ዕዝራ 4:17-24
ዕዝራ 4:17-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ንጉሡም ለአዛዡ ለሬሁም፥ ለጸሓፊውም ለሲምሳይ፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶም ለተቀመጡትና ለቀሩት ተባባሪዎቻቸው እንዲህ የሚለውን መልስ ላከ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን። አሁንም ወደ እኛ የላካችሁት መልእክተኛ ወደ እኔ ደረሰ እኔም አዝዣለሁ፤ ተመረመረም፤ ይህችም ከተማ ከጥንት ጀምራ በነገሥታት ላይ ዐመፀኛ እንደ ነበረች፥ በእርስዋም ዐመፅና ሽፍትነት እንደ ተደረገ ተገኘ። በኢየሩሳሌምም እጅግ ኀያላን ነገሥታት ነበሩ፤ በወንዝም ማዶ ያለውን ሀገር ሁሉ ይገዙ ነበር፤ ግብርንና እጅ መንሻንም ይቀበሉ ነበር። አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲተዉ፥ ይህችም ከተማ እንዳትሠራ ትእዛዝ ስጡ። በዚህም ነገር እንዳትሳሳቱ፥ በነገሥታቱም ጕዳትና ጥፋት እንዳይበዛ ተጠንቀቁ።” የንጉሡም የአርተሰስታ መልእክተኛ በደረሰ ጊዜ በአዛዡ በሬሁምና በጸሓፊው በሲምሳይ፥ በተባባሪዎቻቸውም ፊት መልእክቱን ባነበበ ጊዜ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አይሁድ በፈረስ ሄዱ፤ በኀይልም አስተዉአቸው። በዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ተቋረጠ፤ እስከ ፋርስም ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ተጓጐለ።
ዕዝራ 4:17-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ንጉሡም ይህን መልስ ላከ፤ ለአገረ ገዥው ሬሁም፣ ለጸሓፊው ሲምሳይ፣ በሰማርያና በኤፍራጥስ ማዶ ለሚኖሩ ተባባሪዎቻቸው፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ የላካችሁልኝ ደብዳቤ በፊቴ ተተርጕሞ ተነብቧል። እኔም ትእዛዝ ሰጥቼ ምርመራ ተደርጓል፤ በምርመራውም መሠረት ይህች ከተማ ከጥንት ጀምሮ በነገሥታት ላይ ስታምፅ የኖረች የዐመፅና የወንጀል መናኸሪያ እንደ ሆነች ማስረጃ ተገኝቷል። ኢየሩሳሌም ከኤፍራጥስ ማዶ ያለውን አገር ሁሉ የገዙ፣ ቀረጥ፣ ግብርና እጅ መንሻም ይቀበሉ የነበሩ ኀያላን ነገሥታት ነበሯት። አሁንም እኔ ትእዛዝ እስከምሰጥበት ድረስ ይህች ከተማ እንደ ገና እንዳትሠራ ሥራውን ያቆሙ ዘንድ ለእነዚህ ሰዎች ትእዛዝ አስተላልፉ። ይህን ነገር ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ በነገሥታቱ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ለምን እየበዛ ይሄዳል? የንጉሡ የአርጤክስስ ደብዳቤ ቅጅ በሬሁም፣ በጸሓፊው በሲምሳይና በተባባሪዎቻቸው ፊት እንደ ተነበበ፣ ወዲያውኑ በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት አይሁድ ሄደው ሥራውን እንዲያቆሙ አስገደዷቸው። ስለዚህም በኢየሩሳሌም የሚሠራው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ሁለተኛ ዓመት ድረስ ተቋረጠ።
ዕዝራ 4:17-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ንጉሡም ለአዛዡ ለሬሁም፥ ለጸሐፊውም ለሲምሳይ፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶም ለተቀመጡት እና ለቀሩት ተባባሪዎቻቸው እንዲህ የሚለውን መልስ ላከ፤ “ሰላም፤ አሁንም ወደ እኛ የላካችሁት ደብዳቤ በፊቴ ተተርጕሞ ተነበበ። እኔም አዝዣለሁ፤ ተመረመረም፤ ይህችም ከተማ ከጥንት ጀምራ በነገሥታት ላይ ዓመፀኛ እንደ ነበረች፥ በእርስዋም ዓመፅና ሽፍትነት እንደ ተደረገ ተገኘ። በኢየሩሳሌምም እጅግ ኃያላን ነገሥታት ነበሩ፤ በወንዝም ማዶ ያለውን አገር ሁሉ ይገዙ ነበር፤ ግብርንና ቀረጥን መጥንንም ይቀበሉ ነበር። አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲተዉ፥ እኔም እስካዝዝ ድረስ ይህች ከተማ እንዳትሠራ ትእዛዝ ስጡ። ቸልም እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ ለነገሥታቱ ጉዳትና ጥፋት እየበዛ ስለ ምን ይሄዳል?” የንጉሡም የአርጤክስስ ደብዳቤ ግልባጭ በሬሁምና በጸሐፊው በሲምሳይ በተባባሪዎቻቸውም ፊት በተነበበ ጊዜ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አይሁድ ሄዱ፤ በግድና በኃይልም አስተዉአቸው። በዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ቀረ፤ እስከ ፋርስም ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ተጓጐለ።
ዕዝራ 4:17-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ንጉሠ ነገሥቱም ለዚህ ደብዳቤ ከዚህ የሚከተለውን መልስ ላከ፦ “ለአገረ ገዢው ረሑም፥ ለአውራጃ ጸሐፊው ሺምሻይ፥ እንዲሁም በሰማርያና ከኤፍራጥስ በስተ ምዕራብ ለሚኖሩ ተባባሪዎችህ ሁሉ፥ ሰላም ለእናንተ ይሁን። “የላካችሁልኝ ደብዳቤ ተተርጒሞ በንባብ ሰምቼዋለሁ፤ በእርሱም መነሻነት ጥብቅ ምርምርና ጥናት እንዲደረግ ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ ከጥናቱም የተገኘው ውጤት ኢየሩሳሌም ከጥንት ጀምሮ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ስታምፅ የኖረች ዐመፀኞችና አስቸጋሪዎች ሰዎች የሞሉባት ከተማ እንደ ነበረች ያስረዳል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ፥ ኢየሩሳሌም ከኤፍራጥስ በስተ ምዕራብ ያሉትን አገሮች ሁሉ በማስገበር ቀረጥና ግብር የሚያስከፍሉ ኀያላን ነገሥታት ነግሠውባት ነበር። ስለዚህ እኔ ሌላ ትእዛዝ እስካስተላልፍ ድረስ እነዚያ ሰዎች ከተማይቱን እንደገና መሥራታቸውን ያቆሙ ዘንድ እዘዙ። በመንግሥታችን ላይ ምንም ችግር እንዳይደርስ ኀላፊነታችሁን ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ።” ንጉሠ ነገሥቱ አርጤክስስ የላከው የመልስ ደብዳቤም መጥቶ ለረሑም፥ ለሺምሻይና ለተባባሪዎቻቸው ሁሉ እንደ ተነበበላቸው፥ ወዲያውኑ ወደ ኢየሩሳሌም ገሥግሠው በመምጣት ሕዝቡን በማስገደድ የኢየሩሳሌምን ከተማ እንደገና ከመሥራት አገዱአቸው፤ ስለዚህ ዳርዮስ በፋርስ እስከ ነገሠበት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ የቤተ መቅደሱ ሥራ በመቋረጡ በጅምር ቀርቶ ነበር።
ዕዝራ 4:17-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ንጉሡ እንዲህ የሚለውን መልስ ላከ፦ “ለአዛዡ ለሬሑምና ለጸሐፊውም ለሺምሻይ፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶ ባለ አገር ለተቀመጡ ለቀሩት ተባባሪዎቻቸው ሰላም! አሁንም ወደ እኛ የላካችሁት ደብዳቤ በፊቴ በግልፅ ተነበበ። እኔም አዝዣለሁ፥ ተመረመረም፥ ይህችም ከተማ ከጥንት ጀምራ በነገሥታት ላይ ዓመፀኛ እንደ ነበረች፥ በእርሷም ዓመፅና ሽፍትነት እንደ ተደረገ ተገኘ። በኢየሩሳሌምም እጅግ ኃያላን ነገሥታት ነበሩ፥ በወንዝም ማዶ ያለውን አገር ሁሉ ይገዙ ነበር፤ ግብርንና ቀረጥን መጥንንም ይቀበሉ ነበር። አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲተዉ፥ እኔም ትእዛዝ እስከምሰጥ ድረስ ይህች ከተማ እንዳትሠራ ትእዛዝ ስጡ። ቸልም እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ ለነገሥታቱ ጉዳትና ጥፋት እየበዛ ስለምን ይሄዳል?” የንጉሡም የአርጤክስስ ደብዳቤ ግልባጭ በሬሑምና በጸሐፊው በሺምሻይ በተባባሪዎቻቸውም ፊት በተነበበ ጊዜ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አይሁድ ሄዱ፤ በግድና በኃይልም አስተዉአቸው። በዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ቀረ፤ እስከ ፋርስም ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ተቋረጠ።