ዘፀአት 25:16-22
ዘፀአት 25:16-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የምሰጥህንም ምስክር በታቦቱ ውስጥ አኑር። “ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ከንጹሕ ወርቅ ሥራለት። በስርየት መክደኛው ዳርና ዳር ላይ የሚሆኑ ከወርቅ የተቀረጹ ሁለት ኪሩቤል ሥራ። አንዱን ኪሩብ በአንደኛው፣ ሁለተኛውን ኪሩብ በሌላኛው ዳር አድርግ በሁለቱም ጫፎች ሁለቱን ኪሩቤል ከስርየት መክደኛው ጋራ አንድ ወጥ አድርገህ ሥራቸው። ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ በመዘርጋት የስርየት መክደኛውን በክንፎቻቸው ይሸፍኑ፤ እርስ በርሳቸው ትይዩ በመሆንም ፊታቸውን ወደ ስርየት መክደኛው ያድርጉ። የስርየት መክደኛውን በታቦቱ ዐናት ላይ አስቀምጠው፤ እኔ የምሰጥህን ምስክሩንም በታቦቱ ውስጥ አስቀምጥ። በምስክሩ ታቦት ላይ ባሉት በሁለቱ ኪሩቤል መካከል፣ በስርየት መክደኛው ላይ በዚያ እኔ ከአንተ ጋራ እገናኛለሁ፤ ለእስራኤላውያን የሚሆኑትን ትእዛዞቼንም እሰጥሃለሁ።
ዘፀአት 25:16-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ። ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ። ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፤ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ፤ ሁለቱንም ኪሩቤል እንዲሁ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፤ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፤ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይሁን። የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ። በዚያም እገለጥልሃለሁ፤ ለእስራኤል ልጆች የማዝዝህን ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ።
ዘፀአት 25:16-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ። ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ። ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ። ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ። የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ። በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ።
ዘፀአት 25:16-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህም በኋላ እኔ የምሰጥህን፥ ትእዛዞቹ የተጻፉባቸውን ሁለት ጽላቶች በታቦቱ ውስጥ አኑር። “ርዝመቱ መቶ ኻያ አምስት ሳንቲ ሜትር፥ የጐኑም ስፋት ሰባ አምስት ሳንቲ ሜትር የሆነም የስርየት መክደኛ ሥራለት። ከተቀጠቀጠም ወርቅ ክንፎች ያሉአቸው የሁለት ኪሩቤል ምስል ሥራ፤ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት በኩል በጫፍና በጫፍ አኑራቸው፤ እነርሱም ከክዳኑ ጋር አብረው የተሠሩ ይሁኑ። እነዚህም ክንፍ ያላቸው ኪሩቤል በመክደኛው ግራና ቀኝ ሆነው ፊት ለፊት የሚተያዩ ይሁኑ፤ በተዘረጉትም ክንፎቻቸው መክደኛውን ይሸፍኑት። በታቦቱ ላይ መክደኛውን አድርግ፤ የምሰጥህንም ጽላት በታቦቱ ውስጥ አኑረው፤ እኔም በዚያ ለአንተ እገለጥልሃለሁ፤ በመክደኛው ላይ በተሠሩት ክንፍ ባላቸው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል ሆኜ ለእስራኤል ሕዝብ የምታቀርበውን ትእዛዞቼን ሁሉ እሰጥሃለሁ።
ዘፀአት 25:16-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እኔ የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ አኑር። ከንጹሕ ወርቅ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ። ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። አንዱን ኪሩብ በአንድ በኩል፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው በኩል አኑር፥ በስርየት መክደኛው ላይ ኪሩቤል በሁለት በኩል ላይ ታደርጋቸዋለህ። ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ። የስርየት መክደኛውን በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔ የምሰጥህንም ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ። በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች እንድታዝዝ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛው ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ።