መጽሐፈ ዕዝራ 4:17-24

መጽሐፈ ዕዝራ 4:17-24 መቅካእኤ

ንጉሡ እንዲህ የሚለውን መልስ ላከ፦ “ለአዛዡ ለሬሑምና ለጸሐፊውም ለሺምሻይ፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶ ባለ አገር ለተቀመጡ ለቀሩት ተባባሪዎቻቸው ሰላም! አሁንም ወደ እኛ የላካችሁት ደብዳቤ በፊቴ በግልፅ ተነበበ። እኔም አዝዣለሁ፥ ተመረመረም፥ ይህችም ከተማ ከጥንት ጀምራ በነገሥታት ላይ ዓመፀኛ እንደ ነበረች፥ በእርሷም ዓመፅና ሽፍትነት እንደ ተደረገ ተገኘ። በኢየሩሳሌምም እጅግ ኃያላን ነገሥታት ነበሩ፥ በወንዝም ማዶ ያለውን አገር ሁሉ ይገዙ ነበር፤ ግብርንና ቀረጥን መጥንንም ይቀበሉ ነበር። አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲተዉ፥ እኔም ትእዛዝ እስከምሰጥ ድረስ ይህች ከተማ እንዳትሠራ ትእዛዝ ስጡ። ቸልም እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ ለነገሥታቱ ጉዳትና ጥፋት እየበዛ ስለምን ይሄዳል?” የንጉሡም የአርጤክስስ ደብዳቤ ግልባጭ በሬሑምና በጸሐፊው በሺምሻይ በተባባሪዎቻቸውም ፊት በተነበበ ጊዜ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አይሁድ ሄዱ፤ በግድና በኃይልም አስተዉአቸው። በዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ቀረ፤ እስከ ፋርስም ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ተቋረጠ።