ግን ይሸነፋሉ። 9ዓለትም ትውጣቸዋለች ድልም ይሆናሉ የሸሸም ይያዛል። በጽዮን ዘርእ፥ በኢየሩሳሌምም ቤቶች ያሉት ብፁዕ ነው” ይላል እግዚአብሔር። #ዕብ. “እሳቱ በጽዮን እቶኑም በኢየሩሳሌም የሆነ እግዚአብሔር” ይላል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 31: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ