የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 11

11
ሰላም የሰፈነበት መንግሥት
1ግንድ እንደሚያቈጠቊጥና ከስሩም ቅርንጫፍ እንደሚያበቅል እንዲሁም ከእሴይ (ከዳዊት ንጉሣዊ) ዘር አንድ ንጉሥ ይወጣል። #ራዕ. 5፥5፤ 22፥16።
2የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ይኖራል፤
የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥
የምክርና የኀይል መንፈስ፥
የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።
3እግዚአብሔርን በመፍራት ደስ ይለዋል፤
በሚያየው ብቻ አይፈርድም፤
ወይም በሚሰማው ብቻ አይበይንም።
4ነገር ግን በእውነት ለድኾች ይፈርዳል፤
ረዳት ለሌላቸውም ወገኖች ተከላካይ በመሆን መብታቸውን ያስከብራል፤
በበትር እንደሚመታ፥ መረን በተለቀቁት ላይ ይፈርዳል፤
በቃሉም ክፉዎችን ያጠፋል። #2ተሰ. 2፥8።
5ሕዝቡን የሚያስተዳድርበት የወገቡ መታጠቂያ እውነት፥
የጐኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል። #ኤፌ. 6፥14።
6ተኲላና በግ በአንድነት ይኖራሉ፤
ነብርም ከፍየል ግልገሎች ጋር አብሮ ይመሰጋል፤
ጥጃና የአንበሳ ደቦል አብረው ይመገባሉ፤
ትንሽ ልጅም እየመራ ይጠብቃቸዋል።
7ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፤
ጥጆቻቸውና ግልገሎቻቸውም አብረው ይመሰጋሉ፤
አንበሶችም እንደ በሬ ገለባ ይበላሉ።
8ጡት የሚጠባው ሕፃን በእባብ ጒድጓድ አጠገብ ይጫወታል፤
ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኚት ቤት ላይ እጁን ያኖራል።
9በእግዚአብሔር ቅዱስ ተራራ ላይ ምንም ጒዳት አይደርስም፤
ባሕር በውሃ እንደሚሞላ
ምድርም እግዚአብሔርን በሚያውቁና በሚያከብሩ ሰዎች ትሞላለች። #ኢሳ. 65፥25። #ዕን. 2፥14።
በሕይወት የተረፉት ስደተኞች መመለስ
10በዚያን ጊዜ የእሴይ (የዳዊት) ዘር ለሕዝቦች ምልክት ሆኖ ይቆማል፤ ሕዝቦች እርሱን ይፈልጉታል፤ መኖሪያውም የተከበረ ይሆናል። #ሮም 15፥12። 11በዚያን ጊዜ ጌታ እንደገና የኀይል ሥራ ይሠራል፤ ይኸውም በአሦር፥ በግብጽ፥ በጳጥሮስ አገሮች፥ በኢትዮጵያ፥ በዔላም፥ በባቢሎንና በሐማት እንዲሁም በባሕር ጠረፍ አገሮችና በደሴቶች ሁሉ የሚኖሩትን የቀሩት ወገኖቹን ወደ አገራቸው ይመልሳቸዋል። 12በዚያን ጊዜ ጌታ በመላው ዓለም ተበታትነው ይኖሩ የነበሩትን የእስራኤልንና የይሁዳን ሕዝብ ከአራቱ ማእዘን ሰብስቦ ያመጣቸው መሆኑን ለመንግሥታት ሁሉ የሚያሳውቅበትን አርማ ከፍ አድርጎ ያቆማል። 13ከዚያን በኋላ የእስራኤል መንግሥት በይሁዳ ላይ ያለውን ምቀኝነት ይተዋል፤ ይሁዳም በእስራኤል ላይ ያለውን ጠላትነትና ጥላቻ ያቆማል። 14ሁለቱም ተባብረው በምዕራብ በኩል በፍልስጥኤማውያን ላይ ይነሣሉ፤ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩ ሕዝቦችንም ሀብት ይዘርፋሉ፤ የኤዶምንና የሞአብን ሕዝብ ድል ይነሣሉ፤ የዐሞንም ሕዝብ ለእነርሱ ታዛዦች ይሆናሉ። 15እግዚአብሔር የግብጽን ባሕረ ልሳን ያደርቃል፤ ማንም ሰው በእግሩ መሻገር እንዲችል የኤፍራጥስን ወንዝ በኀይለኛ ነፋስ መትቶ ወደ ትናንሽ ሰባት ጅረቶች ይከፋፍለዋል። #ራዕ. 16፥12። 16እግዚአብሔር የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብጽ በወጡ ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ከጥፋት የተረፉት የእስራኤል ሕዝብ ከአሦር የሚወጡበትን መንገድ ያዘጋጅላቸዋል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ