ወደ ዕብራውያን 11:20-31

ወደ ዕብራውያን 11:20-31 መቅካእኤ

ይስሐቅ ስለ መጪው ነገር ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን ባረካቸው፤ በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ። ዮሴፍ ወደ ሞት በቀረበ ጊዜ፥ በእምነት ስለ እስራኤል ልጆች መውጣት አስታወሰ፤ ስለ አጥንቱም አዘዛቸው። ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት፤ የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም። ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ ተብሎ ላለመጠራት በእምነት እምቢ አለ፤ በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ፥ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ። ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቶአልና፥ ከግብጽ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ። የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና፥ የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብጽን አገር ትቶ የሄደው በእምነት ነበር። የበኩር ልጆችን የሚያጠፋው እንዳይነካቸው ፋሲካን የጠበቀውና ደምን መርጨትን ያደረገው በእምነት ነበር። በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ የኤርትራን ባሕር በእምነት ተሻገሩ፤ የግብጽ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ሰመጡ። የኢያሪኮ ግንብ ሰባት ቀን ከዞሩት በኋላ በእምነት ፈረሰ። ጋለሞታይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው በእምነቷ ምክንያት ከማይታዘዙ ጋር አልጠፋችም።