ዕብራውያን 11:20-31

ዕብራውያን 11:20-31 NASV

ይሥሐቅ ወደ ፊት የሚሆነውን ዐስቦ ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ እያንዳንዳቸውን የዮሴፍን ልጆች በእምነት ባረካቸው፤ በበትሩም ጫፍ ዘንበል ብሎ ሰገደ። ዮሴፍ ሊሞት በተቃረበ ጊዜ፣ ስለ እስራኤል ሕዝብ ከግብጽ መውጣት በእምነት ተናገረ፤ ስለ ዐፅሙም ትእዛዝ ሰጠ። ሙሴ ከተወለደ በኋላ፣ ወላጆቹ መልከ መልካም ሕፃን መሆኑን ስላዩ በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት፤ የንጉሡንም ዐዋጅ አልፈሩም። ሙሴ ካደገ በኋላ፣ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እንቢ አለ። ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋራ መከራን መቀበል መረጠ። ከግብጽ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ፤ ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቷልና። የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ ግብጽን ለቅቆ በእምነት ወጣ፤ የማይታየውንም እንዳየው አድርጎ በመቍጠር በሐሳቡ ጸና። በኵሮች የሆኑትን የሚገድለው ቀሣፊ የእስራኤልን በኵር ልጆች እንዳይገድል ፋሲካን በእምነት አደረገ፤ ደምንም ረጨ። ሕዝቡ በደረቅ መሬት እንደሚኬድ ቀይ ባሕርን በእምነት ተሻገሩ፤ ግብጻውያን ግን እንደዚሁ ለማድረግ ሲሞክሩ ሰጠሙ። ሕዝቡ የኢያሪኮን ግንብ ሰባት ቀን ከዞሩት በኋላ፣ በእምነት ወደቀ። ዝሙት ዐዳሪዋ ረዓብ፣ ሰላዮቹን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙት ጋራ ያልጠፋችው በእምነት ነው።