ትንቢተ ኢሳይያስ 28
28
ለሰሜናዊው መንግሥት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
1ከለምለሙ ሸለቆ በላይ ላለችው የሰማርያ ከተማ ወዮላት! መሪዎችዋ በመጠጥ የተሞሉ ሰካራሞች ናቸው ነገር ግን እነርሱ ደርቆ እንደሚረግፍ አበባ ይሆናሉ። 2እነሆ፥ ጌታ እንደ በረዶ ወጨፎ፥ እንደሚያጠፋ ዐውሎ ነፋስና እንደሚያጥለቀልቅ ኀይለኛ የውሃ ጐርፍ የሆነ አንድ ጠንካራና ኀያል ሰው አለው። ይህም ሰው በሥልጣኑ ወደ ምድር አሽቀንጥሮ ይጥላቸዋል። 3የእስራኤላውያን ሰካራሞች የትዕቢት ዘውድ በእግር ይረገጣል 4ከለምለሙ ሸለቆ በላይ ያለችው ሰማርያ በፍጥነት ክብርዋን ታጣለች፤ እርስዋም እንደሚረግፍ አበባና በበለስ ወራት መጀመሪያ በስለው በመገኘታቸው ተለቅመው እንደሚበሉ የበለስ ፍሬዎች ትሆናለች።
5በዚያን ጊዜ የሠራዊት አምላክ ከሞት ለተረፉት ሕዝቡ የክብር አክሊል ይሆናል። 6በዳኝነት ለሚያገለግሉት የፍትሕ ጥበብ ይሰጣቸዋል፤ የከተማይቱን የቅጽር በሮች ከጠላት ለሚከላከሉትም ኀይልን ይሰጣቸዋል።
ኢሳይያስና ሰካራሞቹ የይሁዳ ነቢያት
7ነቢያቱና ካህናቱ እንኳ ሰክረው ይንገዳገዳሉ፤ ብዙ ወይን ጠጅና የሚያሰክርም ጠንካራ መጠጥ ስለ ጠጡ አእምሮአቸው ታውኮ ይሰናከላሉ፤ ነቢያቱ ሰክረው ከመደናበራቸው የተነሣ እግዚአብሔር የገለጠላቸውን ራእይ አያስተውሉም፤ ካህናቱም እጅግ ስለሚሰክሩ ለሚቀርብላቸው ጉዳይ ተገቢውን ውሳኔ መስጠት አይችሉም። 8የሚመገቡበት ገበታ ሁሉ በትውከት ተሞልቶአል፤ ያልተበላሸ ንጹሕ ስፍራ ከቶ የለም።
9እርሱ ማንን ለማስተማር ይፈልጋል? መልእክቱንስ የሚገልጠው ለማነው? የእርሱ ትምህርት የሚጠቅመው ጡት ለጣሉ ሕፃናት ብቻ አይደለም። 10እርሱ፦ ሊያስተምረን የሚሞክረው ፊደል በፊደል ላይ፥ መስመር በመስመር ላይ፥ ትምህርት በትምህርት ላይ እያነባበረ እንደ ጀማሪ እንድንንተባተብ ነው።
11እነሆ፥ እግዚአብሔር ይህንን ሕዝብ በአልተለመደ አነጋገርና በባዕድ ቋንቋ ይናገራል። 12ዕረፍትንና መጽናናትን ሰጥቶአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን እርሱን ማዳመጥ እምቢ አላችሁ። #1ቆሮ. 14፥21። 13እግዚአብሔር ፊደል በፊደል ላይ፥ መስመር በመስመር ላይ፥ ትምህርት በትምህርት ላይ እያነባበረ ሊያስተምራችሁ የፈቀደው ስለዚህ ነው፤ በዚያን ጊዜ በእርምጃችሁ ሁሉ ትሰናከላላችሁ፤ ትቈስላላችሁ፤ በወጥመድም ተይዛችሁ ትታሰራላችሁ።
ለጽዮን የማእዘን ራስ የሚሆን ድንጋይ
14በዚህ ሕዝብ ላይ ተሾማችሁ ኢየሩሳሌምን የምትገዙ እናንተ ፌዘኞች፥ እግዚአብሔር የሚለውን አድምጡ፤ 15“ከሞት ጋር ስምምነት አድርገናል፤ ከሙታንም ዓለም ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል” እያላችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲሁም “ማታለልን እንደ መጠለያ፥ ሐሰትንም እንደ መጠጊያ አምባ ስላደረግን መቅሠፍት በሚመጣበት ጊዜ ሳይነካን ያልፋል” ብላችሁ ተስፋ ታደርጋላችሁ። 16ስለዚህም ጌታ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “እነሆ፥ የጸና የመሠረት ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ፤ እርሱም የተመሰከረለት፥ የከበረ የማእዘን ድንጋይ ነው፤ በእርሱም የሚያምን ሁሉ አይናወጥም። #መዝ. 118፥22-23፤ ሮም 9፥33፤ 10፥11፤ 1ጴጥ. 2፥6። 17የመሠረቱ መለኪያ ፍትሕ፥ ቱምቢውም ታማኝነት ይሆናሉ፤” መጠጊያችን ነው ብላችሁ የምትተማመኑበትን ሐሰት የበረዶ ወጀብ ይመታዋል፤ የምትሸሸጉበትንም ቦታ ጐርፍ ይጠራርገዋል። 18ከሞት ጋር የገባችሁት ስምምነት ይቀራል፤ ከሙታን ዓለም ጋር የገባችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፤ መቅሠፍት በድንገት በሚመጣበት ጊዜ መጨረሻችሁ ይሆናል። 19እርሱም ባለፈ ቊጥር ይወስዳችኋል፤ እርሱም በየማለዳው በቀንና በሌሊት ያልፋል፤ ይህን መልእክት መረዳት የሚያመጣው ሽብርን ብቻ ነው። 20የሚከተለው ምሳሌ እንደ ተነገረበት ሰው ትሆናላችሁ፤ ይህም ሰው በጣም አጭር በሆነ ድንክ አልጋ ላይ ተኝቶ እግሩን መዘርጋት ተሣነው፤ ልብሱም ጠባብ ከመሆኑ የተነሣ ሰውነቱን በሙሉ መሸፈን አልቻለም። 21እግዚአብሔር በጰራጺም ተራራ ላይና በገባዖን ሸለቆ ላይ እንዳደረገው፥ አሁንም ያልተለመደ ሥራውን ለመሥራትና ለሰው እንግዳ የሆነው ተግባሩን ለመፈጸም ይነሣል። #ኢያሱ 10፥10-12፤ 2ሳሙ. 5፥20፤ 1ዜ.መ. 14፥11።
22ጌታ የሠራዊት አምላክ አገሪቱን በሞላ ለማጥፋት መወሰኑን ስለ ሰማሁ ማፌዝ ይቅርባችሁ፤ አለበለዚያ እስራታችሁ ይጠብቅባችኋል።
የእግዚአብሔር ጥበብ
23የምነግራችሁን አድምጡ፤ የምላችሁንም ሁሉ በጥንቃቄ ስሙ። 24ማሳውን ለዘርና ለተክል ለማዘጋጀት ያለማቋረጥ ሲያርስና ጓሉን እያፈረሰ ሲጐለጒል የሚኖር ገበሬ አለን? 25አንድ ጊዜ መሬቱን ካስተካከለ በኋላ ጥቊር አዝሙድና ከሙን፥ ስንዴና ገብስ እንዲሁም አጃ የመሳሰሉትን አዝርዕት በየምድቡ ይዘራ የለምን? 26ከአምላኩ የተማረ ስለ ሆነ ትክክለኛውን መንገድ ያውቃል። 27ጥቊር አዝሙድን፥ ከሙንን በብረት መውቂያ በሠረገላ መንኰራኲር አይወቃም፤ ከዚህ ይልቅ መጠነኛ ክብደት ባለው በትር ይወቃል። 28ስንዴና ገብስ ይወቃሉ እንጂ እንዲደቁ አይደረጉም፤ ሠረገላና ፈረስ በላያቸው ላይ ቢነዱም እንኳ እንዲደቁ አይደረጉም። 29የዚህ ሁሉ ጥበብ መገኛ የሠራዊት አምላክ ነው፤ እርሱ አስደናቂ መካሪ ጥበቡም ፍጹም ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 28: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997