ኦሪት ዘጸአት 40
40
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2ከመጀመሪያው ወር በፊተኛው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ማደሪያ ትተክላለህ። 3በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፥ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ። 4ገበታውንም አግብተህ በእርሱ ላይ የሚኖረውን ዕቃ ታሰናዳለህ፤ መቅረዙንም አግብተህ ቀንዲሎቹን ትለኩሳለህ። 5ለዕጣንም የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ታኖራለህ፥ በማደሪያውም ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ትጋርዳለህ። 6ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት ታኖረዋለህ። 7የመታጠቢያውን ሰንም በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኑረህ ውኃ ትጨምርበታለህ። 8በዙሪያውም አደባባዩን ትተክላለህ፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ትዘረጋለህ። 9የቅብዓቱንም ዘይት ወስደህ ማደሪያውን በእርሱም ያለውን ሁሉ ትቀባለህ፥ እርሱንም ዕቃውንም ሁሉ ትቀድሳለህ፤ ቅዱስም ይሆናል። 10ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ ዕቃውንም ሁሉ ትቀባዋለህ፥ መሠዊያውንም ትቀድሳለህ፤ መሠዊያውም ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናል። 11የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውን ቀብተህ ትቀድሳለህ። 12አሮንንና ልጆቹንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አቅርበህ በውኃ ታጥባቸዋለህ። 13የተቀደሰውንም ልብስ አሮንን ታለብሰዋለህ፤ በክህነትም ያገለግለኝ ዘንድ ቀብተህ ትቀድሰዋለህ። 14ልጆቹንም አቅርበህ ሸሚዞችን ታለብሳቸዋለህ፤ 15በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አባታቸውን እንደ ቀባህ ትቀባቸዋለህ፤ መቀባታቸውም ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ክህነት ይሆንላቸዋል። 16ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ። 17እንዲህም ሆነ፤ በሁለተኛው ዓመት በፊተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ማደሪያው ተተከለ። 18እግዚአብሔርም እንዳዘዘው ሙሴ ማደሪያውን ተከለ፥ እግሮቹንም አኖረ፥ ሳንቆቹንም አቆመ፥ መወርወሪያዎቹንም አደረገባቸው፥ ምሰሶቹንም አቆመ። 19ድንኳኑንም በማደሪያው ላይ ዘረጋ፥ የድንኳኑን መደረቢያ በላዩ አደረገበት። 20እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ጽላቱን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አኖረው፥ መሎጊያዎቹን በታቦቱ ዘንድ አደረገ፥ የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ አኖረው፤ 21ታቦቱን ወደ ማደሪያው አገባ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ አድርጎ የምስክሩን ታቦት ሸፈነ። 22እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ገበታውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ ከመጋረጃው ውጭ፥ በማደሪያው በሰሜን በኩል አኖረው፤ 23እንጀራውን በላዩ በእግዚአብሔር ፊት አሰናዳ። 24እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው መቅረዙን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በገበታው ፊት ለፊት፥ በማደሪያው በደቡብ በኩል አኖረ፤ 25ቀንዲሎቹን በእግዚአብሔር ፊት ለኰሰ። 26እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የወርቁን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በመጋረጃው ፊት አኖረ፤ 27የጣፋጩን ሽቱ ዕጣን ዐጠነበት። 28እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በማደሪያው ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ዘረጋ። 29ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት አኖረ፥ የሚቃጠለውንና የእህልን መሥዋዕት ሠዋበት። 30እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የመታጠቢያውን ሰን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኖረ፥ ለመታጠቢያም ውኃን ጨመረበት። 31በእርሱም ሙሴና አሮን ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ታጠቡ፤ 32ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ፥ ወደ መሠዊያውም በቀረቡ ጊዜ ይታጠቡ ነበር። 33በማደሪያውና በመሠዊያውም ዙሪያ አደባባዩን ተከለ፤ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ዘረጋ። እንዲሁም ሙሴ ሥራውን ፈጸመ። 34ደመናውም የመገናኛውን ድንኳን ከደነ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ሞላ። 35ደመናውም በላዩ ስለ ነበረ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም። 36ደመናውም ከማደሪያው በተነሣ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በመንገዳቸው ሁሉ ይጓዙ ነበር። 37ደመናው ባይነሣ እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። 38በመንገዳቸውም ሁሉ በእስራኤል ቤት ሁሉ ፊት የእግዚአብሔር ደመና በማደሪያው ላይ በቀን ነበረና፥ እሳትም በሌሊት በዚያ ላይ ነበረና።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 40: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ