የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 27

27
1በዚያን ቀን እግዚአብሔር በጽኑ፥ በታላቁና በኀያል ሰይፉ የሚስለከለከውንና የሚጠመጠመውን እባብ ሌዋታንን ይቀጣል፤ የባሕሩንም ዘንዶ ይገድላል። 2በዚያን ጊዜ ፍሬአማ ለሆነው የወይን ተክል ቦታ ዘምሩለት፤ 3እኔ እግዚአብሔር እጠብቀዋለሁ በየጊዜውም ውሃ አጠጣዋለሁ፤ ማንም ሰው እንዳይጐዳው ሌሊትና ቀን እጠብቀዋለሁ። 4ዳግመኛ በወይን ቦታዬ ላይ አልቈጣም፤ የወይን ቦታዬን የሚያበላሹ ኲርንችትና እሾኽ ቢኖሩ ነቃቅዬ በእሳት በማቃጠል ፈጽሞ አጠፋቸዋለሁ። 5ሆኖም የአትክልቱ ቦታ በእኔ ጥበቃ ከተማመነ እርሱ ወዳጄ ይሆናል፤ ከእኔም ጋር በሰላም ይኖራል።
6በሚመጡት ዘመናት የያዕቆብ ዘር የሆኑ የእስራኤል ሕዝብ እንደ ወይን ግንድ ሥር ይሰዳሉ፤ አብበውም ያፈራሉ፤ ፍሬአቸውም ምድርን ይሞላል።
7እስራኤል የተቀጣችው ጠላቶችዋ በእግዚአብሔር የተቀጡትን ያኽል አይደለም፤ የጠላቶችዋንም ያኽል ብዙ ሰው አልተገደለባትም። 8እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ ምርኮ እንዲሰደዱ በማድረግ ቀጣቸው፤ እንደ ኀይለኛ የምሥራቅ ዐውሎ ነፋስም አባረራቸው። 9እንግዲህ የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ለኃጢአታቸው ይቅርታ ማግኘት የሚችሉት የአሕዛብን የመሠዊያ ድንጋዮች እንደ ኖራ ፈጭተው፥ የዕጣን መሠዊያዎችንም ሆነ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስሎች ሲያስወግዱ ነው።
10የተመሸገችው ከተማ ፈራርሳለች፤ ባዶዋን ቀርታ ጭው ያለ ምድረ በዳ መስላለች፤ የከብቶች መሰማሪያ ስለ ሆነች በዚያ ጥጆች የዛፍ ቅርንጫፎችን እየበሉ ያርፋሉ። 11የዛፍ ቅርንጫፎች በሚደርቁበትም ጊዜ ይሰባበራሉ፤ ሴቶችም ለእሳት ማገዶ ይለቅሙአቸዋል፤ ሕዝቡ ማስተዋል ስለ ጐደለው ፈጣሪ አምላኩ አይራራለትም፤ ምንም ምሕረት አያደርግለትም።
12ገበሬ ስንዴውን ከገለባ እንደሚለይ በዚያን ቀን ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ እስከ ግብጽ ወሰን ድረስ ያሉትን ሕዝቡን እስራኤልን እግዚአብሔር አንድ በአንድ ይሰበስባል።
13በዚያም ዘመን ትልቅ መለከት ይነፋል፤ በአሦር ምድር ጠፍተው የነበሩትና ወደ ግብጽ ተሰደው የነበሩት እስራኤላውያንም ተመልሰው በኢየሩሳሌም በሚገኘው በተቀደሰው ተራራ ላይ ይሰግዳሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ