ዕብራውያን 9:11-15
ዕብራውያን 9:11-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ክርስቶስ ግን ለምትመጣይቱ መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ የሰው እጅ ወደ አልሠራት፥ በዚህ ዓለም ወደ አልሆነችው፥ ከፊተኛዪቱ ወደምትበልጠውና ወደምትሻለው ድንኳን፥ የዘለዓለም መድኀኒትን ገንዘብ አድርጎ፥ በገዛ ደሙ አንድ ጊዜ ወደ መቅደስ ገባ እንጂ በላምና በፍየል ደም አይደለም። የላምና የፍየል ደም፥ በረከሱትም ላይ የሚረጭ የጊደር አመድ፥ የሚያነጻና የረከሱትንም ሥጋቸውን የሚቀድሳቸው ከሆነ፥ ነውር የሌለው ሆኖ፥ በዘለዓለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እናመልከው ዘንድ ሕሊናችንን ከሞት ሥራ እንዴት ይልቅ ያነጻ ይሆን? ስለዚህ ኢየሱስ ሞትን ተቀብሎ፥ በቀደመው ሥርዐት ስተው የነበሩትን ያድናቸው ዘንድ ወደ ዘለዓለም ርስቱም የጠራቸው ተስፋውን ያገኙ ዘንድ፥ ለአዲሲቱ ኪዳን መካከለኛ ሆነ።
ዕብራውያን 9:11-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ክርስቶስ አሁን ስላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ፣ በሰው እጅ ወዳልተሠራችው፣ ከዚህ ፍጥረት ወዳልሆነችው ታላቅና ፍጹም ድንኳን ገባ። የገባውም የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ። የውጭ አካላቸው ይነጻ ዘንድ በረከሱ ሰዎች ላይ የሚረጨው የፍየሎችና የኰርማዎች ደም እንዲሁም የፍየሎችና የጊደር ዐመድ የሚቀድሳቸው ከሆነ፣ በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም፣ ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን! ስለዚህም የተጠሩት፣ ተስፋ የተሰጠውን የዘላለም ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፤ በመጀመሪያው ኪዳን ሥር በነበሩበት ጊዜ ከሠሩት ኀጢአት ነጻ ለማውጣት ቤዛ ሆኖ ሞቷልና።
ዕብራውያን 9:11-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፥ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው።
ዕብራውያን 9:11-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ነገር ግን ክርስቶስ በመምጣት ላይ ላሉት መልካም ነገሮች የካህናት አለቃ ሆኖ ተገልጦአል፤ እርሱ የገባባት ድንኳን ትልቅና ፍጹም ናት፤ ይህች ድንኳን በሰው እጅ ያልተሠራችና ከዚህ ፍጥረት ያልሆነች ናት። እርሱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አንዴ በማያዳግም ሁኔታ የራሱን ደም ይዞ ገባ እንጂ የፍየሎችንና የወይፈኖችን ደም ይዞ አልገባም፤ በዚህም ዐይነት የዘለዓለም ቤዛን አስገኘልን። የፍየሎችና የወይፈኖች ደምና ለመሥዋዕት የተቃጠለች ጊደር ዐመድ በረከሱ ሰዎች ላይ ሲረጭ ከሥጋዊ ርኲሰት አንጽቶ የሚቀድሳቸው ከሆነ፥ በዘለዓለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር የሌለበት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናገለግል ኅሊናችንን ከሞተ ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን! እነዚያ የተጠሩት እግዚአብሔር በተስፋ የሰጠውን ዘለዓለማዊ ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ማእከላዊ አስማሚ ሆኖአል፤ ይህም የሆነው ሰዎችን በመጀመሪያው ቃል ኪዳን ሥር ሆነው ከሠሩት ኃጢአት ለማዳን እርሱ በመሞቱ ነው።
ዕብራውያን 9:11-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን ክርስቶስ እንደ ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ ስለሚሆነው መልካም ነገር፥ በምትበልጠውና በምትሻለው፥ በእጆችም ባልተሠራች፥ እርሷም ከፍጡራን ባልሆነች ድንኳን፥ የዘለዓምን ቤዛነት አግኝቶ፥ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ፥ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። የኮርማዎችና የፍየሎች ደም፥ በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ፥ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፥ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም እንዴት ልቆ፥ ሕያው እግዚአብሔርን ለማምለክ፥ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን! በዚህ ምክንያት የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞቱ ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘለዓምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው።