ዘፀአት 4:10-13
ዘፀአት 4:10-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሙሴም እግዚአብሔርን አለው፥ “ጌታ ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ ትናንት፥ ከትናንት ወዲያ ባሪያህን ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም። እኔ አፌ ኰልታፋ፥ ምላሴም ተብታባ የሆነ ሰው ነኝ።” እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ለሰው አፍን የሰጠ ማን ነው? ዲዳስ፥ ደንቆሮስ፥ የሚያይስ፥ ዕውርስ የሚያደርግ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? እንግዲህ አሁን ሂድ፤ እኔም አንደበትህን አረታለሁ፤ ትናገረውም ዘንድ ያለህን አለብምሃለሁ” አለው። ሙሴም፥ “ጌታ ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ መናገር የሚችል የምትልከው ሌላ ሰው ፈልግ” አለው።
ዘፀአት 4:10-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሙሴም እግዚአብሔርን (ያህዌ)፣ “ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋር ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም። እኔ ኰልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” አለው። እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን፣ “ለሰው አንደበቱን የሰጠው ማነው? ሰውን ደንቈሮ ወይም ዲዳ የሚያደርገው ማነው? ዐይን የሚሰጥ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማነው? እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) አይደለሁምን? በል አሁን ሂድ፤ እኔ እንድትናገር አደርግሃለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ” አለው። ሙሴ ግን፣ “ጌታ ሆይ (አዶናይ)፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” አለው።
ዘፀአት 4:10-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “ጌታ ሆይ! እኔ አፌ ኮልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም።” እግዚአብሔርም፦ “የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳስ ደንቆሮስ የሚያይስ ዕውርስ ያደረገ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? እንግዲህ አሁን ሂድ፤ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ፤” አለው። እርሱም፦ “ጌታ ሆይ! በምትልከው ሰው እጅ ትልክ ዘንድ እለምንሃለሁ፤” አለ።
ዘፀአት 4:10-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እባክህ ጌታ ሆይ፥ ወደዚያ አትላከኝ፤ ቀድሞም ሆነ ወይም አሁን አንተ ከእኔ ጋር መነጋገር ከጀመርክበት ጊዜ አንሥቶ የመናገር ችሎታ የለኝም፤ እኔ አንደበቴ የሚኮላተፍና አጥርቼ ለመናገር የማልችል ነኝ።” ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለሰው አፍን የፈጠረለት ማነው? ድዳ ወይም ደንቆሮ፥ ዐይኑ እንዲያይ ወይም እንዳያይ የሚያደርግስ ማነው? ይህን ሁሉ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ስለዚህ አሁን ሂድ! እኔም ከአንተ ጋር ሆኜ መናገር እንድትችል አደርጋለሁ፤ ምን መናገር እንደሚገባህ እነግርሃለሁ።” ሙሴም “እባክህ ጌታ ሆይ፥ ሌላ ሰው ላክ” አለው።
ዘፀአት 4:10-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴም ጌታን፦ “ጌታ ሆይ፥ እኔ አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባርያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፌንና ምላሴን ይይዘኛል።” ጌታም እንዲህ አለው፦ “የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳ ወይም ደንቆሮ ወይም የሚያይ ወይም ዕውር ያደረገ ማን ነው? እኔ ጌታ አይደለሁምን? ስለዚህ ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ።” እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ ሌላ ሰው ላክ” አለ።