ያዕቆብም አባቱ በስደት በኖረበት አገር በከነዓን ምድር ተቀመጠ።። የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤ ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረበት ጊዜ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዚልፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር፤ የእነርሱንም ክፋት ነገር ዮሴፍ ወደ አባታቸው አመጣ። እስራኤልም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወደው ነበር፥ እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበርና፥ በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት። ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንደሚወደው ባዩ ጊዜ ጠሉት፥ በሰላም ሊያናግሩትም አልቻሉም። ዮሴፍም ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እነርሱም እንደገና አብዝተው ጠሉት። እርሱም አላቸው፦ “እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፥ እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበር፥ እነሆም፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፥ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከብበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።” ወንድሞቹም፦ “በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ልትገዛ ይሆን?” አሉት። እንደገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ የበለጠ ጠሉት። ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም፦ “እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፥ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ።” ሲል ነገራቸው። ለአባቱና ለወንድሞቹም በነገራቸው ጊዜ፥ “ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?” በማለት አባቱ ገሠጸው። ወንድሞቹም ቀኑበት፥ አባቱ ግን ነገሩን ጠብቆ አኖረው። ወንድሞቹ በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ።
ኦሪት ዘፍጥረት 37 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 37:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos