ኢሳይያስ 28:14-29
ኢሳይያስ 28:14-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህ የተጨነቃችሁ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። እናንተም “ከሲኦል ጋር ተማምለናል፤ ከሞትም ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፤ ሐሰትንም መሸሸጊያን አድርገናልና፥ በሐሰትም ተሰውረናልና፥ ዐውሎ ነፋስም ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም” ትላላችሁና፥ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ ዋጋው ብዙ የሆነውን፥ የተመረጠውን፥ የከበረውንና መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ አኖራለሁ፤ በእርሱም የሚያምን አያፍርም። ፍርዴን ለተስፋ ይቅርታዬንም ለትክክለኛ ሚዛን አደርጋለሁ፤ በከንቱና በሐሰት የሚታመኑ ከዐውሎ ነፋስ አያመልጡም። ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፤ ከኢኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይጸናም፤ የሚያልፍ ዐውሎ ነፋስ በመጣ ጊዜ ይረግጣችኋል፤ ትደክማላችሁም። ባለፈም ጊዜ ይወስዳችኋል፤ ማለዳ ማለዳ በቀን ያልፋል፤ በሌሊት ክፉ ተስፋ ይሆናል፤ እናንተ ያዘናችሁ፥ መስማትን ተማሩ።” መዋጋትን አንችልም፤ እናንተንም ለመሰብሰብ ደካሞች ነን። እግዚአብሔርም በኃጥኣን ተራራ እንደ ነበረ ይነሣል፤ በገባዖን ሸለቆም ይኖራል፤ ሥራውን ማለት መራራ ሥራውን በቍጣ ይሠራል፤ ቍጣውም ድንቅን ያደርጋል፤ መርዙም ልዩ ነው። አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚያደርገውን ያለቀና የተቈረጠ ነገርን ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራታችሁ እንዳይጸናባችሁ እናንተ ደስ አይበላችሁ። አድምጡ፤ ድምፄንም ስሙ፤ ልብ አድርጉ፤ ንግግሬንም ስሙ። በውኑ ገበሬ ሊዘራ ሁልጊዜ ያርሳልን? ወይስ ምድሩን ከማረሱ አስቀድሞ ዘርን ይዘራልን? ጓሉንስ ይከሰክሳልን? እርሻውን ባስተካከለ ጊዜ ጥቂት ጥቍሩን አዝሙድ፥ ከሙኑንም፥ ዳግመኛም ስንዴውን፥ ገብሱንም፥ አጃውንም በየስፍራው የሚዘራ አይደለምን? ምድርም የእግዚአብሔርን ፍርድ ተምራ ደስ ይላታል። ጥቍሩን አዝሙድ በተሳለች ማሄጃ አያሄድም፤ የሰረገላም መንኰራኵር በከሙን ላይ አይዞርም፤ ነገር ግን ጥቍሩን አዝሙድ በሽመል፥ ከሙኑንም በበትር ይወቃል። እኔ ለዘለዓለም በእናንተ ላይ አልቈጣም፤ የምሕረቴም ድምፅ አያጠፋችሁም። ይህም ደግሞ ድንቅ ምክርን ከሚመክር በግብሩም ገናና ከሆነው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ወጥቶአል። እናንተ ግን ከንቱ መጽናናትን ታበዙ ዘንድ ትሻላችሁ።
ኢሳይያስ 28:14-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ፣ እናንት ፌዘኞች የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። እናንት፣ “ከሞት ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል፤ ከሲኦልም ጋር ስምምነት አድርገናል፤ ውሸትን መጠጊያችን፣ ሐሰትን መደበቂያችን አድርገናል፤ ታላቅ መቅሠፍት እየጠራረገ ሲያልፍ፣ ሊነካን አይችልም” በማለት ታብያችኋል። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ የተፈተነ ድንጋይ፣ የመሠረት ድንጋይ፣ ለጽኑ መሠረት የሚሆን የከበረ የማእዘን ድንጋይ፣ በጽዮን አስቀምጣለሁ፤ በእርሱም የሚያምን አያፍርም። ፍትሕን የመለኪያ ገመድ፣ ጽድቅንም ቱንቢ አደርጋለሁ፤ ውሸት መጠጊያችሁን የበረዶ ዝናብ ይጠራርገዋል፤ መደበቂያችሁንም ውሃ ያጥለቀልቀዋል። ከሞት ጋር የገባችሁት ቃል ኪዳን ይሻራል፤ ከሲኦልም ጋር ያደረጋችሁት ስምምነት ይፈርሳል፤ ታላቁ መቅሠፍት እየጠራረገ ሲያልፍ፣ እናንተም ትጠራረጋላችሁ። በመጣ ቍጥር ይዟችሁ ይሄዳል፤ ማለዳ ማለዳ፣ በቀንና በሌሊትም ይጠራርጋል።” ይህን ቃል ብታስተውሉ፣ ሽብር በሽብር በሆነ ነበር። እግር ዘርግቶ እንዳይተኛ ዐልጋው ዐጭር ነው፤ ሰውነትንም ለመሸፋፈን ብርድ ልብሱ ጠባብ ነው። እግዚአብሔር ሥራውን፣ አዎን ድንቅ ሥራውን ሊሠራ፣ ተግባሩን፣ እንግዳ የሆነ ተግባሩን ሊያከናውን፣ በፐራሲም ተራራ እንዳደረገው ይነሣል፣ በገባዖን ሸለቆ እንዳደረገው ይነሣሣል። እንግዲህ ፌዛችሁን አቁሙ፤ አለዚያ እስራታችሁ ይጸናባችኋል፤ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ መላውን ምድር ለማጥፋት ያወጀውን ዐዋጅ ሰምቻለሁ። አድምጡ ድምፄን ስሙ፤ አስተውሉ ቃሌንም ስሙ። ገበሬ ሊዘራ መሬቱን ሲያዘጋጅ ያለ ማቋረጥ ያርሳልን? ጓሉን ሲከሰክስ፣ ዐፈሩን ሲያለሰልስ ይከርማልን? ዕርሻውን አስተካክሎ፣ ጥቍር አዝሙድና ከሙን አይዘራምን? ስንዴውንስ በትልሙ፣ ገብሱን በተገቢ ቦታው፣ አጃውንም በተመደበው ስፍራ አይዘራምን? አምላኩ ያስተምረዋል፤ ትክክለኛውንም መንገድ ያሳየዋል። ጥቍር አዝሙድ በመውቂያ መሣሪያ አይወቃም፤ ከሙን የሠረገላ መንኰራኵር አይሄድበትም፤ ጥቍር አዝሙድ በበትር፣ ከሙንም በዘንግ ይወቃል። እንጀራን ለመጋገር እህል ይፈጫል፤ ስለዚህ አንድ ሰው ለዘላለም እህል ሲወቃ አይኖርም። የመውቂያውን መንኰራኵር ቢያኼድበትም፣ ፈረሶቹ አይደፈጥጡትም። ይህ ሁሉ የሚሆነው በምክሩ ድንቅ፣ በጥበቡ ታላቅ ከሆነው፣ ከሰራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
ኢሳይያስ 28:14-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ ፌዘኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። እናንተም፦ ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፥ ከሲኦልም ጋር ተማምለናል፥ ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፥ በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም ስላላችሁ፥ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፥ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ፥ የሚያምንም አያፍርም። ለገመድ ፍርድን ለቱንቢም ጽድቅን አደርጋለሁ፥ በረዶውም የሐሰትን መሸሸጊያ ይጠርጋል፥ ውኆችም መሰወሪያውን ያሰጥማሉ። ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፥ ከሲኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይጸናም፥ የሚትረፈረፍ መቅሰፍት ባለፈ ጊዜ ትረገጡበታላችሁ። ባለፈም ጊዜ ይወስዳችኋል፥ ማለዳ ማለዳ ቀንና ሌሊት ያልፋል፥ ወሬውንም ማስተዋል ድንጋጤ ይሆናል። ሰው በእርሱ ላይ ተዘርግቶ ቢተኛ አልጋው አጭር ነው፥ ሰውም ሰውነቱን መሸፈን ቢወድድ መጎናጸፊያ ጠባብ ነው። እግዚአብሔርም ሥራውን ማለት እንግዳ ሥራውን ይሠራ ዘንድ፥ አድራጎቱንም ማለት ያልታወቀውን አድራጎቱን ያደርግ ዘንድ በፐራሲም ተራራ እንደ ነበረ ይነሣል፥ በገባዖንም ሸለቆ እንደ ነበረ ይቈጣል። አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚጸናውን የጥፋት ትእዛዝ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ። አድምጡ ድምፄንም ስሙ፥ ልብ አድርጉ ንግግሬንም ስሙ። በውኑ ገበሬ ሊዘራ ሁልጊዜ ያርሳልን? ወይስ ሁልጊዜ እርሻውን ይገለግላልን? ጓሉንስ ይከሰክሳልን? እርሻውን ባስተካከለ ጊዜ ጥቁሩን አዝሙድ፥ ከሙኑንም፥ ስንዴውንም በተርታ፥ ገብሱንም በስፍራው፥ አጃውንም በደረጃው የሚዘራ አይደለምን? ይህንም ብልሃት አምላኩ ያስታውቀዋል ያስተምረውማል። ጥቁሩ አዝሙድ በተሳለች ማሄጃ አያኬድም፥ የሰረገላም መንኮራኵር በካሙን ላይ አይዞርም፥ ነገር ግን ጥቁሩ አዝሙድ በሽመል ከሙኑም በበትር ይወቃል። የእንጀራ እህል ይደቅቃልን? ለዘላለም አያኬደውም፥ የሰረገላውን መንኮራኵርና ፈረሶቹን ምንም ቢያስኬድበት አያደቅቀውም። ይህም ደግሞ ድንቅ ምክር ከሚመክር በግብሩም ማለፊያ ከሆነው ከሠራዊቱ ጌታ ከእግዚአብሔር ወጥቶአል።
ኢሳይያስ 28:14-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚህ ሕዝብ ላይ ተሾማችሁ ኢየሩሳሌምን የምትገዙ እናንተ ፌዘኞች፥ እግዚአብሔር የሚለውን አድምጡ፤ “ከሞት ጋር ስምምነት አድርገናል፤ ከሙታንም ዓለም ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል” እያላችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲሁም “ማታለልን እንደ መጠለያ፥ ሐሰትንም እንደ መጠጊያ አምባ ስላደረግን መቅሠፍት በሚመጣበት ጊዜ ሳይነካን ያልፋል” ብላችሁ ተስፋ ታደርጋላችሁ። ስለዚህም ጌታ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “እነሆ፥ የጸና የመሠረት ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ፤ እርሱም የተመሰከረለት፥ የከበረ የማእዘን ድንጋይ ነው፤ በእርሱም የሚያምን ሁሉ አይናወጥም። የመሠረቱ መለኪያ ፍትሕ፥ ቱምቢውም ታማኝነት ይሆናሉ፤” መጠጊያችን ነው ብላችሁ የምትተማመኑበትን ሐሰት የበረዶ ወጀብ ይመታዋል፤ የምትሸሸጉበትንም ቦታ ጐርፍ ይጠራርገዋል። ከሞት ጋር የገባችሁት ስምምነት ይቀራል፤ ከሙታን ዓለም ጋር የገባችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፤ መቅሠፍት በድንገት በሚመጣበት ጊዜ መጨረሻችሁ ይሆናል። እርሱም ባለፈ ቊጥር ይወስዳችኋል፤ እርሱም በየማለዳው በቀንና በሌሊት ያልፋል፤ ይህን መልእክት መረዳት የሚያመጣው ሽብርን ብቻ ነው። የሚከተለው ምሳሌ እንደ ተነገረበት ሰው ትሆናላችሁ፤ ይህም ሰው በጣም አጭር በሆነ ድንክ አልጋ ላይ ተኝቶ እግሩን መዘርጋት ተሣነው፤ ልብሱም ጠባብ ከመሆኑ የተነሣ ሰውነቱን በሙሉ መሸፈን አልቻለም። እግዚአብሔር በጰራጺም ተራራ ላይና በገባዖን ሸለቆ ላይ እንዳደረገው፥ አሁንም ያልተለመደ ሥራውን ለመሥራትና ለሰው እንግዳ የሆነው ተግባሩን ለመፈጸም ይነሣል። ጌታ የሠራዊት አምላክ አገሪቱን በሞላ ለማጥፋት መወሰኑን ስለ ሰማሁ ማፌዝ ይቅርባችሁ፤ አለበለዚያ እስራታችሁ ይጠብቅባችኋል። የምነግራችሁን አድምጡ፤ የምላችሁንም ሁሉ በጥንቃቄ ስሙ። ማሳውን ለዘርና ለተክል ለማዘጋጀት ያለማቋረጥ ሲያርስና ጓሉን እያፈረሰ ሲጐለጒል የሚኖር ገበሬ አለን? አንድ ጊዜ መሬቱን ካስተካከለ በኋላ ጥቊር አዝሙድና ከሙን፥ ስንዴና ገብስ እንዲሁም አጃ የመሳሰሉትን አዝርዕት በየምድቡ ይዘራ የለምን? ከአምላኩ የተማረ ስለ ሆነ ትክክለኛውን መንገድ ያውቃል። ጥቊር አዝሙድን፥ ከሙንን በብረት መውቂያ በሠረገላ መንኰራኲር አይወቃም፤ ከዚህ ይልቅ መጠነኛ ክብደት ባለው በትር ይወቃል። ስንዴና ገብስ ይወቃሉ እንጂ እንዲደቁ አይደረጉም፤ ሠረገላና ፈረስ በላያቸው ላይ ቢነዱም እንኳ እንዲደቁ አይደረጉም። የዚህ ሁሉ ጥበብ መገኛ የሠራዊት አምላክ ነው፤ እርሱ አስደናቂ መካሪ ጥበቡም ፍጹም ነው።
ኢሳይያስ 28:14-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ ፌዘኞች ሆይ፥ የጌታን ቃል ስሙ። እናንተም፦ “ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፥ ከሲኦልም ጋር ተማምለናል፤ ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፥ በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም” ስላላችሁ፥ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ፤ “የሚያምን አያፍርም።” ለገመድ ፍትህን፥ ለቱንቢም ጽድቅን አደርጋለሁ፤ በረዶውም የሐሰትን መሸሸጊያ ይጠርጋል፥ ውኆችም መሰወሪያውን ያሰጥማሉ። ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፥ ከሲኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይጸናም፤ የሚትረፈረፍ መቅሰፍት ባለፈ ጊዜ ትረገጡበታላችሁ። ባለፈም ጊዜ ይወስዳችኋል፤ እለት ከእለት፥ ቀንና ሌሊት ያልፋል፤ ወሬውንም መስማት ፍርሃት ያሳድራል። ሰው በእርሱ ላይ ተዘርግቶ ቢተኛ አልጋው አጭር ነው፤ ሰውም ሰውነቱን መሸፈን ቢወድድ መጎናጸፊያ ጠባብ ነው። ጌታም፥ በፐራሲም ተራራ እንዳደረገው፥ በገባዖንም ሸለቆ እንዳደረገው፥ ሥራውን ለመሥራት፥ አስደናቂ ሥራውን! ተግባሩን ለመፈጸም፥ አስገራሚ ተግባሩን! ይነሣል፤ ይነሣሣልም። አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚጸናውን የጥፋት ትእዛዝ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ። አድምጡ ድምፄንም ስሙ፤ ልብ አድርጉ ንግግሬንም ስሙ። በውኑ ገበሬ ሊዘራ ሁልጊዜ ያርሳልን? ወይስ መሬቱን ሲገለብጥ፥ ዐፈሩን ሲያለሰልስ ይከርማል? እርሻውን አስተካክሎ ጥቁሩን አዝሙድ፥ ከሙኑንም፥ ስንዴውንም በተርታ፥ ገብሱንም በስፍራው፥ አጃውንም በደረጃው አይዘራምን? ይህንም ብልሃት አምላኩ ያሳውቀዋል ያስተምረውማል። ጥቁሩ አዝሙድ በመውቂያ አይወቃም፥ ከሙንም የሠረገላ መንኰራኵር አይዞርበትም፤ ነገር ግን ጥቁሩ አዝሙድ በሽመል ከሙኑም በበትር ይወቃል። እንጀራን ለመጋገር እህል ይፈጫል፤ ነገር ግን ለዘለዓለም አይፈጨውም፤ የሠረገላውን መንኰራኵርና ፈረሶቹን ምንም ቢያስኬድበት አያደቀውም። ይህም ደግሞ በምክሩ ድንቅ በጥበቡ የላቀ ከሆነው ከሠራዊት ጌታ ወጥቶአል።