ዘፍጥረት 37:1-12
ዘፍጥረት 37:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ያዕቆብ አባቱ በኖረበት በከነዓን ምድር ተቀመጠ። የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ ይህ ነው። ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረ ጊዜ፣ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዘለፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋራ የአባቱን በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር። እርሱም ስለ ወንድሞቹ ድርጊት ለአባቱ መጥፎ ወሬ ይዞለት መጣ። እስራኤል ዮሴፍን በስተርጅናው ስለ ወለደው፣ ከልጆቹ ሁሉ አብልጦ ይወድደው ነበር፤ በኅብረ ቀለማት ያጌጠ እጀ ጠባብም አደረገለት። ወንድሞቹም፣ አባታቸው ከእነርሱ አብልጦ የሚወድደው መሆኑን ሲያዩ፣ ዮሴፍን ጠሉት፤ በቅን አንደበትም ሊያናግሩት አልቻሉም። ዮሴፍም ሕልም ዐለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ ሲነግራቸው የባሰ ጠሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ ስሙኝ እኛ ሁላችን በዕርሻ ውስጥ ነዶ እናስር ነበር፤ የእኔ ነዶ በድንገት ተነሥታ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶዎች ዙሪያዋን ከብበው ለእኔ ነዶ ሰገዱላት።” ወንድሞቹም፣ “ለካስ በላያችን ለመንገሥ ታስባለህና! ለመሆኑ አንተ እኛን ልትገዛ!” አሉት፤ ስለ ሕልሙና ስለ ተናገረው ቃል ከፊት ይልቅ ጠሉት። እንደ ገናም ሌላ ሕልም ዐለመ፤ ለወንድሞቹም፣ “እነሆ፤ ሌላ ሕልም ዐለምሁ፤ ፀሓይና ጨረቃ፣ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ” ብሎ ነገራቸው። ሕልሙን ለአባቱና ለወንድሞቹ በነገራቸው ጊዜ፣ አባቱ “ይህ ያየኸው ሕልም ምንድን ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም በፊትህ ወደ ምድር ተጐንብሰን በርግጥ ልንሰግድልህ ነው?” ሲል ገሠጸው። ወንድሞቹ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ነገሩን በልቡ ያዘው። ከዚህም በኋላ የዮሴፍ ወንድሞች የአባታቸውን በጎችና ፍየሎች ለማሰማራት ወደ ሴኬም አካባቢ ሄዱ፤
ዘፍጥረት 37:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ያዕቆብም አባቱ በስደት በኖረበት ሀገር በከነዓን ምድር ተቀመጠ። የያዕቆብም ትውልድ እንዲህ ነው። ዮሴፍ ዐሥራ ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜ ከወንድሞቹ ጋር የአባቱን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ እርሱም ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዘለፋ ልጆች ጋር ሳለ ብላቴና ነበረ፤ ዮሴፍም የክፋታቸውን ወሬ ወደ አባታቸው ወደ እስራኤል ያመጣ ነበር። ያዕቆብም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወድደው ነበር፤ እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበርና። በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት። ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንደሚወድደው በአዩ ጊዜ ጠሉት፤ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም። ዮሴፍም ሕልምን አለመ፤ ለወንድሞቹም ነገራቸው። እርሱም አላቸው፥ “እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፤ እነሆ፥ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበርና፥ እነሆ፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶዎች በዙርያ ከብበው እነሆ፥ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።” ወንድሞቹም፥ “በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ገዢ ትሆነን ይሆን?” አሉት። እንደገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ የበለጠ ጠሉት። ደግሞም ሌላ ሕልምን አየ፤ ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ እንዲህም አለ፥ “እነሆ፥ ደግሞ ሌላ ሕልም አለምሁ፤ ሕልሙም እንዲህ ነው፦ ፀሐይና ጨረቃ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ይሰግዱልኝ ነበር።” አባቱም ገሠጸው፤ እንዲህም አለው፥ “ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድን ነው? በውኑ እኔና እናትህ፥ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?” ወንድሞቹም ቀኑበት፤ አባቱ ግን ይህን ነገር በልቡ ይጠብቀው ነበር። ወንድሞቹም በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ።
ዘፍጥረት 37:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ያዕቆብም አባቱ በስደት በኖረበት አገር በከነዓን ምድር ተቀመጠ። የያዕቆብም ትውልድ ይህ ነው። ዮሴፍ የአሥራ ሰባት ዓመት ልጅ በሆን ጊዜ ከወንድሞቹ ጋር በጎችን ይጠብቅ ነበር፤ እርሱም ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዘለፋ ልጆች ጋር ሳለ ብላቴና ነበረ፤ ዮሴፍም የክራታቸውን ወሬ ወደ አባታቸው አመጣ። እስራኤልም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወደው ነበር እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበር በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት። ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንዲወደው ባዩ ጊዜ ጠሉት፥ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም። ዮሴፍም ሕልምን አለመ ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ እነርሱም እንደ ገና በብዙ ጠሉት እርሱ አላቸው፦ እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፤ እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበርና እነሆም የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከብበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ። ወንድሞቹም፦ በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ልትገዛ ይሆን? አሉት። እንደ ገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ ይልቁን ጠሉት። ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እንዲህም አለ፦ እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ እነሆ ፀሐይን ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብርም ሲሰግዱልኝ አየሁ። ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው አባቱም ገሠጸው እንዲህም አለው፦ ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድር ነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንስገድልህ ይሆን? ወንድሞቹም ቀኑበት አባቱ ግን ነገሩን ይጠብቅው ነበር። ወንድሞቹ በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ።
ዘፍጥረት 37:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ያዕቆብ ተቀማጭነቱን አባቱ በኖረበት በከነዓን ምድር አደረገ። የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤ ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረበት ጊዜ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዚልፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር፤ ወንድሞቹ የሚፈጽሙትንም በደል እያመጣ ለአባቱ ይነግር ነበር። በስተርጅና የወለደው ስለ ሆነ ያዕቆብ ዮሴፍን ከሌሎች ልጆች ሁሉ አብልጦ ይወደው ነበር፤ ስለዚህም ጌጠኛ የሆነ እጀ ጠባብ ሰፋለት። ወንድሞቹም አባታቸው ከእነርሱ ይልቅ ዮሴፍን እንደሚወድ ባዩ ጊዜ በመቅናት ጠሉት፤ መልካም ቃልም ሊናገሩት አልወደዱም። አንድ ሌሊት ዮሴፍ ሕልም አየ፤ ሕልሙን ለወንድሞቹ በነገራቸውም ጊዜ ከቀድሞው ይበልጥ ጠሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ፤ እኛ ሁላችን በእርሻ ውስጥ የስንዴ ነዶ እናስር ነበር፤ የእኔ ነዶ ተነሣና ቀጥ ብሎ ቆመ፤ የእናንተ ነዶዎች ዙሪያውን ተሰብስበው ለእኔ ነዶ ሰገዱለት።” ወንድሞቹም “ታዲያ በእኛ ላይ ንጉሥ ሆነህ ልትገዛን ታስባለህን?” ብለው ጠየቁት። ስላየው ሕልምና ስለ ተናገረው ቃል ከበፊቱ ይበልጥ ጠሉት። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ሌላ ሕልም አይቶ ወንድሞቹን “እነሆ፥ ሌላ ሕልም አየሁ፤ በሕልሜም ፀሐይ፥ ጨረቃና ዐሥራ አንድ ከዋክብት ሰገዱልኝ” አላቸው። ይህንኑ ለወንድሞቹ የነገራቸውን ሕልም ለአባቱም በነገረው ጊዜ፥ አባቱ “ይህ ምን ዐይነት ሕልም ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም የምንሰግድልህ ይመስልሃልን?” በማለት ገሠጸው። የዮሴፍ ወንድሞች እጅግ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ይህን ነገር በልቡ እያሰላሰለ ይጠብቀው ነበር። አንድ ቀን የዮሴፍ ወንድሞች የአባታቸውን መንጋዎች ይዘው ወደ ሴኬም ተሰማሩ፤
ዘፍጥረት 37:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ያዕቆብም አባቱ በስደት በኖረበት አገር በከነዓን ምድር ተቀመጠ።። የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤ ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረበት ጊዜ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዚልፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር፤ የእነርሱንም ክፋት ነገር ዮሴፍ ወደ አባታቸው አመጣ። እስራኤልም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወደው ነበር፥ እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበርና፥ በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት። ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንደሚወደው ባዩ ጊዜ ጠሉት፥ በሰላም ሊያናግሩትም አልቻሉም። ዮሴፍም ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እነርሱም እንደገና አብዝተው ጠሉት። እርሱም አላቸው፦ “እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፥ እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበር፥ እነሆም፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፥ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከብበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።” ወንድሞቹም፦ “በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ልትገዛ ይሆን?” አሉት። እንደገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ የበለጠ ጠሉት። ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም፦ “እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፥ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ።” ሲል ነገራቸው። ለአባቱና ለወንድሞቹም በነገራቸው ጊዜ፥ “ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?” በማለት አባቱ ገሠጸው። ወንድሞቹም ቀኑበት፥ አባቱ ግን ነገሩን ጠብቆ አኖረው። ወንድሞቹ በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ።