ትንቢተ ኢሳይያስ 11
11
ሰላም የሰፈነበት መንግሥት
1ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከግንዱ ይወጣል። 2የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኀይል መንፈስ፥ የዕውቀትና የእውነት#ዕብ. “እግዚአብሔርን የመፍራት” ይላል። መንፈስ ያርፍበታል። 3እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ይሞላበታል፤ በፍርድ አያዳላም፤ በነገርም አይከራከርም፤ 4ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፤ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፤ በአፉም ቃል ምድርን ይመታል፤ በከንፈሩም እስትንፋስ ኀጢአተኛውን ያጠፋዋል። 5ወገቡን በጽድቅ ይታጠቃል፤ እውነትንም በጎኑ ይጐናጸፋል።
6ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይሰማራል፤ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና በሬ የአንበሳ ደቦልም በአንድነት ይሰማራሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል። 7ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፤ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያድጋሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። 8የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጕድጓድና በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል። 9እነርሱም አይጐዱትም፤ በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ማንንም አይጐዱም፤ አያጠፉምም፤ ብዙ ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።
የእስራኤል ከስደት መመለስ
10በዚያም ቀን የእሴይ ሥር ይቆማል፤ የተሾመውም የአሕዛብ አለቃ ይሆናል፤ አሕዛብም በእርሱ ተስፋ ያደርጋሉ፤#ዕብ. “እንዲህ ይሆናል፥ ለአሕዛብ ምልክት ሊሆን የቆመውን የእሴይን ሥር አሕዛብ ይፈልጉታል” ይላል። ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል።
11በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ከአሦርና ከግብፅ፥ ከባቢሎንና#ዕብ. “ከጳትሮስና” ይላል። ከኢትዮጵያ፥ ከኤላሜጤን፥ ከምሥራቅና ከምዕራብ#ዕብ. “ከሐማትም ከባሕርም ደሴቶች” ይላል። ለቀሩት ለሕዝቡ ቅሬታ ይቀና ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ገና እጁን ይገልጣል። 12ለአሕዛብም ምልክትን ያቆማል፤ ከእስራኤልም የቀሩትን ይሰበስባል፤ ከይሁዳም የተበተኑትን ከአራቱ የምድር ማዕዘኖች ያከማቻል። 13የኤፍሬምም ቅናት ይሻራል፤ የይሁዳም ጠላቶች ይጠፋሉ፤ ኤፍሬምም በይሁዳ አይቀናም፤ ይሁዳም ኤፍሬምን አያስጨንቅም። 14በባሕርም#“ባሕር” ማለት በምዕራብና በሰሜን መካከል ያለ አቅጣጫ ነው። በኩል በፍልስጥኤማውያን መርከቦች ላይ እየበረሩ ይወርዳሉ፤ የምሥራቅ ሰዎችንና ኤዶምያስን በአንድነት ይዘርፋሉ፤ በሞዓብ ላይ ቀድመው እጃቸውን ይዘረጋሉ፤ የአሞንም ልጆች ቀድመው ለእነርሱ ይታዘዛሉ። 15እግዚአብሔርም የግብፅን ባሕር ያደርቃል፤ በኀይለኛም ነፋስ እጁን በወንዙ ላይ ያነሣል፤ ሰባት ፈሳሾችንም ይመታል፤ ሰዎችም በጫማቸው እንዲሻገሩ ያደርጋቸዋል። 16ከግብፅም በወጣ ጊዜ ለእስራኤል እንደ ነበረ፥ በአሦር#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በግብፅ” ይላል። ለቀረው ለሕዝቡ ጎዳና ይሆናል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 11: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ