የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 26

26
1ደግሞም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ የተሠሩ አሥር መጋረጆች ያሉበትን ማደሪያ ሥራ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእነርሱ ላይ ይሁኑ። 2የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን፤ የመጋረጆቹ ሁሉ መጠን ትክክል ይሁን። 3አምስቱ መጋረጆች እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ፤ አምስቱም መጋረጆች እንዲሁ እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ። 4ከሚጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ የሰማያዊውን ግምጃ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞም ከተጋጠሙት ከሌሎች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አድርግ። 5አምሳ ቀለበቶችን በአንድ መጋረጃ አድርግ፥ አምሳውንም ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ አድርግ፤ ቀለበቶቹ ሁሉ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት ይሆናሉ። 6አምሳ የወርቅ መያዣዎች ሥራ፤ ማደሪያውንም አንድ እንዲሆን መጋረጆችን እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጥማቸው። 7ከማደሪያውም በላይ ለድንኳን የሚሆኑ መጋረጆች ከፍየል ጠጉር አድርግ፤ አሥራ አንድ መጋረጆች ታደርጋለህ። 8እያንዳንዱም መጋረጃ ርዝመቱ ሠላሳ ክንድ፥ እያንዳንዱም መጋረጃ ወርዱ አራት ክንድ ይሁን፤ የአሥራ አንዱም መጋረጆች መጠናቸው ትክክል ይሁን። 9አምስቱ መጋረጆች አንድ ሆነው ይጋጠሙ፥ ስድስቱም መጋረጆች እርስ በርሳቸው አንድ ሆነው ይጋጠሙ፤ ስድስተኛውም መጋረጃ በድንኳኑ ፊት ይደረብ። 10ከተጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አምሳ ቀለበቶች አድርግ። 11አምሳ የናስ መያዣዎችን ሥራ፥ መያዣዎችንም ወደ ቀለበቶች አግባቸው፥ ድንኳኑም አንድ እንዲሆን አጋጥመው። 12ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ በማደሪያው ጀርባ ይንጠልጠል። 13ማደሪያውን እንዲሸፍን ከርዝመቱ በአንድ ወገን አንድ ክንድ፥ በአንድ ወገንም አንድ ክንድ ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረው ትርፍ በማደሪያው ውጭ በወዲህና በወዲያ ይንጠልጠል። 14ለድንኳኑም መደረቢያ ከቀይ አውራ በግ ቁርበት፥ ከዚያም በላይ ሌላ መደረቢያ ከአስቆጣ ቁርበት አድርግ። 15ለማደሪያውም የሚቆሙትን ሳንቆች ከግራር እንጨት አድርግ። 16የሳንቃውም ሁሉ ርዝመቱ አሥር ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። 17ለእያንዳንዱም ሳንቃ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያያይዙ ሁለት ማጋጠሚያዎች ይሁኑለት፤ ለማደሪያው ሳንቆች ሁሉ እንዲሁ አድርግ። 18ለማደሪያውም በደቡብ ወገን ሀያ ሳንቆችን አድርግ። 19ከሀያውም ሳንቆች በታች አርባ የብር እግሮችን አድርግ፤ ከእያንዳንዱ ሳንቃ በታች ለሁለት ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ይሁኑ። 20ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሀያ ሳንቆች፥ 21ለእነርሱም አርባ የብር እግሮች ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሁኑ። 22ለማደሪያውም በምዕራቡ ወገን በስተ ኋላ ስድስት ሳንቆችን አድርግ። 23ለማደሪያውም ለሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቆችን አድርግ። 24ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንዱ ሳንቃ ድርብ ይሁን፤ እንዲሁም ለሁለቱ ይሁን፤ እነርሱም ለሁለቱ ማዕዘን ይሆናሉ። 25ስምንት ሳንቆችና አሥራ ስድስት የብር እግሮቻቸው ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሆናሉ። 26ከግራርም እንጨት በማደሪያው በአንድ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ 27በማደሪያውም በሁለተኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ በማደሪያውም በስተ ኋላ በምዕራብ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች አድርግ። 28መካከለኛውም መወርወሪያ በሳንቆች መካከል ከዳር እስከ ዳር ይለፍ። 29ሳንቆቹንም በወርቅ ለብጣቸው፤ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያ ቤት እንዲሆኑላቸው ከወርቅ ሥራቸው፤ መወርወሪያዎችንም በወርቅ ለብጣቸው። 30ማደሪያውንም በተራራ እንዳሳየሁህ ምሳሌ አቁም። 31መጋረጃውንም ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም አድርግ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእርሱ ላይ ይሁኑ። 32በወርቅ በተለበጡት ከግራር እንጨትም በተሠሩት በአራቱ ምሰሶች ላይ ስቀለው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ፥ አራቱም እግሮቻቸው ከብር የተሠሩ ይሁኑ። 33መጋረጃውንም ከመያዣዎቹ በታች ታንጠለጥለዋለህ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የምስክርን ታቦት አግባው፤ መጋረጃውም በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል መለያ ይሁናችሁ። 34በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ የስርየት መክደኛውን በምስክሩ ታቦት ላይ አድርግ። 35ገበታውንም በመጋረጃው ውጭ፥ መቅረዙንም በገበታው ፊት ለፊት በማደሪያው በደቡብ ወገን አድርግ፤ ገበታውንም በሰሜን ወገን አድርገው። 36ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ መጋረጃ አድርግለት። 37ለመጋረጃውም አምስት ምሰሶች ከግራር እንጨት አድርግ፥ በወርቅም ለብጣቸው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ይሁኑ፤ አምስትም እግሮች አድርግላቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ