የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፀአት 4:10-16

ዘፀአት 4:10-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሙሴም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አለው፥ “ጌታ ሆይ፥ እማ​ል​ድ​ሃ​ለሁ፤ ትና​ንት፥ ከት​ና​ንት ወዲያ ባሪ​ያ​ህን ከተ​ና​ገ​ር​ኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይ​ደ​ለ​ሁም። እኔ አፌ ኰል​ታፋ፥ ምላ​ሴም ተብ​ታባ የሆነ ሰው ነኝ።” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴን አለው፥ “ለሰው አፍን የሰጠ ማን ነው? ዲዳስ፥ ደን​ቆ​ሮስ፥ የሚ​ያ​ይስ፥ ዕው​ርስ የሚ​ያ​ደ​ርግ ማን ነው? እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አይ​ደ​ለ​ሁ​ምን? እን​ግ​ዲህ አሁን ሂድ፤ እኔም አን​ደ​በ​ት​ህን አረ​ታ​ለሁ፤ ትና​ገ​ረ​ውም ዘንድ ያለ​ህን አለ​ብ​ም​ሃ​ለሁ” አለው። ሙሴም፥ “ጌታ ሆይ፥ እማ​ል​ድ​ሃ​ለሁ፤ መና​ገር የሚ​ችል የም​ት​ል​ከው ሌላ ሰው ፈልግ” አለው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በሙሴ ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እን​ዲ​ህም አለ፥ “ሌዋ​ዊው ወን​ድ​ምህ አሮን አለ አይ​ደ​ለ​ምን? እርሱ እን​ደ​ሚ​ና​ገ​ር​ልህ አው​ቃ​ለሁ፤ እነ​ሆም፥ እርሱ ሊገ​ና​ኝህ ይመ​ጣል፤ በአ​የ​ህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለ​ዋል። አን​ተም ትና​ገ​ረ​ዋ​ለህ፤ ቃሌ​ንም በአፉ ታደ​ር​ገ​ዋ​ለህ፤ እኔ አን​ደ​በ​ት​ህ​ንና አን​ደ​በ​ቱን አረ​ታ​ለሁ፤ የም​ታ​ደ​ር​ጉ​ት​ንም አለ​ብ​ማ​ች​ኋ​ለሁ። እርሱ ስለ አንተ ከሕ​ዝቡ ጋር ይነ​ጋ​ገ​ራል፤ እርሱ አፍ ይሆ​ን​ል​ሃል፤ አን​ተም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ትሆ​ን​ለ​ታ​ለህ።

ዘፀአት 4:10-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሙሴም እግዚአብሔርን (ያህዌ)፣ “ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋር ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም። እኔ ኰልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” አለው። እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን፣ “ለሰው አንደበቱን የሰጠው ማነው? ሰውን ደንቈሮ ወይም ዲዳ የሚያደርገው ማነው? ዐይን የሚሰጥ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማነው? እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) አይደለሁምን? በል አሁን ሂድ፤ እኔ እንድትናገር አደርግሃለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ” አለው። ሙሴ ግን፣ “ጌታ ሆይ (አዶናይ)፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” አለው። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደል? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልቡ ደስ ይለዋል። ለእርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገራቸውንም ቃላት በአንደበቱ ታኖራለህ፤ ሁለታችሁም በትክክል እንድትናገሩ እረዳችኋለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ። አንተ እንደ አምላኩ ሆነህ ትነግረዋለህ፤ እርሱም እንደ አንደበትህ ሆኖ ለሕዝቡ ይናገርልሃል።

ዘፀአት 4:10-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “ጌታ ሆይ! እኔ አፌ ኮልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም።” እግዚአብሔርም፦ “የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳስ ደንቆሮስ የሚያይስ ዕውርስ ያደረገ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? እንግዲህ አሁን ሂድ፤ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ፤” አለው። እርሱም፦ “ጌታ ሆይ! በምትልከው ሰው እጅ ትልክ ዘንድ እለምንሃለሁ፤” አለ። የእግዚአብሔርም ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ እንዲህም አለ፦ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ደህና እንዲናገር አውቃለሁ፤ እነሆም ደግሞ ሊገናኝህ ይመጣል፤ ባየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል። አንተም ትናገረዋለህ፤ ቃሉንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ ከአፍህና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፤ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ። እርሱ ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል፤ አንተም በእግዚአብሔር ፈንታ ትሆንለታለህ።

ዘፀአት 4:10-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እባክህ ጌታ ሆይ፥ ወደዚያ አትላከኝ፤ ቀድሞም ሆነ ወይም አሁን አንተ ከእኔ ጋር መነጋገር ከጀመርክበት ጊዜ አንሥቶ የመናገር ችሎታ የለኝም፤ እኔ አንደበቴ የሚኮላተፍና አጥርቼ ለመናገር የማልችል ነኝ።” ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለሰው አፍን የፈጠረለት ማነው? ድዳ ወይም ደንቆሮ፥ ዐይኑ እንዲያይ ወይም እንዳያይ የሚያደርግስ ማነው? ይህን ሁሉ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ስለዚህ አሁን ሂድ! እኔም ከአንተ ጋር ሆኜ መናገር እንድትችል አደርጋለሁ፤ ምን መናገር እንደሚገባህ እነግርሃለሁ።” ሙሴም “እባክህ ጌታ ሆይ፥ ሌላ ሰው ላክ” አለው። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ሙሴን እጅግ ተቈጥቶ እንዲህ አለው፤ “ሌዋዊ የሆነው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ጥሩ ተናጋሪ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልብ ደስ ይለዋል። ለእርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገረውንም ቃል ታስረዳዋለህ፤ ሁለታችሁም እንዴት መናገር እንደምትችሉና ምን ማድረግ እንደሚገባችሁ አስተምራችኋለሁ፤ እርሱ አንተን ወክሎ ይናገራል፤ በአንተም ስም ቃሉን ለሕዝቡ ያስተላልፋል፤ አንተም ለእርሱ እንደ አምላክ ትሆናለህ።

ዘፀአት 4:10-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሙሴም ጌታን፦ “ጌታ ሆይ፥ እኔ አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባርያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፌንና ምላሴን ይይዘኛል።” ጌታም እንዲህ አለው፦ “የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳ ወይም ደንቆሮ ወይም የሚያይ ወይም ዕውር ያደረገ ማን ነው? እኔ ጌታ አይደለሁምን? ስለዚህ ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ።” እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ ሌላ ሰው ላክ” አለ። የጌታም ቁጣ በሙሴ ላይ ነደደ እንዲህም አለ፦ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር አውቃለሁ፤ እርሱም ደግሞ ሊገናኝህ ይመጣል፤ ያይሃልም፤ በልቡም ደስ ይለዋል። አንተም ትናገረዋለህ ቃሎቹን በአፉ ታስቀምጣለህ፤ እኔም ከአፍህ ጋርና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፥ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ። እርሱ ለአንተ ብሎ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል አንተም እንደ እግዚአብሔር ትሆንለታለህ።