የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 9

9
የምድራዊው ቤተ መቅደስ አገልግሎት
1የመጀመሪያው ኪዳን የአምልኮ አገልግሎት ሥርዓትና ምድራዊ መቅደስ ነበረው፤ 2ሁለት ክፍሎች ያሉአት ድንኳን ተዘጋጅታ ነበር። መቅረዙና ጠረጴዛው፥ የመሥዋዕቱም ኅብስት የነበረባት መጀመሪያይቱ ክፍል “ቅድስት” ትባል ነበር። 3ከሁለተኛው መጋረጃ በስተኋላ የምትገኘው ውስጠኛዋ ክፍል “ቅድስተ ቅዱሳን” ትባል ነበር። #ዘፀ. 26፥31-33። 4በዚህችኛዋ ክፍል ውስጥ የወርቅ ማዕጠንትና በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ታቦት ነበሩባት፤ ከዚህችም የኪዳን ታቦት ውስጥ መና ያለባት የወርቅ መሶብ፥ ለምልማ የነበረችው የአሮን በትር፥ ዐሥሩ ትእዛዞች የተጻፉባት ጽላት ነበሩ። #ዘፀ. 30፥1-6፤ 25፥10-16፤ 16፥33፤ ዘኍ. 17፥8-10፤ ዘፀ. 25፥16፤ ዘዳ. 10፥3-5። 5በታቦትዋም ላይ ያለውን የኃጢአት ማስተስረያ መክደኛ በክንፋቸው የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ ነገር ግን ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሁን በዝርዝር መናገር አንችልም። #ዘፀ. 25፥18-22።
6ሁሉ ነገር በዚህ ሁኔታ ከተዘጋጀ በኋላ ካህናት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ወደ ድንኳኒቱ መጀመሪያ ክፍል ዘወትር ይገባሉ። #ዘኍ. 18፥2-6። 7ወደ ሁለተኛዋ ውስጠኛ ክፍል የሚገባው ግን የካህናቱ አለቃ ብቻ ነው፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ቀን ብቻ ነው፤ እርሱም ስለ ራሱ ኃጢአትና ሕዝቡ ባለማወቅ ስላደረገው ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም። #ዘሌ. 16፥2-34። 8የመጀመሪያይቱ ድንኳን እስካለች ድረስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ ገና ያልተገለጠ መሆኑን መንፈስ ቅዱስ በዚህ ዐይነት ያሳያል። 9ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፤ በዚህ ዐይነት የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የአቅራቢውን ሰው ኅሊና ፈጽመው ሊያነጹት አይችሉም፤ 10እነዚህ ነገሮች የመታደስ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ በሥራ ላይ የዋሉ አፍአዊ ሥርዓቶች ናቸው፤ እነርሱ ስለ መብልና ስለ መጠጥ፥ ስለ ልዩ ልዩ የመንጻት ሥርዓቶችም ብቻ የተደረጉ ናቸው።
11ነገር ግን ክርስቶስ በመምጣት ላይ ላሉት መልካም ነገሮች የካህናት አለቃ ሆኖ ተገልጦአል፤ እርሱ የገባባት ድንኳን ትልቅና ፍጹም ናት፤ ይህች ድንኳን በሰው እጅ ያልተሠራችና ከዚህ ፍጥረት ያልሆነች ናት። #9፥11 በመምጣት ላይ ላሉት አንዳንድ ቅጂዎች “ወደፊት ለሚመጡት” ይላሉ። 12እርሱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አንዴ በማያዳግም ሁኔታ የራሱን ደም ይዞ ገባ እንጂ የፍየሎችንና የወይፈኖችን ደም ይዞ አልገባም፤ በዚህም ዐይነት የዘለዓለም ቤዛን አስገኘልን። 13የፍየሎችና የወይፈኖች ደምና ለመሥዋዕት የተቃጠለች ጊደር ዐመድ በረከሱ ሰዎች ላይ ሲረጭ ከሥጋዊ ርኲሰት አንጽቶ የሚቀድሳቸው ከሆነ፥ #ዘሌ. 16፥15-16፤ ዘኍ. 19፥9፤17-19። 14በዘለዓለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር የሌለበት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናገለግል ኅሊናችንን ከሞተ ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!
15እነዚያ የተጠሩት እግዚአብሔር በተስፋ የሰጠውን ዘለዓለማዊ ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ማእከላዊ አስማሚ ሆኖአል፤ ይህም የሆነው ሰዎችን በመጀመሪያው ቃል ኪዳን ሥር ሆነው ከሠሩት ኃጢአት ለማዳን እርሱ በመሞቱ ነው።
16ኑዛዜ ሲኖር የተናዛዡን ሞት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ 17የኑዛዜ ቃል የሚጸናው ተናዛዡ ከሞተ በኋላ ነው፤ ተናዛዡ በሕይወት ካለ ግን የኑዛዜው ቃል ዋጋ አይኖረውም። 18በዚህ ምክንያት የመጀመሪያው ኪዳን እንኳ ያለ ደም የጸና አይደለም። 19በመጀመሪያ ሙሴ የሕጉን ትእዛዞች ለሕዝቡ ሁሉ ነገረ፤ ከዚህ በኋላ የወይፈኖችንና የፍየሎችን ደም ከውሃ ጋር አድርጎ የሕጉን መጽሐፍና ሕዝቡን ሁሉ በሂሶጵና በቀይ የበግ ጠጒር ረጨ፤ 20የረጨውም “እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የቃል ኪዳን ደም ይህ ነው” ብሎ ነው። #ዘፀ. 24፥6-8። 21እንዲሁም በድንኳኒቱና በመገልገያ ዕቃ ሁሉ ላይ ደምን ረጨ። #ዘሌ. 8፥15። 22በእርግጥም በሙሴ ሕግ መሠረት ከጥቂት ነገር በቀር ሁሉም ነገር በደም ይነጻል፤ ደም ካልፈሰሰም የኃጢአት ስርየት አይገኝም። #ዘሌ. 17፥11።
የክርስቶስ መሥዋዕትነት ኃጢአትን የሚያስወግድ መሆኑ
23እንግዲህ እነዚህ የሰማያዊ ነገሮች ምሳሌ የሆኑት ሁሉ በዚህ ዐይነት ሥርዓት መንጻት ያስፈልጋቸው ነበር፤ ከሰማይ የሆኑት ነገሮች ግን ከዚህ በሚበልጥ መሥዋዕት መንጻት ያስፈልጋቸዋል። 24ክርስቶስ የእውነተኛይቱ “መቅደስ” ምሳሌ ወደ ሆነችውና በሰው እጅ ወደተሠራችው ቅድስተ ቅዱሳን አልገባም፤ እርሱ አሁን ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት ወደ ሰማይ ገባ። 25የአይሁድ የካህናት አለቃ የራሱ ያልሆነውን ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባ ነበር፤ ክርስቶስ ግን ራሱን ብዙ ጊዜ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ አልገባም። 26እንዲህማ ቢሆን ኖሮ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ መቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዘመናት መጨረሻ ኃጢአትን ለማስወገድ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ አንዴ በማያዳግም ሁኔታ ተገልጦአል። 27ለሰው አንድ ጊዜ መሞት ተመድቦለታል፤ ከሞት በኋላም ፍርድ አለበት። 28እንዲሁም ክርስቶስ የብዙዎችን ኃጢአት ለማስወገድ አንድ ጊዜ ተሠውቶአል፤ ደግሞም ኃጢአትን ለመሸከም ሳይሆን እርሱን የሚጠባበቁትን ለማዳን ሁለተኛ ጊዜ ይገለጣል። #ኢሳ. 53፥12።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ