ዘፀአት 29:38-46

ዘፀአት 29:38-46 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“በመ​ሠ​ዊ​ያ​ውም ላይ የም​ታ​ቀ​ር​በው ይህ ነው፤ በቀን በቀን ዘወ​ትር በመ​ሠ​ዊ​ያው ላይ ሁለት ንጹ​ሓን የዓ​መት ጠቦ​ቶች ታቀ​ር​ባ​ለህ። አን​ዱን ጠቦት በነ​ግህ፥ ሁለ​ተ​ኛ​ው​ንም ጠቦት በሠ​ርክ መሥ​ዋ​ዕት አድ​ር​ገህ ታቀ​ር​በ​ዋ​ለህ። ከአ​ንዱ ጠቦ​ትም ጋር የኢን መስ​ፈ​ሪያ አራ​ተኛ እጅ በሆነ ተወ​ቅጦ በተ​ጠ​ለለ ዘይት የተ​ለ​ወሰ የኢፍ መስ​ፈ​ሪያ ዐሥ​ረኛ እጅ መል​ካም ዱቄት፥ ደግሞ ለመ​ጠጥ ቍር​ባን የኢን መስ​ፈ​ሪያ አራ​ተኛ እጅ የወ​ይን ጠጅ ታቀ​ር​ባ​ለህ። ሁለ​ተ​ኛ​ው​ንም ጠቦት በሠ​ርክ ታቀ​ር​በ​ዋ​ለህ፤ እንደ ነግ​ሁም የእ​ህ​ልና የመ​ጠጥ ቍር​ባን ታደ​ር​ግ​በ​ታ​ለህ፤ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በጎ መዓዛ እን​ዲ​ሆን የእ​ሳት ቍር​ባን ይሆ​ናል። በዚያ እና​ገ​ርህ ዘንድ ለአ​ንተ በም​ገ​ለ​ጥ​በት በም​ስ​ክሩ ድን​ኳን ደጃፍ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ለልጅ ልጃ​ችሁ የዘ​ወ​ትር መሥ​ዋ​ዕት ይሆ​ናል። በዚ​ያም የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ልጆች አዝ​ዛ​ለሁ፤ በክ​ብ​ሬም እቀ​ደ​ሳ​ለሁ። የም​ስ​ክ​ሩ​ንም ድን​ኳን መሠ​ዊ​ያ​ው​ንም እቀ​ድ​ሳ​ለሁ፤ በክ​ህ​ነ​ትም ያገ​ለ​ግ​ሉኝ ዘንድ አሮ​ን​ንና ልጆ​ቹን እቀ​ድ​ሳ​ለሁ። በእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች መካ​ከል እኖ​ራ​ለሁ፤ አም​ላ​ካ​ቸ​ውም እሆ​ና​ቸ​ዋ​ለሁ። በእ​ነ​ርሱ እጠራ ዘንድ፥ አም​ላ​ክም እሆ​ና​ቸው ዘንድ ከግ​ብፅ ምድር ያወ​ጣ​ኋ​ቸው አም​ላ​ካ​ቸው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እኔ እንደ ሆንሁ ያው​ቃሉ።

ዘፀአት 29:38-46 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“በየዕለቱ ያለ ማቋረጥ በመሠዊያው ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ ዓመት የሞላቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች፤ አንዱን ጠቦት በማለዳ፣ ሌላውን በማታ አቅርብ። ከመጀመሪያው የበግ ጠቦት ጋራ የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ ምርጥ ዱቄትን ተወቅጦ ከተጠለለ ሩብ ኢፍ ዘይት ጋራ ለውስና ሩብ ሂን ወይንን ደግሞ የመጠጥ መሥዋዕት በማድረግ አቅርብ። ሌላውን የበግ ጠቦት በማለዳው እንደ ቀረበው ተመሳሳይ ከሆነው የእህልና የመጠጥ መሥዋዕት ጋራ በማታ ሠዋው፤ ይህም ጣፋጭ መዐዛና ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው። “ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በሚመጡት ትውልዶች ዘወትር ይደረጋል፤ በዚያ እገናኝሃለሁ፤ እናገርሃለሁም፤ በዚያ ደግሞ ከእስራኤላውያን ጋራ እገናኛለሁ፤ ስፍራውም በክብሬ ይቀደሳል። “ስለዚህ የመገናኛው ድንኳንና መሠዊያውን እኔ እቀድሳለሁ፤ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ አሮንና ወንድ ልጆቹን እቀድሳለሁ። ከዚያም በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ። በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ከግብጽ ያወጣኋቸው እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ።

ዘፀአት 29:38-46 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በመሠዊያውም ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ በቀን በቀን ዘወትር ሁለት የዓመት ጠቦቶች ታቀርባለህ። አንዱን ጠቦት በማለዳ ቍርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ፤ ሁለተኛውንም ጠቦት በማታ ቍርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ። ከአንዱ ጠቦትም ጋር የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት፥ ደግሞ ለመጠጥ ቍርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ታቀርባለህ። ሁለተኛውንም ጠቦት በማታ ታቀርበዋለህ፥ እንደ ማለዳውም የእህልና የመጠጥ ቍርባን ታደርግበታለህ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽቱ እንዲሆን የእሳት ቍርባን ይሆናል። ለአንተ እናገር ዘንድ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ፥ በእግዚአብሔር ፊት ይህ ዘወትር ለልጅ ልጃችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል። ከእስራኤልም ልጆች ጋር በዚያ እገናኛለሁ፤ ድንኳኑም በክብሬ ይቀደሳል። የመገናኛውንም ድንኳን መሠዊያውንም እቀድሳለሁ፤ በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን እቀድሳለሁ። በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፥ አምላክም እሆናቸዋለሁ። በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው አምላካቸው እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝ።

ዘፀአት 29:38-46 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“በሚመጡት ዘመናት ሁሉ በየዕለቱ አንድ ዓመት የሆናቸው ሁለት ጠቦቶች መሥዋዕት አድርገህ በመሠዊያው ላይ ታቀርባለህ፤ ከጠቦቶቹ አንዱን ጠዋት ሌላውን ማታ ትሠዋለህ። ከመጀመሪያው ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ግራም ምርጥ የሆነ የስንዴ ዱቄት ከአንድ ሊትር ተጨምቆ የተጠለለ የወይራ ዘይት ጋር ለውሰህ አቅርብ፤ አንድ ሊትር የወይን ጠጅም መባ አድርገህ አፍስስበት። ሁለተኛውንም ጠቦት በምሽት ጊዜ መሥዋዕት አድርገህ አቅርብ፤ በማለዳው መሥዋዕት ባቀረብከውም መጠን ተመሳሳይ ዱቄት፥ ዘይትና ወይን ጠጅ አቅርብ፤ ይህ ለእኔ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የምግብ መባ ነው፤ መዓዛውም እኔን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ መቅረብ አለበት፤ እኔ ሕዝቤን የምገናኘውና አንተንም የማነጋግርበት ስፍራ ይኸው ነው። በዚህም ከሕዝቤ ከእስራኤል ጋር እገናኛለሁ፤ ክብሬም ይህን ስፍራ የተቀደሰ ያደርገዋል። እኔ መሠዊያውንና ድንኳኑን እቀድሳለሁ፤ በክህነት ያገለግሉኝም ዘንድ አሮንንና ልጆቹን እለያለሁ። በእስራኤል ሕዝብ መካከል እኖራለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ በመካከላቸው እኖር ዘንድ ከግብጽ ምድር መርቼ ያወጣኋቸው እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ።

ዘፀአት 29:38-46 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“በመሠዊያው ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ በየቀኑ ዘወትር ሁለት የአንድ ዓመት ጠቦቶች ታቀርባለህ። አንዱን ጠቦት ጠዋት ሁለተኛውን ጠቦት ደግሞ ማታ ታቀርበዋለህ። ከአንዱ ጠቦት ጋር አሥረኛ እጅ የኢፍ መስፈሪያ መልካም ዱቄት ከአራተኛ እጅ የኢን መስፈሪያ ተወቅጦ ከተጠለለ ዘይት ጋር የተለወሰ፥ ለመጠጥ ቁርባን የሚሆን ደግሞ አራተኛ እጅ የኢን መስፈሪያ የወይን ጠጅ ታቀርባለህ። ሁለተኛውን ጠቦት ደግሞ በማታ ታቀርበዋለህ፥ እንደ ጠዋቱም የእህልና የመጠጥ ቁርባን ከእርሱ ጋር ታቀርባለህ፤ ለጌታ መልካም መዓዛ የሚሆን የእሳት ቁርባን ይሆናል። ከአንተ ጋር ለመነጋገር በዚያ በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን መግቢያ፥ ይህ ዘወትር በትውልዶቻችሁ በጌታ ፊት የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል። በዚያም ከእስራኤል ልጆች ጋር እገናኛለሁ፤ በክብሬም የተቀደሰ ይሆናል። የመገናኛውን ድንኳንና መሠዊያውን እቀድሳለሁ፤ በክህነትም እንዲያገለግሉኝ አሮንንና ልጆቹን እቀድሳለሁ። በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ። በመካከላቸው እንድኖር ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው ጌታ አምላካቸው እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ ጌታ አምላካቸው ነኝ።”