እነሆ፥ ጻድቅ ንጉሥ ይነግሣል፤ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ። ሰውም ቃሉን ይሰውራል፤ በውኃ እንደሚጠልቅም ይሰወራል፤ ክብሩም በደረቅ ምድር እንደሚፈስስ ውኃ በጽዮን ይገለጣል። እንግዲህ በሰው አይታመኑም፤ በጆሮአቸው ያዳምጣሉ እንጂ። የደካሞች ሰዎች ልብ ዕውቀትን ትሰማለች፤ የተብታቦችም ምላስ ፈጥና የሰላምን ነገር ትማራለች። ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍን አለቃ ይሆን ዘንድ ግድ አይሉትም፤ ከእንግዲህ ሎሌህ ዝም በል አይልህም። ሰነፍ ግን ስንፍናን ይናገራል፤ ልቡም ዐመፅን ያደርግ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ላይ ስሕተትን ይናገር ዘንድ፥ የተራበችውንም ሰውነት ይበትን ዘንድ፥ የተጠማችንም ነፍስ ባዶ ያደርግ ዘንድ ከንቱን ያስባል። በዐመፃቸው ነገር ድሃውን ይገድሉት ዘንድ፥ የድሆችንም ፍርድ ይገለብጡ ዘንድ የክፉዎች ሕሊና ዐመፅን ትመክራለች። ጻድቃን ግን ጥበብን ይመክራሉ፤ ምክራቸውም ትጸናለች። እናንተ ባለጸጎች ሴቶች ሆይ፥ ተነሡ፤ ድምፄንም ስሙ፤ እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ልጆች ሆይ፥ ንግግሬን አድምጡ። በየዓመቱ የኀዘን በዓል መታሰቢያ አድርጉ፤ ወይን መቍረጥ አልፎአል፤ ፍሬ ማከማችትም አልቆአል፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይመጣም። እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ደንግጡ፤ ሴቶች ሆይ፥ እዘኑ፤ ልብሳችሁንም አውልቁ፤ ዕራቁታችሁንም ሁኑ፤ ወገባችሁንም በማቅ ታጠቁ። ስለ ተወደደችዉ እርሻ ስለሚያፈራውም ወይን ደረታችሁን ድቁ። በሕዝቤ ምድር ላይ በእርሻቸውም ላይ እሾህና አሜከላ ይበቅላሉ፤ ደስታም ከቤታቸው ሁሉ ይጠፋል። የበለጸገች ከተማና ቤቶችዋ ምድረ በዳ ይሆናሉ። የከተማውን ሀብትና ያማሩ ቤቶችን ይተዋሉ፤ አንባዎችም ለዘለዓለም ዋሻ፥ የምድረ በዳም አህያ ደስታ፥ የመንጎችም ማሰማሪያ ይሆናሉ። ይህም፥ መንፈስ ከላይ እስኪመጣላችሁ፥ ምድረ በዳውም ፍሬያማ እርሻ እስኪሆን፥ ፍሬያማውም እርሻ ዱር ተብሎ እስኪቈጠር ድረስ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ፍርድ በምድረ በዳ ይኖራል፤ ጽድቅም በፍሬያማው እርሻ ያድራል። የጽድቅም ሥራ ሰላም ይሆናል፤ ጽድቅም የዕረፍት ቦታን ይይዛል፤ ለዘለዓለምም ይታመኑበታል። ሕዝቤም በሰላም ከተማ ይኖራል። ተዘልሎም በውስጥዋ ያድራል፤ በብልጽግናም ያርፋል። በረዶ ቢወርድ አይደርስባችሁም፤ በዛፍ ሥር የሚኖሩ ሰዎች በበረሃ እንደሚኖሩ ሰዎች ታምነው ይኖራሉ። ውኃ ባለበት፥ በሬና አህያም በሚረግጠው ቦታ የሚዘሩ ብፁዓን ናቸው።
ትንቢተ ኢሳይያስ 32 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 32:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች