ኦሪት ዘጸአት 25
25
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2ስጦታ ያመጡልኝ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ በገዛ እጁ ሊሰጠኝ በልቡ ከሚያምረው ሰው ሁሉ መባ ተቀበሉ። 3ከእነርሱም የምትቀበሉት መባ ይህ ነው፤ 4ወርቅ፥ ብር፥ ናስም፥ ሰማያዊና ሐምራዊ ቀይም ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም፥ 5የፍየልም ጠጉር፥ ቀይ የአውራ በግ ቁርበት፥ የአስቆጣ ቁርበት፥ የግራርም እንጨት፥ 6የመብራትም ዘይት፥ ለቅብዓት ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን ቅመም፥ 7መረግድም፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ። 8በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ። 9እኔ እንደማሳይህ ሁሉ፥ እንደ ማደሪያው ምሳሌ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ፥ እንዲሁ ሥሩት። 10ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። 11በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት። 12አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፥ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር፤ በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላው ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ። 13መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሥራ፥ በወርቅም ለብጣቸው። 14ለታቦቱ መሸከሚያ በታቦቱ ጎን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አግባ። 15መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፥ ከቶም አይውጡ። 16በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ። 17ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ። 18ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። 19ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ። 20ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ። 21የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ። 22በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ። 23ርዝመቱም ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ፥ ቁመቱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ገበታ ከግራር እንጨት ሥራ። 24በጥሩም ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አድርግለት፤ 25በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አድርግለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አድርግለት። 26አራትም የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አድርግ። 27ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶቹ በክፈፉ አቅራቢያ ይሁኑ። 28ገበታውን ይሸከሙባቸው ዘንድ መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው። 29ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ ወጭቶችዋን ጭልፋዎችዋንም መቅጃዎችዋንም ጽዋዎችዋንም አድርግ፤ እነርሱንም ከጥሩ ወርቅ አድርጋቸው። 30በገበታም ላይ የገጽ ኅብስት ሁልጊዜ በፊቴ ታደርጋለህ። 31መቅረዝንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ፤ መቅረዙ ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀጠቀጠ ሥራ ይደረግ፤ ጽዋዎቹም ጕብጕቦቹም አበቦቹም አንድነት በእርሱ ይደረጉበት። 32በስተጎኑ ስድስት ቅርንጫፎች ይውጡለት፤ ሦስት የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስትም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ይውጡ። 33በአንደኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕብና አበባ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕብና አበባ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፤ እንዲሁም ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አድርግ። 34በመቅረዙም ጕብጕቦቹንና አበቦቹን አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አድርግ። 35ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ ይሁን። 36ጕብጕቦቹና ቅርንጫፎቹ ሁሉ ከእርሱ ጋር አንድ ይሁኑ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ይደረግ። 37ሰባቱንም መብራቶች ሥራ፤ በፊቱ ያበሩ ዝንድ መብራቶቹን ያቀጣጥሉአቸዋል። 38መኮስተሪያዎችዋን የኩስታሪ ማድረጊያዎችዋንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ። 39መቅረዙም ዕቃውም ሁሉ ከአንድ መክሊት ጥሩ ወርቅ ይሠሩ። 40በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 25: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ