ዘፍጥረት 25:1-34

ዘፍጥረት 25:1-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አብ​ር​ሃ​ምም ደግሞ ስምዋ ኬጡራ የተ​ባ​ለች ሚስት አገባ። እር​ስ​ዋም ዘን​በ​ሪን፥ ዮቃ​ጤ​ንን፥ ሜዳ​ንን፥ ዮብ​ቅን፥ ምድ​ያ​ም​ንና ሴሂን ወለ​ደ​ች​ለት። ዮቃ​ጤ​ንም ሶቤ​ቅን፥ ቲማ​ን​ንና ድዳ​ንን ወለደ። የድ​ዳ​ንም ልጆች ራጉ​ኤል፥ ንበ​ከዝ፥ እስ​ራ​ኦ​ምና ሎአም ናቸው። የም​ድ​ያ​ምም ልጆች ጌፌር፥ ዔፋር፥ ሄኖኅ፥ አቢ​ሮ​ንና ቲያ​ሮስ ናቸው። እነ​ዚ​ህም ሁሉ የኬ​ጡራ ልጆች ናቸው። አብ​ር​ሃ​ምም በሕ​ይ​ወቱ ሳለ ገን​ዘ​ቡን ሁሉ ለልጁ ለይ​ስ​ሐቅ ሰጠው፤ አብ​ር​ሃ​ምም ለቁ​ባ​ቶቹ ልጆች ሀብ​ትን ሰጣ​ቸው፤ እር​ሱም ገና በሕ​ይ​ወቱ ሳለ ከልጁ ከይ​ስ​ሐቅ ለይቶ ወደ ምሥ​ራቅ ሀገር ሰደ​ዳ​ቸው። አብ​ር​ሃ​ምም የኖ​ረ​በት የዕ​ድ​ሜው ዓመ​ታት እነ​ዚህ ናቸው፤ መቶ ሰባ አም​ስት ዓመት ኖረ። አብ​ር​ሃ​ምም መል​ካም ሽም​ግ​ል​ናን ሸም​ግሎ፥ ዘመ​ኑ​ንም ፈጽሞ ሞተ፤ ወደ ወገ​ኖ​ቹም ተጨ​መረ። ልጆቹ ይስ​ሐ​ቅና ይስ​ማ​ኤ​ልም በመ​ምሬ ፊት ለፊት ባለው በኬ​ጢ​ያ​ዊው በሰ​ዓር ልጅ በኤ​ፍ​ሮን እርሻ ላይ ባለ ድርብ ክፍል በሆ​ነው ዋሻ ውስጥ ቀበ​ሩት። ይህም አብ​ር​ሃም ከኬጢ ልጆች የገ​ዛው እርሻ ነው፤ አብ​ር​ሃ​ም​ንና ሚስ​ቱን ሣራን በዚያ ቀበ​ሩ​አ​ቸው። እን​ዲ​ህም ሆነ፥ አብ​ር​ሃ​ምም ከሞተ በኋላ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጁን ይስ​ሐ​ቅን ባረ​ከው፤ ይስ​ሐ​ቅም ዐዘ​ቅተ ራእይ ተብሎ በሚ​ጠ​ራው ምንጭ አጠ​ገብ ኖረ። የሣራ ባሪያ ግብ​ፃ​ዊቱ አጋር ለአ​ብ​ር​ሃም የወ​ለ​ደ​ች​ለት የአ​ብ​ር​ሃም ልጅ የይ​ስ​ማ​ኤል ትው​ልድ ይህ ነው፤ የይ​ስ​ማ​ኤ​ልም የል​ጆቹ ስም በየ​ስ​ማ​ቸ​ውና በየ​ት​ው​ል​ዳ​ቸው እን​ዲህ ነው። የይ​ስ​ማ​ኤል የበ​ኵር ልጁ ናቡ​አት፥ ቄዳር፥ ነብ​ዳ​ኤል፥ መብ​ሳን፥ ማሴሜ፥ ዱማ፥ ማሤን፥ ኩዳን፥ ቴማን፥ ኤያ​ጤር፥ ናፌስ፥ ቄድን። የይ​ስ​ማ​ኤል ልጆች እነ​ዚህ ናቸው፤ ስማ​ቸ​ውም በየ​መ​ን​ደ​ራ​ቸ​ውና በየ​ሰ​ፈ​ራ​ቸው ይህ ነው፤ በየ​ወ​ገ​ና​ቸ​ውም ዐሥራ ሁለት አለ​ቆች ናቸው። እር​ሱም ከኤ​ው​ላጥ አን​ሥቶ በግ​ብፅ ፊት ለፊት እስ​ከ​ም​ት​ገኝ እስከ ሴይር ባለው ሀገር ኖረ፤ ወደ አሦ​ር​ዮ​ንም ደረሰ፤ እን​ዲ​ህም ከወ​ን​ድ​ሞቹ ሁሉ ፊት ተቀ​መጠ። ይስ​ማ​ኤ​ልም የኖ​ረ​በት የዕ​ድ​ሜው ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው ፤ ሸም​ግሎ ሞተ፤ ወደ ወገ​ኖ​ቹም ተጨ​መረ። የአ​ብ​ር​ሃም ልጅ የይ​ስ​ሐቅ ትው​ል​ድም ይህ ነው፤ አብ​ር​ሃም ይስ​ሐ​ቅን ወለደ፥ ይስ​ሐ​ቅም ሚስት ትሆ​ነው ዘንድ የሶ​ር​ያ​ዊ​ውን የላ​ባን እኅት፥ የሶ​ር​ያ​ዊ​ውን የባ​ቱ​ኤ​ልን ልጅ ርብ​ቃን ከሁ​ለቱ ከሶ​ርያ ወን​ዞች መካ​ከል በወ​ሰ​ዳት ጊዜ አርባ ዓመት ሆኖት ነበር። ይስ​ሐ​ቅም ስለ ሚስቱ ርብቃ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለመነ፤ መካን ነበ​ረ​ችና፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሰማው፤ ሚስቱ ርብ​ቃም ፀነ​ሰች። ልጆ​ች​ዋም በሆ​ድዋ ውስጥ ይን​ቀ​ሳ​ቀሱ ነበር ፤ እር​ስ​ዋም፥ “እን​ዲህ እሆን ዘንድ ካለኝ ይህ ለእኔ ምኔ ነው?” አለች። ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ትለ​ምን ዘንድ ሄደች። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም አላት፥ “ሁለት ሕዝ​ቦች በማ​ኅ​ፀ​ንሽ አሉ፤ ሁለ​ቱም ሕዝብ ከሆ​ድሽ ይወ​ለ​ዳሉ፤ ሕዝ​ብም ከሕ​ዝብ ይበ​ረ​ታል፤ ታላ​ቁም ለታ​ናሹ ይገ​ዛል።” የም​ት​ወ​ል​ድ​በ​ትም ወራት ተፈ​ጸመ፤ በማ​ኅ​ፀ​ን​ዋም መንታ ነበሩ። የበ​ኵር ልጅ​ዋም ወጣ፤ እንደ ጽጌ​ረ​ዳም ቀይ ነበረ፤ ሁለ​ን​ተ​ና​ውም ጠጕ​ራም ነበር፤ ስሙ​ንም ዔሳው ብላ ጠራ​ችው። ከዚ​ያም በኋላ ወን​ድሙ ወጣ፤ በእ​ጁም የዔ​ሳ​ውን ተረ​ከዝ ይዞ ነበር፤ ስሙ​ንም ያዕ​ቆብ ብላ ጠራ​ችው። ርብቃ ዔሳ​ው​ንና ያዕ​ቆ​ብን በወ​ለ​ደ​ቻ​ቸው ጊዜ ይስ​ሐቅ ስድሳ ዓመት ሆኖት ነበር። ብላ​ቴ​ኖ​ቹም አደጉ፤ ጐለ​መ​ሱም፤ ዔሳ​ውም አደን የሚ​ያ​ውቅ የበ​ረሃ ሰው ሆነ፤ ያዕ​ቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፤ በቤ​ትም ይቀ​መጥ ነበር። ይስ​ሐ​ቅም ዔሳ​ውን ይወድ ነበር፤ እርሱ ከአ​ደ​ነው ይበላ ነበ​ርና። ርብቃ ግን ያዕ​ቆ​ብን ትወድ ነበ​ረች። ለያ​ዕ​ቆ​ብም የም​ስር ንፍሮ ቀቀ​ለ​ች​ለት፤ ዔሳ​ውም ደክሞ ከበ​ረሃ ገባ፤ ዔሳ​ውም ያዕ​ቆ​ብን፥ “ከም​ስር ንፍ​ሮህ አብ​ላኝ፤ እኔ እጅግ ደክ​ሜ​አ​ለ​ሁና” አለው፤ ስለ​ዚ​ህም ስሙ ኤዶም ተባለ። ያዕ​ቆ​ብም ዔሳ​ውን፥ “ዛሬ ብኵ​ር​ና​ህን ስጠኝ” አለው። ዔሳ​ውም፥ “እነሆ፥ እኔ ልሞት ነኝ፤ ይህች ብኵ​ርና ለምኔ ናት?” አለ። ያዕ​ቆ​ብም፥ “ብኵ​ር​ና​ህን ትሰ​ጠኝ ዘንድ እስኪ ዛሬ ማል​ልኝ” አለው። ዔሳ​ውም ማለ​ለት፤ ብኵ​ር​ና​ው​ንም ለያ​ዕ​ቆብ ሸጠ። ያዕ​ቆ​ብም ለዔ​ሳው እን​ጀ​ራና የም​ስር ንፍሮ ሰጠው፤ በላ፥ ጠጣ፥ ተነ​ሥ​ቶም ሄደ፤ ዔሳ​ውም ብኵ​ር​ና​ውን አቃ​ለ​ላት።

ዘፍጥረት 25:1-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አብርሃም ኬጡራ የተባለች ሌላ ሚስት አገባ። እርሷም፦ ዘምራንን፣ ዮቅሳንን፣ ሜዳንን፣ ምድያምን፣ የስቦቅንና ስዌሕን ወለደችለት። ዮቅሳንም ሳባንና ድዳንን ወለደ፤ የድዳንም ልጆች፦ አሦራውያን፣ ለጡሳውያንና ለኡማውያን ናቸው። የምድያም ልጆች፦ ጌፌር፣ ዔፌር፣ ሄኖኅ፣ አቢዳዕና ኤልዳዓ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው። አብርሃም ያለውን ሀብት ሁሉ ለይሥሐቅ አወረሰው፤ ለቁባቶቹ ልጆች ግን በሕይወት እያለ ስጦታ አደረገላቸው፤ ከልጁ ከይሥሐቅም ርቀው እንዲኖሩ ወደ ምሥራቅ ምድር ሰደዳቸው። አብርሃም በጠቅላላው መቶ ሰባ ዐምስት ዓመት ኖረ። ከዚያም ዐረፈ፤ ዕድሜ ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። ልጆቹ ይሥሐቅና እስማኤል በመምሬ አጠገብ በምትገኝ በኬጢያዊው በሰዓር ልጅ በኤፍሮን ዕርሻ በመክፈላ ዋሻ ቀበሩት፤ ይህም የዕርሻ ቦታ አብርሃም ከኬጢያውያን የገዛው ነበር፤ ከሚስቱ ከሣራ አጠገብ በዚያ ተቀበረ። አብርሃም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ይሥሐቅን ባረከው፤ በዚህ ጊዜ ይሥሐቅ በብኤርላሃይሮኢ አቅራቢያ ይኖር ነበር። ግብጻዊቷ የሣራ አገልጋይ አጋር፣ ለአብርሃም የወለደችለት የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው። የእስማኤል ልጆች ስም እንደ ዕድሜያቸው ቅደም ተከተል እንዲህ ነው፦ የእስማኤል በኵር ልጅ ነባዮት፣ ቄዳር፣ ነብዳኤል፣ መብሳም፣ ማስማዕ፣ ዱማ፣ ማሣ፣ ኩዳን፣ ቴማን፣ ኢጡር፣ ናፌስና ቄድማ። እነዚህ የእስማኤል ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም በኖሩባቸውና በሰፈሩባቸው ቦታዎች የዐሥራ ሁለት ነገድ አለቆች ስሞች ናቸው። እስማኤል በጠቅላላው መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። ዘሮቹም መኖሪያቸውን ከግብጽ ድንበር አጠገብ፣ ወደ አሦር በሚወስደው መንገድ፣ በኤውላጥና በሱር መካከል አደረጉ፤ ከወንድሞቻቸውም ሁሉ ጋራ በጠላትነት ኖሩ። የአብርሃም ልጅ የይሥሐቅ ትውልድ ይህ ነው። አብርሃም ይሥሐቅን ወለደ፤ ይሥሐቅ ርብቃን ሲያገባ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበር፤ ርብቃ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ የሚኖረው የሶርያዊው የባቱኤል ልጅ፣ የሶርያዊውም የላባ እኅት ነበረች። ይሥሐቅ፣ ርብቃ መካን ስለ ነበረች ስለ እርሷ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰማ፤ ርብቃም ፀነሰች። ልጆቹም በማሕፀኗ ውስጥ እርስ በርሳቸው ይጋፉ ጀመር፤ እርሷም “ለምን እንዲህ ይሆንብኛል?” ብላ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሄደች። እግዚአብሔርም እንዲህ አላት፤ “ሁለት ወገኖች በማሕፀንሽ አሉ፤ ሁለትም ሕዝቦች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤ አንደኛው ከሌላው ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል” አላት። የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስም፣ እነሆ፤ በማሕፀኗ መንታ ወንዶች ልጆች ነበሩ። በመጀመሪያ የተወለደው መልኩ ቀይ፣ ሰውነቱም በሙሉ ጠጕር የለበሰ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ዔሳው ተባለ። ከዚያም ወንድሙ ተወለደ፤ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ወጣ፤ ከዚህም የተነሣ ስሙ ያዕቆብ ተባለ። ርብቃ ልጆቿን ስትወልድ፣ ይሥሐቅ የስድሳ ዓመት ሰው ነበር። ልጆቹም ዐደጉ፤ ዔሳው ጐበዝ ዐዳኝ፣ የበረሓም ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት፣ ከድንኳኑ የማይወጣ ሰው ነበር። ይሥሐቅ ከዐደን የመጣ ሥጋ ደስ ይለው ስለ ነበር፣ ዔሳውን ይወድደው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድደው ነበር። አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ሳለ ዔሳው እጅግ ተርቦ ከዱር መጣ። ዔሳውም ያዕቆብን፣ “ቶሎ በል፤ በጣም ርቦኛልና ከዚህ ቀይ ወጥ አብላኝ” አለው። ስለዚህም ስሙ ኤዶም ተባለ። ያዕቆብም፣ “በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ” አለው። ዔሳውም፣ “እነሆ፤ ልሞት ደርሻለሁ፤ ታዲያ ብኵርናው ምን ያደርግልኛል!” አለ። ያዕቆብም ዔሳውን፣ “እንግዲያማ፣ አስቀድመህ ማልልኝ” አለው፤ ስለዚህም ማለለት፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠለት። ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ እርሱም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ። ዔሳው ብኵርናውን እንዲህ አድርጎ አቃለላት።

ዘፍጥረት 25:1-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አብርሃምም ደግሞ ስምዋ ኬጡራ የተባላች ሚስት አገባ። እርስዋም ዘምራንን ዩቅሳንን ሜዳንን ምድያምን የስቦቅን ስዌሕን ወለደችለት። ዩቅሳንም ሳባንና ድዳንን ወለደ። የድዳንም ልጆች አሦርያውያን ለጡሳውያን ለኡማውያን ናቸው፥ የምድይምም ስጆች ጌፌር ዔፌት ሄኖኅ እቢዳዕ ኤልዳዓ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው። አብርሃምም የነበረውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጠው፤ የአብርሃም ለነበሩ ለቁብቶቹ ልጆች አብርሃም ስጦታን ሰጣቸው እርሱም ገና በሕይወቱ ሳለ ከልጁ ከይስሕቅ ለይቶ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደ ምሥራቅ አገር ሰደዳቸው። አብርሃምም የኖረበት የዕድሜው ዓመታት እነዚህ ናቸው መቶ ሰባ አምስት ዓመት ኖረ። አብርሃናም ነፍሱን ሰጠ በመልካም ሽምግልናም ሞተ ሸመገለ፥ ብዙ ዘመንም ጠገበ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ። ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤልም በመምሬ ፊት ለፊት ባለው በኬጢያዊ በሰዓርልጅ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ ቀበሩት። አብርሃምም ከኬጢ ልጆች የገዛው እርሻ ይህ ነው አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ። አብርሃምም ከሞተ በኍላ እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን ባረከው ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ በሚጠራው ምንጭ አጠገብ ኖረ። የሣራ ባሪያ ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችው የአብርሃም ልጅ የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው፤ የእስማኤልም የልጆቹ ስም በየስማቸውን በየትውልዳቸው እንዲህ ነው፤ የእስማኤል የበኵር ልጁ፥ ነባዮት፥ ቄዳር፥ ነብዳኤል፥ መብሳም፥ ማስማዕ፥ ዱማ፥ ማሣ፥ ኩዳን፥ ቴማን፥ ኢጡር፥ ናፊስ፥ ቄድማ። የእስማኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ስማቸውም በየመንደራቸውና በየሰደራቸው ይኸው ነው በየወገናቸውም አሥራ ሁለት አለቆች ናቸው። እስማኤልም የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው፤ ነፍሱን ሰጠ ሞትንም፤ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ። መኖሪያቸውም ከኤውላጥ አንሥቶ በግብፅ ፊት ለፊት እስከምትገኝ እስከሱር ድረስ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ ላይ ነበረ፤ እንዲህም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ተቀመጠ። የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድም ይህ ነው አብርሃም ይስሐቅም አርባ ዓመት ሲሆነውም ርብቃን አገባ። እርስዋም በሁለት ወንዞች መካከል ያለ የሶርያዊው የባቱኤል ልጅና የሶርይዊው የላባ እኅት ናት። ይስሐቅም ስለሚስቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ መካን ነበረችና፤ እግዚአብሔርም ተለመነው፥ ርብቃም ሚስቱ ፀነሰች። ልጆችም በሆድዋ ውስጥ ይገፋፋ ነበር፤ እርስዋም፦ እንዲህ ከሆነ ይህ ለእኔም ምኔ ነው? አለች። ከእግዚአብሔርም ትጠይቅ ዘንድ ሄደች። እግዚአብሔርም አላት፦ ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል። ትወልድ ዘንድ ዘመንዋ በተፈጸመ ጊዜም እነሆ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ። በፊትም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንትናውም ጠጕር ለብሶ ነበር፤ ስሙም ዔሳው ተባለ። ከዚይም በኍላ ወንድሙ ወጣ በእጁም፥ የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስሙም ያዕቆብ ተባለ። እርስዋ ልጆችን በወለደቻቸው ጊዜ ይስሐቅ ስድሳ ዓመት ሆኖት ነበር። ብላቴኖቹም አደጉ፤ ዔሳውም አደን የሚያውቅ የበረሃ ሰው ሆነ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በድንኳንም ይቀመጥ ነበር። ይስሐቅም ዔሳውን ይወድ ነበረ ካደነው ይበላ ነበርና፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበረች። ያዕቆብም ወጥ ሠራ ዔሳውም ደክሞ ከበረሃ ገባ፤ ዔሳውም ያዕቆብን፦ ከዚህ ከቀዩ ወጥ አብላኝ እኔ እጅግ ደክሜአለሁና አለው ስለዚህ ስሙ ኤዶም ተባለ። ያዕቆብም፦ በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ አለው። ዔሳውም፦ እነሆ እኔ ልሞት ነኝ ይህች ብኵርና ለምኔ ናት? አለ። ያዕቆብም፦ እስኪ በመጀመሪያ ማልልኝ አለው። ማለለትም ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠ። ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራን የምስር ወጥ ሰጠው በላ ጠጣ ተነሥቶም ሄደ፤ እንዲሁም ዔሳው ብኵርናውን አቃለላት።

ዘፍጥረት 25:1-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አብርሃም ቀጡራ የምትባል ሌላ ሚስት አገባ፤ እርስዋም ዚምራንን፥ ዮቅሻንን፥ መዳንን፥ ምድያምን፥ ዩሽባቅንና ሹሐን ወለደችለት። ዮቅሻንም ሳባንና ደዳንን ወለደ፤ የደዳንም ዘሮች አሹራውያን፥ ሌጡሻውያንና ሌኡማውያን ናቸው። የምድያምም ልጆች ዔፋ፥ ዔፈር፥ ሐኖክ፥ አቢዳዕና ኤልዳዓ ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የቀጡራ ዘሮች ናቸው። አብርሃም ያለውን ሀብት ሁሉ ለይስሐቅ አወረሰው፤ ከሌሎች ሴቶች ለተወለዱትም ልጆች ገና በሕይወት ሳለ ስጦታ ሰጣቸው፤ ከዚህ በኋላ እነዚህ ሌሎች ልጆች ከይስሐቅ ርቀው ወደ ምሥራቅ አገር እንዲሄዱ አደረጋቸው። የአብርሃም ዕድሜ በአጠቃላይ መቶ ሰባ አምስት ዓመት ነበር፤ በዚህም ዐይነት አብርሃም በቂ ዕድሜ አግኝቶ ካረጀ በኋላ ሞተ፤ ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤል ማክፌላ በተባለ ዋሻ ቀበሩት፤ ይህም ዋሻ ከመምሬ በስተምሥራቅ በሒታዊው በጾሐር ልጅ በዔፍሮን እርሻ ውስጥ የሚገኘው ነው፤ እርሱም አብርሃም ከሒታውያን ላይ የገዛው የመቃብር ቦታ ነው፤ በዚህ ዐይነት አብርሃም ሚስቱ ሣራ በተቀበረችበት ዋሻ ተቀበረ። አብርሃም ከሞተ በኋላ ልጁን ይስሐቅን እግዚአብሔር ባረከው፤ ይስሐቅም “ብኤርላሐይ ሮኢ ወይም የሚያየኝ ሕያው አምላክ” ተብሎ በሚጠራው ኲሬ አጠገብ ይኖር ነበር። የሣራ አገልጋይ ግብጻዊትዋ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል፥ ከዚህ በታች በዕድሜአቸው ቅደም ተከተል ተራ የተዘረዘሩትን ልጆች ወለደ፤ እነርሱም፦ ነባዮት፥ ቄዳር፥ አድብኤል፥ ሚብሣም፥ ሚሽማዕ፥ ዱማ፥ ማሣ፥ ሐዳድ፥ ቴማ፥ ይጡር፥ ናፊሽ እና ቄድማ ናቸው። እነዚህ የእስማኤል ልጆች ለዐሥራ ሁለት ነገዶች ቅድመ አያቶች ነበሩ፤ ስማቸውም በኖሩባቸው ከተሞችና ስፍራዎች ሲጠራ ይኖራል። እስማኤል መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ሲሆነው ሞተ፤ የእስማኤል ዘሮች ከግብጽ በስተምሥራቅ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ በሐዊላና በሹር መካከል ይኖሩ ነበር፤ የኖሩትም ከሌሎቹ የአብርሃም ዘሮች ጋር በጥላቻ ተራርቀው ነበር። የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ታሪክ ይህ ነው፤ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ። ይስሐቅ የባቱኤልን ልጅ ርብቃን ሲያገባ አርባ ዓመት ሆኖት ነበር፤ የርብቃ አባት ባቱኤልና ወንድምዋ ላባ በመስጴጦምያ የሚኖሩ ሶርያውያን ነበሩ፤ ርብቃ መኻን ስለ ነበረች ይስሐቅ ስለ እርስዋ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ስለ ሰማ ርብቃ ፀነሰች፤ የተፀነሱትም መንትያዎች ስለ ነበሩ እርስ በርሳቸው በማሕፀንዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርስዋም “ይህን ዐይነት ነገር ለምን ደረሰብኝ?” በማለት ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ ተነሣሣች። እግዚአብሔርም፥ “በማሕፀንሽ ያሉት ሁለት ሕዝቦች ናቸው፤ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ሁለት ወገኖች ትወልጃለሽ፤ አንዱም ከሌላው የበረታ ይሆናል፤ ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል” አላት። የመውለጃዋም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደች። የመጀመሪያው ልጅ መልኩ ቀይ፥ ሰውነቱ ጠጒራም ነበር፤ ስለዚህ ዔሳው ተባለ። ሁለተኛው ልጅ ሲወለድ የዔሳውን ተረከዝ ይዞ በመውጣቱ ያዕቆብ ተባለ፤ ልጆቹ በተወለዱ ጊዜ ይስሐቅ ሥልሳ ዓመት ሆኖት ነበር። ሁለቱም ልጆች አደጉ፤ ዔሳው በዱር መዋል የሚወድ ብልኅ አዳኝ ሆነ፤ ያዕቆብ ግን በቤት መዋል የሚወድ ጭምት ሰው ነበር። ዔሳው እያደነ ሥጋ ያበላው ስለ ነበረ ይስሐቅ ዔሳውን ይወድ ነበር። ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ያዕቆብ ቀይ የምስር ወጥ በመሥራት ላይ እንዳለ ዔሳው ከአደን መጣ፤ በጣም እርቦት ነበር፤ ስለዚህም ያዕቆብን “ከዚህ ከቀይ ወጥ ስጠኝ” አለው። ኤዶም የተባለውም በዚህ ምክንያት ነበር። ያዕቆብም “መጀመሪያ ብኲርናህን ሽጥልኝ” አለው። ዔሳውም “እኔ በራብ መሞቴ ነው፤ ታዲያ ብኲርና ምን ያደርግልኛል?” አለው። ያዕቆብም “እንግዲያውስ ብኲርናህን እንደምትሸጥልኝ መጀመሪያ ማልልኝ” አለው። ስለዚህ ዔሳው ምሎ ብኲርናውን ለያዕቆብ ሸጠ። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ የምስሩን ወጥ በእንጀራ አድርጎ ሰጠው፤ ዔሳውም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ፤ በዚህ ዐይነት ዔሳው ብኲርናውን በመናቅ አቃለላት።

ዘፍጥረት 25:1-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አብርሃም ኬጡራ የምትባል ሌላ ሚስት አገባ። እርሷም ዚምራንን፥ ዮቅሻንን፥ ሜዳንን፥ ምድያምን፥ የሽቦቅን፥ እና ሹሐን ወለደችለት። ዮቅሻንም ሳባንና ድዳንን ወለደ። የድዳንም ልጆች አሹራውያን፥ ለጡሻውያንና፥ ለኡማውያን ናቸው። የምድያምም ልጆች ዔፋ፥ ዔፈር፥ ሐኖክ፥ አቢዳዕና ኤልዳዓ ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው። አብርሃምም የነበረውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጠው፥ ነገር ግን የአብርሃም ለነበሩትም ለቁባቶቹ ልጆች አብርሃም ስጦታ ሰጣቸው፥ እርሱም ገና በሕይወቱ ሳለ ከልጁ ከይስሐቅ ለይቶ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደ ምሥራቅ አገር ሰደዳቸው። አብርሃምም በሕይወት የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሰባ አምስት ዓመታት ናቸው። በመጨረሻዋ እስትንፋሱ አብርሃም ነፍሱን ሰጠ፥ በመልካምም ሽምግልና ሞተ፥ ሸምግሎ፥ ብዙ ዘመንም ጠገበ፥ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤል፥ ከመምሬ በስተ ምሥራቅ በሒታዊው በጾሐር ልጅ በዔፍሮን እርሻ ውስጥ፥ ማክፌላ በተባለ ዋሻ ቀበሩት። የእርሻው ቦታ አብርሃም ከሒታውያን ላይ የገዛው ነው፤ ከዚያም አብርሃም ከሚስቱ ሣራ ጋር ተቀበረ። ከአብርሃም ሞት በኋላም እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን ባረከው፤ ይስሐቅም ብኤር-ላሃይ-ሮኢ ተብሎ በሚጠራው ምንጭ አጠገብ ኖረ። የሣራ አገልጋይ ግብጻዊትዋ አጋር ለአብርሃም የወለደችው የአብርሃም ልጅ የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው፤ በትውልዳቸው ቅደም ተከተል የተዘረዘሩት የእስማኤል የልጆቹ ስም እንዲህ ነው፥ የእስማኤል የበኩር ልጁ ነባዮት፥ እና ቄዳር፥ አድብኤል፥ ሚብሣም፥ ሚሽማዕ፥ ዱማ፥ ማሣ፥ ሐዳድ፥ ቴማ፥ ይጡር፥ ናፊሽ እና ቄድማ ናቸው። የእስማኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ስማቸውም በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው ይኸው ነው፥ በየወገናቸውም ዐሥራ ሁለት አለቆች ናቸው። እስማኤልም የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው፥ የመጨረሻዋ እስትንፋሱን ተንፍሶም ሞተ፥ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። ዘሮቹም ከግብጽ በስተ ምሥራቅ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ በሐዊላና በሹር መካከል ሲሰፍሩ፤ የኖረውም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት በተቃርኖ ነበር። የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድም ይህ ነው፥ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፥ ይስሐቅም አርባ ዓመት ሲሆነው ርብቃን አገባ፥ እርሷም በመስጴጦምያ የሚኖሩ የሶርያዊው የባቱኤል ልጅና የሶርያዊው የላባ እኅት ናት። ርብቃ መኻን ስለ ነበረች ይስሐቅ ስለ እርሷ ወደ ጌታ ጸለየ፤ ጌታም ጸሎቱን ስለ ሰማ ርብቃ ፀነሰች፤ ልጆቹም በማሕፀንዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርሷም፥ “እንዲህ እሆን ዘንድ ከሆነ፥ ስለምንድን ነው የምኖረው?” አለች። ከጌታም ምላሽ ታገኝ ዘንድ ሄደች። ጌታም እንዲህ አላት፥ “ሁለት ሕዝቦች በማሕፀንሽ አሉ፤ ሁለቱም ወገኖች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤ አንዱም ከሌላው ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል።” የመውለጃዋም ሰዓት በደረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ። በመጀመሪያም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንተናውም ጠጉር ለብሶ ነበር፥ ስለዚህ ዔሳው ብለው ጠሩት። ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፥ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ያዕቆብ ተባለ። ልጆቹን በወለደች ጊዜ ይስሐቅ ሥልሳ ዓመት ሆኖት ነበር። ልጆቹም ባደጉ ጊዜ፥ ዔሳውም በዱር የሚውል ብልኅ አዳኝ ሆነ፥ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በቤትም ይቀመጥ ነበር። ይስሐቅም ዔሳው ካደነው ይበላ ነበርና ይወደው ነበር፥ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ ሲሠራ፥ ዔሳው ከአደን መጣ፤ በጣም እርቦት ነበር፤ ዔሳውም ያዕቆብን፥ “ከዚህ ከቀዩ ወጥ አብላኝ፥ እኔ እጅግ እርቦኛልና!” አለው፤ (ኤዶም የተባለውም በዚህ ምክንያት ነበር።) ያዕቆብም፥ “በመጀመሪያ ብኩርናህን ሽጥልኝ” አለው። ዔሳውም “እኔ መሞቴ ነው፤ ታዲያ ብኲርና ምን ያደርግልኛል?” አለው። ያዕቆብም፥ “እስኪ በቅድሚያ ማልልኝ” አለው። ስለዚህ ዔሳው ምሎ ብኲርናውን ለያዕቆብ ሸጠ። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ ዔሳውም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ፤ በዚህ ዓይነት ዔሳው ብኩርናውን አቃለላት።