ዕዝራ 4:17-24

ዕዝራ 4:17-24 NASV

ንጉሡም ይህን መልስ ላከ፤ ለአገረ ገዥው ሬሁም፣ ለጸሓፊው ሲምሳይ፣ በሰማርያና በኤፍራጥስ ማዶ ለሚኖሩ ተባባሪዎቻቸው፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ የላካችሁልኝ ደብዳቤ በፊቴ ተተርጕሞ ተነብቧል። እኔም ትእዛዝ ሰጥቼ ምርመራ ተደርጓል፤ በምርመራውም መሠረት ይህች ከተማ ከጥንት ጀምሮ በነገሥታት ላይ ስታምፅ የኖረች የዐመፅና የወንጀል መናኸሪያ እንደ ሆነች ማስረጃ ተገኝቷል። ኢየሩሳሌም ከኤፍራጥስ ማዶ ያለውን አገር ሁሉ የገዙ፣ ቀረጥ፣ ግብርና እጅ መንሻም ይቀበሉ የነበሩ ኀያላን ነገሥታት ነበሯት። አሁንም እኔ ትእዛዝ እስከምሰጥበት ድረስ ይህች ከተማ እንደ ገና እንዳትሠራ ሥራውን ያቆሙ ዘንድ ለእነዚህ ሰዎች ትእዛዝ አስተላልፉ። ይህን ነገር ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ በነገሥታቱ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ለምን እየበዛ ይሄዳል? የንጉሡ የአርጤክስስ ደብዳቤ ቅጅ በሬሁም፣ በጸሓፊው በሲምሳይና በተባባሪዎቻቸው ፊት እንደ ተነበበ፣ ወዲያውኑ በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት አይሁድ ሄደው ሥራውን እንዲያቆሙ አስገደዷቸው። ስለዚህም በኢየሩሳሌም የሚሠራው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ሁለተኛ ዓመት ድረስ ተቋረጠ።