ትንቢተ ኢሳይያስ 10
10
1ክፉንም ጽሕፈት ለሚጽፉ ወዮላቸው! 2መበለቶች ቅሚያቸው እንዲሆኑ፥ የሙት ልጆችንም ብዝበዛቸው እንዲያደርጉ፥ የድሃውን ፍርድ ያጣምሙ ዘንድ፥ የችግረኛውንም ሕዝቤን ፍርድ ያጐድሉ ዘንድ የግፍን ትእዛዛት ለሚያዝዙ ወዮላቸው! 3በተጐበኛችሁበት ቀን፥ ምን ታደርጉ ይሆን? መከራ ከሩቅ ይመጣባችኋልና፥ ለረድኤትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ? 4በሐሣር እንዳትወድቁ፥ ክብራችሁን ወዴት ትተዉታላችሁ? በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፤ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
5ለቍጣዬ በትር ለሆኑ፥ ለመዓቴም ጨንገር በእጃቸው ላለ ለአሦራውያን ወዮላቸው! 6ቍጣዬን በኀጢአተኛ ሕዝብ ላይ እልካለሁ፤ ይማርኳቸውና ይበዘብዙአቸው ዘንድ፥ ከተሞችንም ይረግጡአቸውና እንደ ትቢያ ያደርጓቸው ዘንድ ሕዝቤን አዝዛለሁ። 7እርሱ በልቡ እንዲህ አይመስለውም፤ እንዲህም አያስብም፤ ነገር ግን ማጥፋት፥ ጥቂት ያይደሉትንም አሕዛብ መቍረጥ በልቡ አለ። 8“አንተ ብቻህን አለቃ ነህን?” ቢሉትም፥ የሔማትን መንደር ወሰድሁ ይላል። 9እንደ ሔማት አርፋድ፥ እንደ አርፋድ ሴፋሩሔም፥ እንደ ሴፋሩሔም ካሌና፥ እንደ ካሌናም ደማስቆ፥ እንደ ደማስቆም ሰማርያ አይደለችምን? 10ይሁዳንም እንዲሁ አደርጋታለሁ፤ በኢየሩሳሌምና በሰማርያ የሚያድን ጣዖት አለን? 11በሰማርያና በጣዖቶችዋም እንዳደረግሁ፥ እንዲሁ በኢየሩሳሌምና በጣዖቶችዋ አደርጋለሁ።
12ስለዚህ እንዲህ ይሆናል፤ ጌታ ሥራውን ሁሉ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ በፈጸመ ጊዜ የአሦርን ንጉሥ የኵሩ ልብን ፍሬ፥ የዐይኑንም ከፍታ ትምክሕት ይቀጣል። 13እርሱ እንዲህ ብሎአልና፥ “በኀይሌ አደርጋለሁ፤ በማስተዋል ጥበቤም የአሕዛብን ድንበሮች አርቃለሁ፤ ሀብታቸውንም#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ግእዝ “ኀይላቸውን” ይላል። እዘርፋለሁ፤ 14የሚቀመጡባቸውንም ከተሞች አናውጣለሁ። በእጄም ዓለምን ሁሉ እንደ ወፍ ቤት እሰበስባለሁ፤ እንደ ተተወ እንቍላልም እወስዳቸዋለሁ፤ ከእኔም የሚያመልጥ የለም፤ የሚቃወመኝም የለም።
15“በውኑ መጥረቢያ በሚቈርጥበት ሰው ላይ ይነሣልን? ወይስ መጋዝ በሚስበው ሰው ላይ ይጓደዳልን? ይህም ዘንግ በሚመቱበት ላይ እንደ መነሣት፥ በትርም ዕንጨት አይደለሁም እንደ ማለት ነው።” 16ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በክብርህ ላይ ውርደትን፥ በጌጥህ ላይም የሚነድና የሚያቃጥል እሳትን ይሰድዳል። 17የእስራኤልም ብርሃን እንደ እሳት ይሆናል፤ በሚነድድ እሳትም ይቀድሰዋል፤ ዛፉንም እንደ ሣር ያቃጥለዋል። 18ያንጊዜ ተራሮችና ኮረብቶች፥ ዛፎችም ይጠፋሉ። ነፍስና ሥጋንም ይበላል፤ የሚሸሽም ከሚነድድ የእሳት ነበልባል እንደሚሸሽ ይሆናል። 19የቀሩትም የዱር ዛፎች በቍጥር ጥቂት ይሆናሉ፤ ታናሽ ብላቴናም ይጽፋቸዋል።
የእስራኤል ቅሬቶች
20በዚያም ጊዜ እንዲህ ይሆናል፤ የእስራኤል ቅሬታ ከያዕቆብም ቤት የዳኑት ከእንግዲህ ወዲህ በአቈሰሉአቸው ላይ አይደገፉም፤ ነገር ግን በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ በእውነት ይደገፋሉ። 21የያዕቆብም ቅሬታ በኀያሉ እግዚአብሔር ይጸናሉ። 22የእስራኤልም ሕዝብ ቍጥር እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆን የቀሩት ይድናሉ። 23የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀና የተቈረጠ ነገርን በዓለም ሁሉ በእውነት ይፈጽማል።
24ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በጽዮን የምትኖር ሕዝቤ ሆይ፥ ከአሦር የተነሣ አትፍራ፤ በበትር ይመቱሃልና፥ የግብፅንም መንገድ ታይ ዘንድ መቅሠፍቴን አመጣብሃለሁና። 25ለጥቂት ጊዜ ቍጣዬ ይበርዳል፤ ነገር ግን መዓቴ በምክራቸው ላይ ይሆናል።” 26እግዚአብሔርም ምድያምን በመከራው ቦታ እንደ መታው ጅራፍን ያነሣበታል፤ ቍጣውም በባሕሩ መንገድና በግብፅ መንገድ በኩል ይሆናል። 27በዚያም ቀን ቀንበሩ ከጫንቃህ፥ ፍርሀቱም ከአንተ ላይ ይወርዳል፤ ቀንበሩም ከጫንቃህ ወርዶ ይሰበራል።
28ወደ አንጋይ ከተማ ይመጣል፤ በመጌዶን በኩል ያልፋል፤ በማክማስም ውስጥ ዕቃውን ያኖራል፤ 29በቆላ ያልፋል፤ ወደ አንጋይም በደረሰ ጊዜ ሬማትና የሳኦል ከተማ ገባዖን ይፈራሉ፤ 30የጋሊም ልጅ ትሸሻለች፤ ላይሳም ትሰማለች፤ አናቶትም ትሰማለች። 31መደቤናና በጌቤር የሚኖሩ ይደነግጣሉ። 32ዛሬ በእጁ እንዲኖሩ በመንገዱ ለምኑ፤ የጽዮን ልጅ ተራራንና የኢየሩሳሌምን ኮረብቶች አጽኑ።
33እነሆ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ክቡራንን በኀይል ያውካቸዋል፤ ታላላቆችንም በሐሣር ይቀጠቅጣቸዋል፤ ከፍ ያሉትም ይዋረዳሉ። 34ታላላቆችም በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ሊባኖስም ከረዣዥም ዛፎች ጋር ይወድቃል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 10: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ