የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 11:1-9

ኢሳይያስ 11:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከእ​ሴይ ሥር በትር ትወ​ጣ​ለች፤ አበ​ባም ከግ​ንዱ ይወ​ጣል። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ፈስ፥ የጥ​በ​ብና የማ​ስ​ተ​ዋል መን​ፈስ፥ የም​ክ​ርና የኀ​ይል መን​ፈስ፥ የዕ​ው​ቀ​ትና የእ​ው​ነት መን​ፈስ ያር​ፍ​በ​ታል። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን የመ​ፍ​ራት መን​ፈስ ይሞ​ላ​በ​ታል፤ በፍ​ርድ አያ​ዳ​ላም፤ በነ​ገ​ርም አይ​ከ​ራ​ከ​ርም፤ ነገር ግን ለድ​ሆች በጽ​ድቅ ይፈ​ር​ዳል፤ ለም​ድ​ርም የዋ​ሆች በቅ​ን​ነት ይበ​ይ​ናል፤ በአ​ፉም ቃል ምድ​ርን ይመ​ታል፤ በከ​ን​ፈ​ሩም እስ​ት​ን​ፋስ ኀጢ​አ​ተ​ኛ​ውን ያጠ​ፋ​ዋል። ወገ​ቡን በጽ​ድቅ ይታ​ጠ​ቃል፤ እው​ነ​ት​ንም በጎኑ ይጐ​ና​ጸ​ፋል። ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይሰ​ማ​ራል፤ ነብ​ርም ከፍ​የል ጠቦት ጋር ይተ​ኛል፤ ጥጃና በሬ የአ​ን​በሳ ደቦ​ልም በአ​ን​ድ​ነት ይሰ​ማ​ራሉ፤ ታና​ሽም ልጅ ይመ​ራ​ቸ​ዋል። ላምና ድብ አብ​ረው ይሰ​ማ​ራሉ፤ ግል​ገ​ሎ​ቻ​ቸ​ውም በአ​ን​ድ​ነት ያድ​ጋሉ፤ አን​በ​ሳም እንደ በሬ ገለባ ይበ​ላል። የሚ​ጠ​ባ​ውም ሕፃን በእ​ባብ ጕድ​ጓ​ድና በእ​ፉ​ኝት ቤት ላይ እጁን ይጭ​ናል። እነ​ር​ሱም አይ​ጐ​ዱ​ትም፤ በተ​ቀ​ደ​ሰው ተራ​ራዬ ሁሉ ላይ ማን​ንም አይ​ጐ​ዱም፤ አያ​ጠ​ፉ​ምም፤ ብዙ ውኃ ባሕ​ርን እን​ደ​ሚ​ሸ​ፍን ምድር እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን በማ​ወቅ ትሞ​ላ​ለ​ችና።

ኢሳይያስ 11:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከእሴይ ግንድ ቍጥቋጥ ይወጣል፤ ከሥሮቹም አንዱ ቅርንጫፍ ፍሬ ያፈራል። የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኀይል መንፈስ፣ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስ ይለዋል፤ ዐይኑ እንዳየ አይፈርድም፤ ጆሮውም እንደ ሰማ አይበይንም። ነገር ግን ለድኾች በጽድቅ ይፈርዳል፤ ለምድር ምስኪኖችም ፍትሕን ይበይናል፤ በአፉ በትር ምድርን ይመታል፤ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል። ጽድቅ የወገቡ መታጠቂያ፣ ታማኝነትም የጐኑ መቀነት ይሆናል። ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይኖራል፤ ነብርም ከፍየል ግልገል ጋር ይተኛል፤ ጥጃ፣ የአንበሳ ደቦልና የሠባ ከብት በአንድነት ይሰማራሉ፤ ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል። ላምና ድብ በአንድነት ይሰማራሉ፤ ልጆቻቸውም አብረው ይተኛሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። ጡት የሚጠባ ሕፃን በአደገኛ እባብ ጕድጓድ ላይ ይጫወታል፤ ጡት የጣለም ሕፃን እጁን በእፉኝት ጕድጓድ ይከትታል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ጕዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።

ኢሳይያስ 11:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል። የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል። ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፥ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም፥ ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፥ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፥ በአፉም በትር ምድርን ይመታል፥ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል። የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፥ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል። ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፥ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፥ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፥ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል። ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፥ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያርፋሉ፥ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጕድጓድ ላይ ይጫወታል፥ ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፥ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።

ኢሳይያስ 11:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ግንድ እንደሚያቈጠቊጥና ከስሩም ቅርንጫፍ እንደሚያበቅል እንዲሁም ከእሴይ (ከዳዊት ንጉሣዊ) ዘር አንድ ንጉሥ ይወጣል። የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ይኖራል፤ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኀይል መንፈስ፥ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስ ይለዋል፤ በሚያየው ብቻ አይፈርድም፤ ወይም በሚሰማው ብቻ አይበይንም። ነገር ግን በእውነት ለድኾች ይፈርዳል፤ ረዳት ለሌላቸውም ወገኖች ተከላካይ በመሆን መብታቸውን ያስከብራል፤ በበትር እንደሚመታ፥ መረን በተለቀቁት ላይ ይፈርዳል፤ በቃሉም ክፉዎችን ያጠፋል። ሕዝቡን የሚያስተዳድርበት የወገቡ መታጠቂያ እውነት፥ የጐኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል። ተኲላና በግ በአንድነት ይኖራሉ፤ ነብርም ከፍየል ግልገሎች ጋር አብሮ ይመሰጋል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል አብረው ይመገባሉ፤ ትንሽ ልጅም እየመራ ይጠብቃቸዋል። ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፤ ጥጆቻቸውና ግልገሎቻቸውም አብረው ይመሰጋሉ፤ አንበሶችም እንደ በሬ ገለባ ይበላሉ። ጡት የሚጠባው ሕፃን በእባብ ጒድጓድ አጠገብ ይጫወታል፤ ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኚት ቤት ላይ እጁን ያኖራል። በእግዚአብሔር ቅዱስ ተራራ ላይ ምንም ጒዳት አይደርስም፤ ባሕር በውሃ እንደሚሞላ ምድርም እግዚአብሔርን በሚያውቁና በሚያከብሩ ሰዎች ትሞላለች።

ኢሳይያስ 11:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከእሴይ ግንድ ቁጥቋጥ ይወጣል፤ ከሥሮቹም አንዱ ቅርንጫፍ ፍሬ ያፈራል። የጌታ መንፈስ፤ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፤ የምክርና የኃይል መንፈስ፤ የዕውቀትና ጌታን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። ጌታን በመፍራት ደስ ይለዋል፤ ዐይኑ እንዳየ አይፈርድም፤ ጆሮውም እንደሰማ አይበይንም። ነገር ግን ለድኾች በጽድቅ ይፈርዳል፤ ለምድር ምስኪኖችም ፍትሕን ይበይናል፤ በአፉ በትር ምድርን ይመታል፥ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል። ጽድቅ የወገቡ መታጠቂያ፤ ታማኝነትም የጐኑ መቀነት ይሆናል። ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይኖራል፤ ነብርም ከፍየል ግልገል ጋር ይተኛል፤ ጥጃ፤ የአንበሳ ደቦልና የሰባ ከብት በአንድነት ይሰማራሉ፤ ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል። ላምና ድብ በአንድነት ይሰማራሉ፤ ልጆቻቸውም አብረው ይተኛሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። ጡት የሚጠባ ሕፃን በአደገኛ እባብ ጉድጓድ ላይ ይጫወታል፤ ጡት የጣለም ሕፃን እጁን በእፉኝት ጉድጓድ ይከትታል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ጉዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፤ ምድር ሁሉ ጌታን በማወቅ ትሞላለችና።