ዕዝራ 9:1-4
ዕዝራ 9:1-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህም ከተፈጸመ በኋላ የሕዝቡ አለቆች ወደ እኔ ቀርበው፥ “የእስራኤል ሕዝብ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ እንደ ከነዓናውያን፥ እንደ ኬጤዎናውያን፥ እንደ ፌርዜዎናውያን፦ እንደ ኢያቡሴዎናውያን፥ እንደ አሞናውያን፥ እንደ ሞዓባውያን፥ እንደ ግብፃውያንና እንደ አሞራውያን ርኵሰት ያደርጋሉ እንጂ ከምድር አሕዛብ አልተለዩም፤ ለራሳቸውና ለልጆቻቸውም ሴቶች ልጆቻቸውን ወስደዋል፤ የተቀደሰውንም ዘር ከምድር አሕዛብ ጋር ደባልቀዋል፤ አስቀድሞም አለቆቹና ሹሞቹ በዚህ መተላለፍ መጀመሪያ ሆነዋል” አሉኝ። ይህንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልብሴንና መጐናጸፊያዬን ቀደድሁ፤ አዘንሁም፤ የራሴንና የጢሜንም ጠጕር ነጨሁ፤ ደንግጬም ተቀመጥሁ። ስለ ምርኮኞቹም መተላለፍ የእስራኤልን አምላክ ቃል የሚፈሩ ሁሉ ወደ እኔ ተሰበሰቡ፤ እኔም እስከ ሠርክ መሥዋዕት ድረስ ዐዝኜ ተቀመጥሁ።
ዕዝራ 9:1-4 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እነዚህ ነገሮች ከተፈጸሙ በኋላ መሪዎቹ ወደ እኔ መጥተው እንዲህ አሉኝ፤ “ካህናቱንና ሌዋውያኑን ጨምሮ የእስራኤል ሕዝብ ከጎረቤቶቻቸው ከከነዓናውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኢያቡሳውያን፣ ከአሞናውያን ርኩሰት ራሳቸውን አልለዩም። ሴቶቻቸውን ለራሳቸውና ለልጆቻቸው ሚስት አድርገው ወስደዋል፤ የተቀደሰውንም ዘር ከምድር ሕዝቦች ጋር ደባልቀዋል፤ በዚህ በደል ዋነኛ የሆኑትም መሪዎቹና ሹማምቱ ናቸው።” እኔም ይህን በሰማሁ ጊዜ፣ መጐናጸፊያዬንና ካባዬን ቀደድሁ፤ የራሴን ጠጕርና ጢሜን ነጨሁ፤ እጅግ ደንግጬም ተቀመጥሁ። በደል ከፈጸሙት ምርኮኞች የተነሣም በእስራኤል አምላክ ቃል የተንቀጠቀጡት ሁሉ በዙሪያዬ ተሰበሰቡ፤ እኔም እስከ ሠርክ መሥዋዕት ድረስ እጅግ እንደ ደነገጥሁ በዚያው ተቀመጥሁ።
ዕዝራ 9:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይህም ከተፈጸመ በኋላ አለቆቹ ወደ እኔ ቀርበው፦ “የእስራኤል ሕዝብ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ እንደ ከነዓናውያን፥ እንደ ኬጢያውያን፥ እንደ ፌርዛውያን፥ እንደ ኢያቡሳውያን፥ እንደ አሞናውያን፥ እንደ ሞዓባውያን፥ እንደ ግብጻውያንና እንደ አሞራውያን ርኵሰት ያደርጋሉ እንጂ ከምድር አሕዛብ አልተለዩም፤ ለራሳቸውና ለልጆቻቸውም ሴቶች ልጆቻቸውን ወስደዋል፤ የተቀደሰውንም ዘር ከምድር አሕዛብ ጋር ደባልቀዋል፤ አስቀድሞም አለቆቹና ሹማምንቶቹ በዚህ መተላለፍ መጀመሪያ ሆነዋል” አሉኝ። ይህንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልብሴንና መጐናጸፊያዬን ቀደድሁ፤ የራሴንና የጢሜንም ጠጉር ነጨሁ፤ ደንግጬም ተቀመጥሁ። ስለ ምርኮኞቹም መተላለፍ የእስራኤልን አምላክ ቃል የሚፈሩ ሁሉ ወደ እኔ ተሰበሰቡ፤ እኔም እስከ ሠርክ መሥዋዕት ድረስ ደንግጬ ተቀመጥሁ።
ዕዝራ 9:1-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህም ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ መሪዎች አንዳንዶቹ ወደ እኔ ቀርበው ከዚህ የሚከተለውን ቃል ነገሩኝ፦ “ሕዝቡና ካህናቱ ሌዋውያኑም ጭምር በጐረቤት ባሉት በዐሞን፥ በሞአብና በግብጽ ከሚኖሩትና እንዲሁም ከከነዓናውያን፥ ከሒታውያን፥ ከፈሪዛውያን፥ ከኢያቡሳውያንና ከአሞራውያን ርኲሰት ራሳቸውን አልጠበቁም፤ እነዚያ አሕዛብ ሲፈጽሙት የነበረውን አጸያፊ ነገር ሁሉ አድርገዋል። ለራሳቸውና ለልጆቻቸው ሚስቶች የሚሆኑ ከእነዚያ ወገኖች አግብተዋል፤ አጋብተዋልም፤ ቅዱሱን ዘር ከሌሎች ከአካባቢው አሕዛብ ጋር ቀላቅለዋል፤ በዚህ እምነተ ቢስ በሆነ ተግባር መሪዎቹና ባለ ሥልጣኖቹ ግንባር ቀደም ሆነዋል።” እኔም ይህን በሰማሁ ጊዜ በሐዘን መጐናጸፊያዬንና ካባዬን ቀደድሁ፤ የራስ ጠጒሬንና ጢሜን በመንጨት በብርቱ ሐዘን ላይ ሆኜ ተቀመጥሁ፤ የሠርክ መሥዋዕት እስከሚቀርብበትም ጊዜ ድረስ በድንጋጤና በሐዘን ቈየሁ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች ስለ ሠሩት ኃጢአት በተናገረው ቃል ከመፍራት የተነሣ ድንጋጤ አድሮባቸው የነበሩትም ሁሉ በዙሪያዬ ተሰበሰቡ።
ዕዝራ 9:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነዚህ ነገሮች ከተፈጸሙ በኋላ አለቆቹ ወደ እኔ ቀርበው፦ “የእስራኤል ሕዝብ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑም እንደ ከነዓናውያን፥ ሒቲያውያን፥ ፌርዛውያን፥ ኢያቡሳውያን፥ አሞናውያን፥ ሞዓባውያን፥ ግብጻውያንና አሞራውያን ርኩሰት ያደርጋሉ እንጂ ከምድር ሕዝቦች እራሳቸውን አልለዩም፤ አንዳንድ ሴቶች ልጆቻቸውን ለራሳቸውና ለወንዶች ልጆቻቸው ሚስት አድርገው ወስደዋል፥ ቅዱሱንም ዘር ከምድር ሕዝቦች ጋር ደባልቀዋል፤ በዚህ አለመታመን የአለቆቹና የባለሥልጣኖቹ እጅ ቀዳሚ ነበር።” ይህንንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልብሴንና ካባዬን ቀደድሁ፥ የራሴን ጠጉርና ጢሜንም ነጨሁ፥ ደንግጬም ተቀመጥሁ። በእስራኤል አምላክ ቃል የሚንቀጠቀጡ ሁሉ ስለ ምርኮኞቹ አለመታመን ወደ እኔ ተሰበሰቡ፥ እኔም እስከ ሠርክ መሥዋዕት ድረስ ደንግጬ ተቀመጥሁ።