የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 10

10
1ሕዝቤን የሚጨቊን ግፍ የሞላበት ሕግ ለምታወጡ ወዮላችሁ! 2የድኾች መብት እንዳይከበርና የተበደሉ ፍትሕ እንዳያገኙ የምታደርጉበት ዘዴ ይኸው ነው፤ በዚሁ ዘዴ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና አሳዳጊ የሌላቸውን የሙት ልጆች ንብረት ትነጥቃላችሁ። 3በዚህ ሁሉ የግፍ ሥራችሁ እግዚአብሔር እናንተን በሚቀጣበት ጊዜ ምን ታደርጉ ይሆን? በእናንተ ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ከሩቅ አገር በሚያመጣበት ጊዜስ ምን ይበጃችሁ ይሆን? ርዳታስ ለማግኘት የምትሄዱት ወደማን ነው? ሀብታችሁንስ የት ትሸሽጉታላችሁ? 4ከመማረክና ከመገደል እንዴት ታመልጣላችሁ? ይህም ሁሉ ሆኖ የእግዚአብሔር ቊጣ ገና አልበረደም፤ ስለዚህ እናንተን ለመቅጣት እጁ እንደ ተሰነዘረ ነው።
የአሦር ንጉሠ ነገሥት የእግዚአብሔር መሣሪያ መሆኑ
5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የቊጣዬ በትር፥ የተግሣጼ ጨንገር የሆንከው አሦር፥ ወዮልህ! #ኢሳ. 14፥24-27፤ ናሆም 1፥1—3፥19፤ ሶፎ. 2፥13-15። 6ሀብታቸውን ዘርፈውና መዝብረው ሕዝቡን እንደ መንገድ ላይ ጭቃ እንዲረግጡ በከሐዲውና ቊጣዬንም ባነሣሣው ሕዝብ ላይ አሦራውያንን አስነሥቼ እልካቸዋለሁ።”
7የእነርሱ ዕቅድ ግን ይህ አይደለም፤ ይህም ጉዳይ በሐሳባቸው ውስጥ የለም፤ የእነርሱ ዓላማ ግን ጥቂቶቹን ሳይሆን ብዙዎችን ሕዝቦች ለማጥፋት ነው። 8ስለዚህም ንጉሣቸው እንዲህ እያለ ይደነፋል፥ “የጦር አዛዦቼ ሁሉ ነገሥታት አይደሉምን? 9የካልኖን፥ የካርከሚሽን፥ የሐማትንና የአርፋድን ከተሞች ድል አድርጌአለሁ፤ ሰማርያንና ደማስቆንም በቊጥጥሬ ሥር አድርጌአለሁ። 10ከአሁን በፊትም ከኢየሩሳሌምና ከሰማርያ የበለጡ ጣዖቶች የሞሉባቸውን መንግሥታት አሸንፌአለሁ። 11በሰማርያና በጣዖቶችዋ ላይ እንዳደረግሁት በኢየሩሳሌምና እዚያ በሚሰግዱላቸው ምስሎች ላይ አላደርገውምን?”
12ነገር ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “በኢየሩሳሌምና በጽዮን ተራራ የማደርገውን ሁሉ ከፈጸምኩ በኋላ ስለ ትምክሕቱና ስለ ትዕቢቱ ሁሉ ብዛት የአሦርንም ንጉሠ ነገሥት ደግሞ እቀጣለሁ።” 13የአሦር ንጉሠ ነገሥት በመደንፋት ሲናገር እንዲህ ብሎአል፦ “ይህን ሁሉ ያደረግኹ እኔ ራሴ ነኝ፤ እኔ ብርቱ፥ ዐዋቂና ብልኅ ነኝ፤ በመንግሥታት መካከል የነበረውን ወሰን አፈራረስኩ፤ ያካበቱትንም ሀብት ሁሉ ወሰድኩ፤ በእነዚያም አገሮች የሚኖሩትን ሕዝብ ሁሉ በጀግንነቴ አዋረድኳቸው። 14የዓለም መንግሥታት ሁሉ በእኔ ፊት እንደ ወፍ ጎጆች ነበሩ፤ እንቊላል በቀላሉ እንደሚሰበሰብ ዐይነት ሀብታቸውን ሁሉ ሰብስቤ ወሰድኩ፤ ይህን ባደረግሁ ጊዜ የወፍ ላባ ያኽል እንኳ የተንቀሳቀሰ የለም፤ የወፍ ኩምቢ ያኽል እንኳ ድምፁን ያሰማ የለም።”
15መጥረቢያ እንጨት በሚቈርጥበት በባለቤቱ ላይ መነሣት ይችላልን? መጋዝስ በሚሰነጥቅበት ሰው ላይ መነሣት ይችላልን? እንዲሁም በትር በሚይዘው ሰው ላይ ኀይል አይኖረውም።
16ስለዚህ ጌታ የሠራዊት አምላክ በግዙፉ ሠራዊቱ ላይ የሚያመነምን በሽታ ይልክበታል፤ በሰውነቱም ውስጥ እንደ እሳት የሚያቃጥል ትኲሳት ይልክበታል። 17የእስራኤል ብርሃን እግዚአብሔር ራሱ እሳት ይሆንባቸዋል፤ የእስራኤልም ቅዱስ አምላክ ራሱ በአንዲት ቀን ኲርንችቱንና እሾኹን ሳያስቀር ሁሉን በልቶ እንደሚጨርስ የእሳት ነበልባል ይሆናል። 18ብርቱ ደዌ ሰውን አሰልስሎ እንደሚገድል፥ የተዋቡ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖቹና ለምለም የእርሻ ቦታዎቹ ይደመሰሳሉ። 19በደን ውስጥ የሚቀሩትም ዛፎች በቊጥር ያነሱ ከመሆናቸው የተነሣ ሕፃን ልጅ እንኳ ሊቈጥራቸው ይችላል።
የጥቂቶች መመለስ
20በዚያን ጊዜ ከጥፋት የተረፉት የእስራኤል ሕዝብ፥ ጥቃት ባደረሱባቸው በአሦራውያን ላይ አይተማመኑም፤ በዚህ ፈንታ በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ በእውነት ይተማመናሉ። 21ከእስራኤል ሕዝብ መካከል ከጥፋት የተረፉት ጥቂቶቹ ወደ ኀያል አምላካቸው በእውነት ይመለሳሉ። 22ምንም እንኳ የእስራኤል ሕዝብ ብዛት እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ቢሆንም ከእነርሱ መካከል የሚድኑት የተረፉት ብቻ ናቸው፤ ለሕዝቡ ጥፋት ተገቢ የሆነ እውነተኛ ፍርድ ተዘጋጅቶአል። 23አዎ! የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር በሀገሪቱ በሞላ ቊርጥ ውሳኔ የሰጠበትን የጥፋት ፍርድ ያመጣል። #ሮም 9፥27።
እግዚአብሔር አሦርን እንደሚቀጣ
24የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር በጽዮን ለሚኖሩ ሕዝቦቹ እንዲህ ይላል፦ “ምንም እንኳ ከዚያ በፊት ግብጻውያን ጨቊነው እንደ ገዙአችሁ እነርሱም የጨቈኑአችሁ ቢሆንም አሦራውያንን አትፍሩ። 25ከጥቂት ጊዜ በኋላ በእናንተ ላይ ያለኝ ቊጣ ይቆማል፤ ከዚያን በኋላ እነርሱን እደመስሳለሁ። 26እኔ የሠራዊት አምላክ በዖሬብ አለት አጠገብ በምድያማውያን ላይ እንዳደረግሁት አሦራውያንን የምቀጣበት ጅራፍ ባሕሩን በበትሬ መትቼ ግብጻውያንን እንደቀጣሁ አሦራውያንን እቀጣለሁ። በግብጽ ላይ በትሬን እንዳነሣሁ በኤፍራጥስ ወንዝ ላይም አነሣለሁ። 27በዚያንም ጊዜ እናንተን ከአሦራውያን የጭቈና አገዛዝ ነጻ አወጣችኋለሁ፤ ከዚያን በኋላ የአገዛዝ ቀንበራቸው ከውፍረታችሁ የተነሣ ይሰበራል እንጂ በእናንተ ጫንቃ ላይ እንደተጫነ አይቀርም።”
ወራሪዎች የጣሉት አደጋ
28የጠላት ሠራዊት ወደ ዓይ ከተማ ደረሰ፤ በሚግሮንም በኩል ሲያልፉ ጓዛቸውን በሚክማስ አኖሩ። 29መተላለፊያውን አልፈው ዐዳር በጌባዕ ሆነ በራማ ከተማ የሚኖሩ ሁሉ ደነገጡ፤ በንጉሥ ሳኦል ከተማ በጊብዓ የሚኖሩትም ሁሉ ሸሹ። 30የጋሊም ሕዝብ ሆይ! እሪ በሉ! የላይሻም ሕዝብ ሆይ! አድምጡ! የዐናቶትም ሰዎች መልስ ስጡ! 31የማድሜናህና የጌቢም ሕዝቦች ሕይወታቸውን ለማትረፍ በመሸሽ ላይ ናቸው። 32ዛሬ ጠላት በኖብ ከተማ የሚገኝ ሲሆን፥ የኢየሩሳሌም ከተማ በሆነችው በጽዮን ኰረብታ ላይ ለማስፈራራት ክንዱን እየነቀነቀ ነው።
33እነሆ የሠራዊት አምላክ ከዛፍ እንደ ተቈረጠ ቅርንጫፍ እየሰባበረ ያወርዳቸዋል፤ በእነርሱ መካከል ኩራተኛ የሆነውና እጅግ ከፍ ከፍ ብሎ የታበየው ይዋረዳል። 34በደን መካከል የሚገኝ ዛፍ በመጥረቢያ ተቈርጦ እንደሚወድቅ እነርሱንም እግዚአብሔር ይቈራርጣቸዋል፤ ምርጥ የሆኑ የሊባኖስ ዛፎችም ተቈርጠው እንደሚወድቁ እነርሱም በኀያሉ አምላክ ተቈርጠው ይወድቃሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ