ዕብራውያን 11:20-31
ዕብራውያን 11:20-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ያገኙት ዘንድ ስለ አላቸው ነገር ይስሐቅ ያዕቆብንና ኤሳውን በእምነት ባረካቸው። ያዕቆብም በሚሞትበት ጊዜ የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን በእምነት ባረካቸው፤ በበትሩ ጫፍም ሰገደ። ዮሴፍም በሚሞትበት ጊዜ፥ ስለ እስራኤል ልጆች ከግብፅ መውጣት በእምነት ዐሰበ፤ ዐጽሙንም ትተው እንዳይወጡ አዘዘ። ሙሴ በተወለደ ጊዜ በእምነት ሦስት ወር በአባቱ ቤት ሸሸጉት፤ ሕፃኑ መልካም እንደ ሆነ አይተውታልና፤ የንጉሥንም ትእዛዝ አልፈሩም። ሙሴም በአደገ ጊዜ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እንቢ አለ፤ ለጊዜው በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ። የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት ከግብፅ ሀብት ሁሉ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንደሚሆን ዐውቆአልና፥ ዋጋውንም ተመልክቶአልና። የንጉሡንም ቍጣ ሳይፈራ፥ የግብፅን ሀገር በእምነት ተወ፤ ከሚያየው ይልቅ የማይታየውን ሊፈራ ወዶአልና። ቸነፈር በኵራቸውን እንዳያጠፋባቸው በእምነት ፋሲካን አደረገ፤ ደሙንም ረጨ። በደረቅ ምድር እንደ መሄድ የኤርትራን ባሕር በእምነት ተሻገሩአት፤ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ሰጠሙ። ሰባት ቀን ከዞሩአት በኋላ የኢያሪኮ ቅጽር በእምነት ወደቀ። ዘማ ረአብም በእምነት ከከሓዲዎች ጋር አልጠፋችም፤ ጕበኞችን በሰላም ተቀብላ ሰውራቸዋለችና።
ዕብራውያን 11:20-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይሥሐቅ ወደ ፊት የሚሆነውን ዐስቦ ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ እያንዳንዳቸውን የዮሴፍን ልጆች በእምነት ባረካቸው፤ በበትሩም ጫፍ ዘንበል ብሎ ሰገደ። ዮሴፍ ሊሞት በተቃረበ ጊዜ፣ ስለ እስራኤል ሕዝብ ከግብጽ መውጣት በእምነት ተናገረ፤ ስለ ዐፅሙም ትእዛዝ ሰጠ። ሙሴ ከተወለደ በኋላ፣ ወላጆቹ መልከ መልካም ሕፃን መሆኑን ስላዩ በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት፤ የንጉሡንም ዐዋጅ አልፈሩም። ሙሴ ካደገ በኋላ፣ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እንቢ አለ። ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋራ መከራን መቀበል መረጠ። ከግብጽ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ፤ ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቷልና። የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ ግብጽን ለቅቆ በእምነት ወጣ፤ የማይታየውንም እንዳየው አድርጎ በመቍጠር በሐሳቡ ጸና። በኵሮች የሆኑትን የሚገድለው ቀሣፊ የእስራኤልን በኵር ልጆች እንዳይገድል ፋሲካን በእምነት አደረገ፤ ደምንም ረጨ። ሕዝቡ በደረቅ መሬት እንደሚኬድ ቀይ ባሕርን በእምነት ተሻገሩ፤ ግብጻውያን ግን እንደዚሁ ለማድረግ ሲሞክሩ ሰጠሙ። ሕዝቡ የኢያሪኮን ግንብ ሰባት ቀን ከዞሩት በኋላ፣ በእምነት ወደቀ። ዝሙት ዐዳሪዋ ረዓብ፣ ሰላዮቹን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙት ጋራ ያልጠፋችው በእምነት ነው።
ዕብራውያን 11:20-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይስሐቅ ሊመጣ ስላለው ነገር ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸው ባረካቸው፥ በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ። ዮሴፍ ወደ ሞት ቀርቦ ሳለ በእምነት ስለ እስራኤል ልጆች መውጣት አስታወሰ፥ ስለ አጥንቱም አዘዛቸው። ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም። ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና። አጥፊው የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ። በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ በኤርትራ ባሕር በእምነት ተሻገሩ፥ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ተዋጡ። የኢያሪኮ ቅጥር ሰባት ቀን ከዞሩበት በኋላ በእምነት ወደቀ። ጋለሞታይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙ ጋር በእምነት አልጠፋችም።
ዕብራውያን 11:20-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይስሐቅ ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር በማሰብ ያዕቆብንና ዔሳውን የባረካቸው በእምነት ነው። ያዕቆብ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን የባረካቸውና በብትሩ ጫፍ ተደግፎ የሰገደው በእምነት ነው። ዮሴፍም የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ እስራኤላውያን ከግብጽ እንደሚወጡ የተናገረው ስለ ዐፅሙም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ትእዛዝ የሰጠው በእምነት ነው። የሙሴ ወላጆች ሙሴ በተወለደ ጊዜ መልከ መልካም መሆኑን ስላዩ የንጉሡን ትእዛዝ ሳይፈሩ ሦስት ወር የሸሸጉት በእምነት ነው። ሙሴም ካደገ በኋላ “የፈርዖን የልጅ ልጅ” ተብሎ መጠራትን ያልፈቀደው በእምነት ነው፤ ስለዚህም እርሱ በኃጢአት ከሚገኘው ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ። ወደፊትም የሚቀበለውን ዋጋ ስለ ተመለከተ ከግብጽ ሀብት ይልቅ ስለ መሲሑ መዋረድ የበለጠ መሆኑን አሰበ። የንጉሡንም ቊጣ ሳይፈራ ከግብጽ የወጣው በእምነት ነው፤ በዐይን የማይታየውንም አምላክ እንዳየው ያኽል ሆኖ በዓላማው ጸና። የበኲር ልጆችን ለመግደል የታዘዘው መልአክ የእስራኤላውያንን የበኲር ልጆች እንዳይገድል በማለት ሙሴ የፋሲካና የደም መርጨትን ሥርዓት ያደረገው በእምነት ነው። እስራኤላውያን በደረቅ ምድር እንደሚሻገሩ ሆነው ቀይ ባሕርን የተሻገሩት በእምነት ነው፤ ግብጻውያን ግን እንዲሁ ለማድረግ በሞከሩ ጊዜ ሁሉም ሰጠሙ። እስራኤላውያን በኢያሪኮ ቅጽሮች ዙሪያ ሰባት ቀን ከዞሩ በኋላ ቅጽሮቹን ያፈረሱት በእምነት ነው። አመንዝራይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙት ጋር ከመሞት የተረፈችው በእምነት ነው።
ዕብራውያን 11:20-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይስሐቅ ስለ መጪው ነገር ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን ባረካቸው፤ በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ። ዮሴፍ ወደ ሞት በቀረበ ጊዜ፥ በእምነት ስለ እስራኤል ልጆች መውጣት አስታወሰ፤ ስለ አጥንቱም አዘዛቸው። ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት፤ የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም። ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ ተብሎ ላለመጠራት በእምነት እምቢ አለ፤ በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ፥ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ። ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቶአልና፥ ከግብጽ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ። የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና፥ የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብጽን አገር ትቶ የሄደው በእምነት ነበር። የበኩር ልጆችን የሚያጠፋው እንዳይነካቸው ፋሲካን የጠበቀውና ደምን መርጨትን ያደረገው በእምነት ነበር። በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ የኤርትራን ባሕር በእምነት ተሻገሩ፤ የግብጽ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ሰመጡ። የኢያሪኮ ግንብ ሰባት ቀን ከዞሩት በኋላ በእምነት ፈረሰ። ጋለሞታይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው በእምነቷ ምክንያት ከማይታዘዙ ጋር አልጠፋችም።