የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 27

27
1ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ መሠዊያ ከግራር እንጨት አድርግ፤ አራት ማዕዘንም ይሁን፤ ከፍታውም ሦስት ክንድ ይሁን። 2በአራቱም ማዕዘን ቀንዶችን ታደርጋለህ፥ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ይሁኑ፤ በናስም ለብጠው። 3አመድ የሚሆንባቸውን ምንቸቶች፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦቹንም፥ ማንደጃዎቹንም አድርግ፤ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አድርግ። 4እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የናስ መከታ አድርግለት፤ ለመከታውም አራት የናስ ቀለበት በአራት ማዕዘኑ አድርግለት። 5መከታውም እስከ መሠዊያው እኵሌታ ይደርስ ዘንድ መሰዊያው በሚዞረው በእርከኑ ታች አድርገው። 6ለመሠዊያውም ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሠርተህ በናስ ለብጣቸው። 7መሎጊያዎቹም በቀለበቶች ውስጥ ይግቡ፤ መሠዊያውንም ስትሸከሙ መሎጊያዎቹ በሁለቱ ወገኖች ይሁኑ። 8ከሳንቆች ሠርተህ ባዶ አድርገው፤ በተራራው እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንዲሁ ያድርጉት። 9የማደሪያውንም አደባባይ ሥራ፤ በደቡብ ወገን የጥሩ በፍታ መጋረጆች ይሁኑለት፥ የአንዱም ወገን ርዝመት መቶ ክንድ ይሁን፤ 10ከናስ የተሠሩ ሀያ ምሰሶችና ሀያ እግሮች ይሁኑለት፤ የምሶሶቹም ኩላቦችና ዘንጎች የብር ይሁኑ። 11እንዲሁም በሰሜን ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ ከናስ የተሠሩ ሀያ ምሶሶች ሀያም እግሮች ይሁኑ፤ ለምሰሶችም የብር ኩላቦችና ዘንጎች ይሁኑ። 12በምዕራብም ወገን ለአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ አሥርም ምሰሶች፥ አሥርም እግሮች ይሁኑለት። 13በምሥራቅም ወገን የአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ይሁን። 14በአንድም ወገን የመጋረጆቹ ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ ይሁን፤ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁኑ። 15በሌላውም ወገን የመጋረጆች ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ ይሆናል፤ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁኑ። 16ለአደባባዩም ደጅ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ ሀያ ክንድ መጋረጃ ይሆናል፤ ምሰሶቹም አራት፥ እግሮቹም አራት ይሁኑ። 17በአደባባዩም ዙሪያ ላሉት ምሰሶች ሁሉ የብር ዘንጎች፥ የብርም ኩላቦች፥ የናስም እግሮች ይሁኑላቸው። 18የአደባባዩ ርዝመት መቶ ክንድ ስፋቱም አምሳ ክንድ ይሁን፥ የመጋረጃውም ከፍታ አምስት ክንድ ይሁን፤ መጋረጃውም ከጥሩ በፍታ፥ እግሮቹም ከናስ የተሠሩ ይሁኑ። 19ለማገልገል ሁሉ የማደሪያው ዕቃ ሁሉ፥ ካስማዎቹም ሁሉ የአደባባዩም ካስማዎች ሁሉ፥ የናስ ይሁኑ። 20አንተም መብራቱን ሁልጊዜ ያበሩት ዘንድ ለመብራት ተወቅጦ የተጠለለ ጥሩ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። 21በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ታቦት ፊት ባለው መጋረጃ ውጭ አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት እንዲበራ ያሰናዱት፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ለልጅ ልጃቸው የዘላለም ሥርዓት ይሁን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ