ዘፀአት 40:34-38
ዘፀአት 40:34-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ደመናውም የምስክሩን ድንኳን ከደነ፤ ድንኳንዋም የእግዚአብሔርን ክብር ተሞላች። ደመናውም በላዩ ስለነበር ድንኳኑም የእግዚአብሔርን ክብር ስለ ተሞላ ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም። ደመናውም ከድንኳኑ በተነሣ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በየነገዳቸው ይጓዙ ነበር። ደመናው ካልተነሣ ግን ደመናው እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። ደመና በቀን በድንኳኑ ላይ ነበርና፥ እሳቱም በሚጓዙበት ሁሉ በሌሊት በእስራኤል ሁሉ ፊት በእርስዋ ላይ ነበርና።
ዘፀአት 40:34-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ሸፈነ፤ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ማደሪያውን ሞላ። ደመናው በላዩ ላይ ስለ ነበረና የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላው፣ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን መግባት አልቻለም። በእስራኤላውያን ጕዞ ሁሉ ደመናው ከማደሪያው ላይ በተነሣ ጊዜ፣ ይጓዙ ነበር፤ ደመናው ካልተነሣ ግን፣ እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። ስለዚህ በጕዟቸው ሁሉ ወቅት፣ በእስራኤል ቤት ፊት ሁሉ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ደመና በቀን ከማደሪያው በላይ፣ በሌሊትም እሳቱ በደመናው ውስጥ ነበር።
ዘፀአት 40:34-38 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ደመናውም የመገናኛውን ድንኳን ከደነ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ሞላ። ደመናውም በላዩ ስለ ነበረ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም። ደመናውም ከማደሪያው በተነሣ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በመንገዳቸው ሁሉ ይጓዙ ነበር። ደመናው ባይነሣ እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። በመንገዳቸውም ሁሉ በእስራኤል ቤት ሁሉ ፊት የእግዚአብሔር ደመና በማደሪያው ላይ በቀን ነበረና፥ እሳትም በሌሊት በዚያ ላይ ነበረና።
ዘፀአት 40:34-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ድንኳኑ በደመና ተሸፈነ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ድንኳኑን ሞላው። ደመናው ስለረበበበትና የእግዚአብሔርም ክብር ድንኳኑን ስለ ሞላው ሙሴ ወደ ድንኳኑ ለመግባት አልቻለም። በጉዞአቸው ሁሉ እስራኤላውያን የሰፈሩበትን ቦታ ለቀው የሚንቀሳቀሱት ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሣበት ጊዜ ብቻ ነበር፤ ደመናው እዚያው እስካለ ድረስ ሰፈራቸውን ለቀው አይሄዱም ነበር። በሚጓዙበት ጊዜ ሁሉ በቀን የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጠው ደመና ድንኳኑን ሲሸፍን፥ በሌሊት ደግሞ በደመናው ውስጥ እሳት ያዩ ነበር።
ዘፀአት 40:34-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህ በኋላ ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ሸፈነ፥ የጌታም ክብር ማደሪያውን ሞላ። ደመናው በላዩ ስለ ነበረና የጌታ ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን መግባት አልቻለም። ደመናው ከማደሪያው በሚነሣበት ጊዜ የእስራኤል ልጆች ወደሚጓዙበት ሁሉ ይሄዱ ነበር። ደመናው ካልተነሣ ግን እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። በጉዞአቸው ሁሉ በእስራኤል ቤት ሁሉ ፊት የጌታ ደመና በቀን በማደሪያው ላይ፥ በሌሊትም እሳት በዚያ ላይ ነበረ።