ዕዝራ 2:59-63
ዕዝራ 2:59-63 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ የሚከተሉት ደግሞ ከቴልሜላ፣ ከቴላሬሳ፣ ከክሩብ፣ ከአዳንና ከኢሜር ከተሞች የመጡ ናቸው፤ ነገር ግን ቤተ ሰቦቻቸው የእስራኤል ዘር መሆናቸውን ማስረዳት አልቻሉም፦ የዳላያ፣ የጦብያና የኔቆዳ ዘሮች 652 ከካህናቱ መካከል፦ የኤብያ፣ የአቆስና የቤርዜሊ ዘሮች፤ ቤርዜሊ በዚህ ስም ሊጠራ የቻለው የገለዓዳዊውን የቤርዜሊን ልጅ አግብቶ ስለ ነበር ነው። እነዚህ በትውልድ መዝገቡ ውስጥ የቤተ ሰባቸውን ዝርዝር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም፤ ስለዚህ እንዳልነጹ ተቈጥረው፣ ከክህነት አገልግሎት ተገለሉ። አገረ ገዥውም በኡሪምና በቱሚም እግዚአብሔርን የሚጠይቅ ካህን እስኪነሣ ድረስ፣ እጅግ ከተቀደሰው ምግብ እንዳይበሉ አዘዛቸው።
ዕዝራ 2:59-63 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቴልሜላሕ፥ ቴልሐርሻ፥ ከሩብ፥ አዳንና ኢሜር ተብለው ከሚጠሩት ከተሞች ከምርኮ የተመለሱ ነበሩ፤ ነገር ግን የእነርሱ ዘር ከእስራኤል ወገን መሆኑን ሊያስረዱ አልቻሉም። የደላያ፥ የጦቢያና የነቆዳ ጐሣዎች ወገኖችም 652 ነበሩ፤ ከዚህ የሚከተሉት የካህናት ጐሣዎች ሐባያ፥ ሀቆጽና ባርዚላይ የቀድሞ አባቶች እነማን እንደ ነበሩ ካለማወቃቸውም የተነሣ ካህናት ሆነው ለማገልገል ተቀባይነት አላገኙም። (ባርዚላይ ከገለዓዳዊው የባርዚላይ ልጆች አንድዋን አግብቶ በዚሁ ስም ይጠራ ነበር)። በኡሪምና በቱሚም የእግዚአብሔርን ፈቃድ መጠየቅ የሚችል ካህን እስከሚነሣም ድረስ እነርሱ የተቀደሰውን ምግብ መብላት እንደማይችሉ ገዢው አዘዛቸው።
ዕዝራ 2:59-63 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከቲልሜላ፥ ከቴላርሳ፥ ከክሩብ፥ ከሐዳን፥ ከኤሜር የወጡ እነዚህ ነበሩ፤ ነገር ግን የአባቶቻቸውን ቤቶችና ዘራቸውን ወይም ከእስራኤል ወገን መሆናቸውን ያስታውቁ ዘንድ አልቻሉም፤ የዳላያ ልጆች፥ የጦብያ ልጆች፥ የኒቆዳ ልጆች፥ ስድስት መቶ አምሳ ሁለት ነበሩ። ከካህናቱም ልጆች፤ የአብያ ልጆች፥ የአቆስ ልጆች፥ ከገለዓዳዊው ከቤርዜሊ ልጆች ሚስት ያገባ፥ በስማቸውም የተጠራ የቤርዜሊ ልጆች። እነዚህ በትውልድ መጽሐፍ ትውልዳቸውን ፈለጉ፤ ነገር ግን አልተገኘም፤ ከክህነትም ተከለከሉ። ሐቲርሰስታም፥ “በኡሪምና በቱሚም የሚፈርድ ካህን እስኪነሣ ድረስ ከቅዱሰ ቅዱሳኑ አትበሉም” አላቸው።
ዕዝራ 2:59-63 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከቴልሜላ፥ ከቴላሬሳ፥ ከክሩብ፥ ከአዳን፥ ከኢሜር የወጡ እነዚህ ነበሩ፤ ነገር ግን የአባቶቻቸውን ቤቶችና ዘራቸውን ወይም ከእስራኤል ወገን መሆናቸውን ያስታውቁ ዘንድ አልቻሉም፤ የዳላያ ልጆች፥ የጦብያ ልጆች፥ የኔቆዳ ልጆች፥ ስድስት መቶ አምሳ ሁለት ነበሩ። ከካህናቱም ልጆች፤ የኤብያ ልጆች፥ የአቆስ ልጆች፥ ከገለዓዳዊው ከቤርዜሊ ልጆች ሚስት ያገባ፥ በስሙም የተጠራ የቤርዜሊ ልጆች። እነዚህ በትውልድ መጽሐፍ ትውልዳቸውን ፈለጉ፤ ነገር ግን አልተገኘም፤ ከክህነትም ተከለከሉ። ሐቴርሰታም “በኡሪምና በቱሚም የሚፈርድ ካህን እስኪነሣ ድረስ ከቅዱሰ ቅዱሳን አትበሉም” አላቸው።
ዕዝራ 2:59-63 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከቴልሜላሕ፥ ቴልሐርሻ፥ ክሩብ፥ ዓዳን፥ ኢሜር የወጡ እነዚህ ነበሩ፤ ነገር ግን የአባቶቻቸውን ቤቶችና ዘራቸውን ወይም ከእስራኤል ወገን መሆናቸውን ማስታወቅ አልቻሉም፤ የድላያ ልጆች፥ የጦብያ ልጆች፥ የንቆዳ ልጆች፥ ስድስት መቶ አምሳ ሁለት ነበሩ። ከካህናቱም ልጆች፦ የሖባያ ልጆች፥ የሃቆፅ ልጆች፥ የባርዚላይ ልጆች ከገለዓዳዊው ባርዚላይ ሚስት ያገባ፥ በስማቸውም የተጠራ ነው። እነዚህ በትውልድ መጽሐፍ ትውልዳቸውን ፈለጉ፥ ነገር ግን አልተገኙም፤ እንደ ርኩሳን ከክህነት ተከለከሉ። አስተዳዳሪውም፦ በኡሪምና በቱሚም የሚጠይቅ ካህን እስኪነሣ ድረስ ከቅዱሰ ቅዱሳን አትበሉም አላቸው።