ኦሪት ዘፍጥረት 37
37
1ያዕቆብም አባቱ በስደት በኖረበት አገር በከነዓን ምድር ተቀመጠ።።
ዮሴፍና ወንድሞቹ
2የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤ ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረበት ጊዜ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዚልፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር፤ የእነርሱንም ክፋት ነገር ዮሴፍ ወደ አባታቸው አመጣ። 3እስራኤልም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወደው ነበር፥ እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበርና፥ በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት። 4ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንደሚወደው ባዩ ጊዜ ጠሉት፥ በሰላም ሊያናግሩትም አልቻሉም።
5ዮሴፍም ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እነርሱም እንደገና አብዝተው ጠሉት። 6እርሱም አላቸው፦ “እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፥ 7እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበር፥ እነሆም፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፥ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከብበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።” 8ወንድሞቹም፦ “በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ልትገዛ ይሆን?” አሉት። እንደገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ የበለጠ ጠሉት። 9ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም፦ “እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፥ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ።” ሲል ነገራቸው። 10ለአባቱና ለወንድሞቹም በነገራቸው ጊዜ፥ “ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?” በማለት አባቱ ገሠጸው። 11#የሐዋ. 7፥9።ወንድሞቹም ቀኑበት፥ አባቱ ግን ነገሩን ጠብቆ አኖረው።
የዮሴፍ በወንድሞቹ መሸጥ
12ወንድሞቹ በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ። 13እስራኤልም ዮሴፍን፦ “ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን እየጠበቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እንድልክህ ና” አለው። እርሱም “እነሆኝ” አለው። 14እርሱም፦ “ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ” አለው። በዚህ ዓይነት ከኬብሮን ሸለቆ ላከው፥ ወደ ሴኬምም መጣ። 15እነሆም በየሜዳው ሲባዝን አንድ ሰው አገኘው፤ ሰውዮውም፦ “ምን ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። 16እርሱም “ወንድሞቼን እየፈለግሁ ነው፥ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደሆነ እባክህ ንገረኝ” አለ። 17ሰውዮውም፦ “ከዚህ ተነሥተዋል፥ ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ሰምቼአቸዋለሁ” አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ፥ በዶታይንም አገኛቸው።
18እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩት፥ ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። 19እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦ “ያ ሕልም አላሚ ይኸው መጣ። 20ኑ፥ እንግደለውና በአንዱ ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው፦ ክፉ አውሬም በላው እንላለን፥ የሕልሞቹን መጨረሻ እናያለን።” 21ሮቤልም ይህን ሲሰማ፥ “ሕይወቱን አናጥፋ” በማለት ከእጃቸው አዳነው። 22“ደም አታፍስሱ፥ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጉድጓድ ጣሉት፥ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት” አላቸው። እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። 23እንዲህም ሆነ፥ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱን ቀሚሱን ገፈፉት፥ 24ወስደውም ወደ ጉድጓድ ጣሉት፥ ጉድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ።
25ምግብ ሊበሉ ተቀመጡ፥ ዓይናቸውንም አንሥተው ሲያዩ፥ እነሆ የእስማኤላውያን ነጋዴዎች ወደ ግብጽ ለመውረድ ከገለዓድ ይመጣሉ፥ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን፥ ከርቤም ተጭነው ነበር። 26ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድነው? 27ኑ፥ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፥ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና።” ወንድሞቹም የእርሱን ነገር ሰሙት። 28#ጥበ. 10፥13፤ የሐዋ. 7፥9።የምድያም ነጋዶችም አለፉ፥ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጉድጓድ አወጡት፥ ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሃያ ብር ሸጡት፥ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወሰዱት።
29ሮቤል ወደ ጉድጓዱ በተመለሰ ጊዜ፥ እነሆ ዮሴፍ በጉድጓድ የለም፥ ልብሱንም ቀደደ። 30ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፦ “ብላቴናው የለም፤ እኔስ ወዴት ልሂደው?” አለ። 31የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ፥ የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት። 32ብዙ ኅብር ያለበትንም ልብሱን ወደ አባታቸው ወስደው “እነሆ፥ ይህን አገኘን የልጅህ ልብስ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ እይ” አሉት። 33እርሱም ለይቶ ስላወቀው፦ “የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍ በእርግጥ ተበጫጭቋል” አለ። 34ያዕቆብ ልብሱንም ቀደደ፥ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። 35ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፥ መጽናናትን እንቢ አለ፥ እንዲህም አለ፦ “ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ።” አባቱም እንደዚህ ስለ እርሱ አለቀሰ። 36እነዚያ የምድያም ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብጽ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጶጥፋራ ሸጡት።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 37: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ