ዘፀአት 23:1-9
ዘፀአት 23:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል፤ የዐመፅ ምስክርም ትሆን ዘንድ ከዐመፀኛ ጋር አትቀመጥ። ለዐመፅ ከብዙ ሰው ጋር አንድ አትሁን፤ ፍርድንም ለማጣመም ከብዙ ሰው ጋር አትጨመር። በፍርድ ለድሀው አትራራ። “የጠላትህን በሬ ወይም አህያውን ጠፍቶ ብታገኘው ፈጽሞ መልስለት። የጠላትህን አህያ ከጭነቱ በታች ወድቆ ብታገኘው አትለፈው፤ ነገር ግን ከእርሱ ጋር ለማንሣት ርዳው። “በፍርድ የድሀውን ፍርድ አታጣምም። ከዐመፅ ፍርድ ሁሉ ራቅ፤ በደል የሌለበትንና ጻድቅን አትግደል፤ ኀጢአተኛውንም በመማለጃ አታድን፤ መማለጃን አትቀበል፤ መማለጃ የዐይናማዎችን ዐይን ያሳውራልና፥ እውነተኛ ቃልንም ያጣምማልና። በስደተኛው ግፍ አታድርጉ፤ እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ስለ ነበራችሁ የስደተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች ዐውቃችኋልና።
ዘፀአት 23:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“የሐሰት ወሬ አትንዛ፤ ተንኰል ያለበትን ምስክርነት በመስጠት ክፉውን ሰው አታግዝ። “ክፉ በማድረግ ብዙዎችን አትከተል፤ በሕግ ፊት ምስክርነት ስትሰጥ፣ ከብዙዎቹ ጋራ ተባብረህ ፍትሕ አታጣምም። በዳኝነት ጊዜ ለድኻው አታድላ። “የጠላትህ በሬ ወይም አህያ ሲባዝን ብታገኘው ወደ እርሱ መልሰው። የሚጠላህ ሰው አህያ፣ ጭነት ከብዶት ወድቆ ብታየው ርዳው እንጂ ትተኸው አትሂድ። “በዳኝነት ጊዜ በድኻው ላይ ፍርድ አታጓድልበት። ከሐሰት ክስ ራቅ፤ በደል የሌለበትን ወይም ጻድቁን ሰው ለሞት አሳልፈህ አትስጥ፣ በደለኛውን ንጹሕ አላደርግምና። “ጕቦ አትቀበል፤ ጕቦ አጥርተው የሚያዩትን ሰዎች ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። “መጻተኛውን አትጨቍን፤ በግብጽ መጻተኛ ስለ ነበራችሁ፣ መጻተኛ ምን እንደሚሰማው እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና።
ዘፀአት 23:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል፤ ሐሰተኛ ምስክርም ትሆን ዘንድ ከኃጢአተኛ ጋር እጅህን አታንሣ። ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድንም ለማጥመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር። በፍርድ ነገርም ለድሀው አታድላ። የጠላትህን በሬ ወይም አህያውን ጠፍቶ ብታገኘው በፍጹም መልስለት። የሚጠላህን ሰው አህያ ከሸክሙ በታች ወድቆ ብታየው አትተወው፥ ነገር ግን ከእርሱ ጋር አንሣው። በሚምዋገትበት ጊዜ የድሀህን ፍርድ አታጥምም። ከሐሰት ነገር ራቅ፤ እኔ ኃጢአተኛውን አላጸድቅምና ንጹሕንና ጻድቅን አትግደል። ማማለጃን አትቀበል፤ ማማለጃ የዓይናማዎችን ሰዎች ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። በስደተኛው ግፍ አታድርጉ፤ እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ስለ ነበራችሁ የስደተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች አውቃችኋልና።
ዘፀአት 23:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ሐሰተኛ ወሬ አታሠራጭ፤ በሐሰት በመመስከርም ከወንጀለኛ ሰው ጋር አትተባበር፤ ክፉ ለማድረግ የተሰባሰቡ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድን ለማጣመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር። ድኻ ለፍርድ ቢቀርብ ድኽነቱን በማየት አድልዎ አታድርግለት። “የጠላትህ በሬ ወይም አህያ ጠፍቶ ብታገኝ መልስለት። የሚጠላህ ሰው አህያ ከጭነቱ ክብደት የተነሣ ወድቆ ብታገኝ፥ አህያውን ከወደቀበት ለማንሣት እንዲችል እርዳው እንጂ አልፈኸው አትሂድ። “በፍርድ አደባባይ አድልዎ በማድረግ የድኻውን ፍርድ አታጣምበት፤ ማንንም በሐሰት አትክሰስ፤ ንጹሑንም ሰው በሞት አትቅጣ፤ እንደዚህ ያለ በደል የሚፈጽመውን ሰው ከቅጣት ነጻ አላደርገውም፤ ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ነገር እንዳያዩ ዐይናቸውን ስለሚያሳውርና የንጹሕ ሰዎችንም ፍርድ ስለሚያጣምም ጉቦ አትቀበል። “እናንተ በግብጽ ምድር መጻተኞች ስለ ነበራችሁ መጻተኛ ምን ዐይነት ሐዘን እንደሚደርስበት ታውቃላችሁና መጻተኛውን አታጒላሉ።”
ዘፀአት 23:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ሐሰተኛ ወሬ አታሰራጭ፥ ሐሰተኛ ምስክር ለመሆንም ከኃጢአተኛ ጋር አትተባበር። ክፉ ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድንም ለማጣመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር። በፍርዱ ጊዜ ለድሀው አታድላ። የጠላትህን በሬ ወይም አህያ ጠፍቶ ብታገኘው ለእርሱ መልስለት። የሚጠላህን ሰው አህያ ከሸክሙ በታች ወድቆ ብታየው አትተወው፥ ነገር ግን እንዲነሳ እርዳው። በፍርዱ ጊዜ የድሀውን ፍርድ አታጥምም። ከሐሰት ነገር ራቅ፤ ንጹሑንና ጻድቁን አትግደል፥ እኔ ኃጢአተኛውን አላጸድቅምና። ጉቦን አትቀበል፤ ጉቦ የሚያዩ ሰዎችን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። መጻተኛውን አትጨቁን፤ እናንተ ራሳችሁ በግብጽ ምድር መጻተኞች ስለ ነበራችሁ የመጻተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች ታውቃላችሁና።