ኦሪት ዘጸአት 23
23
ትክክለኛ ፍርድ
1“ሐሰተኛ ወሬ አታሠራጭ፤ በሐሰት በመመስከርም ከወንጀለኛ ሰው ጋር አትተባበር፤ #ዘፀ. 20፥16፤ ዘሌ. 19፥11-12፤ ዘዳ. 5፥20። 2ክፉ ለማድረግ የተሰባሰቡ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድን ለማጣመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር። 3ድኻ ለፍርድ ቢቀርብ ድኽነቱን በማየት አድልዎ አታድርግለት። #ዘሌ. 19፥15።
4“የጠላትህ በሬ ወይም አህያ ጠፍቶ ብታገኝ መልስለት። 5የሚጠላህ ሰው አህያ ከጭነቱ ክብደት የተነሣ ወድቆ ብታገኝ፥ አህያውን ከወደቀበት ለማንሣት እንዲችል እርዳው እንጂ አልፈኸው አትሂድ። #ዘዳ. 22፥1-4።
6“በፍርድ አደባባይ አድልዎ በማድረግ የድኻውን ፍርድ አታጣምበት፤ 7ማንንም በሐሰት አትክሰስ፤ ንጹሑንም ሰው በሞት አትቅጣ፤ እንደዚህ ያለ በደል የሚፈጽመውን ሰው ከቅጣት ነጻ አላደርገውም፤ 8ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ነገር እንዳያዩ ዐይናቸውን ስለሚያሳውርና የንጹሕ ሰዎችንም ፍርድ ስለሚያጣምም ጉቦ አትቀበል። #ዘሌ. 19፥15፤ ዘዳ. 16፥19፤ 23፥9፤ ዘፀ. 22፥21፤ ዘሌ. 19፥33-34፤ ዘዳ. 24፥17-18፤ 27፥19።
9“እናንተ በግብጽ ምድር መጻተኞች ስለ ነበራችሁ መጻተኛ ምን ዐይነት ሐዘን እንደሚደርስበት ታውቃላችሁና መጻተኛውን አታጒላሉ።”
ሰባተኛው ዓመትና ሰባተኛው ቀን
10“ስድስት ዓመት እርሻህን በማረስ ዘርተህ፥ ምርትህን ሰብስብ፤ 11በሰባተኛው ዓመት ግን በሕዝብህ መካከል የሚገኙ ድኾች ምግብ ያገኙ ዘንድ በምድሪቱ ላይ ምንም ነገር አታምርት፤ ምድሪቱ ታርፍ ዘንድ ተዋት፤ ከእነርሱ የተረፈውንም የምድር አራዊት ይመገቡት፤ የወይን ተክል ቦታህንና የወይራ ዘይት ዛፎችህንም እንደዚሁ አሳርፋቸው። #ዘሌ. 25፥1-7።
12“በሳምንት ስድስት ቀን ሥራህን ሁሉ ሥራ፤ በሰባተኛው ቀን ግን ምንም ሥራ አትሥራበት፤ በዚህ ዐይነት አገልጋዮችህና ለአንተ የሚሠሩ መጻተኞች፥ እንዲሁም በሬህና አህያህ ዕረፍት አድርገው ይዋሉ። #ዘፀ. 20፥9-11፤ 31፥15፤ 34፥21፤ 35፥2፤ ዘሌ. 23፥3፤ ዘዳ. 5፥13-14።
13“እኔ እግዚአብሔር የነገርኳችሁን ሁሉ በጥንቃቄ አድምጡ፤ ወደ ሌሎች አማልክት አትጸልዩ፤ ሌላው ቀርቶ ስማቸውን እንኳ አትጥሩ።
ሦስቱ ታላላቅ በዓላት
(ዘፀ. 34፥18-26፤ ዘዳ. 16፥1-17)
14“እኔን የምታከብሩባቸው በዓመት ሦስት በዓላት ይኑሩአችሁ፤ 15ከግብጽ በወጣችሁበት በአቢብ ወር፥ እኔ ባዘዝኳችሁ አኳኋን የቂጣን በዓል አክብሩ፤ ይህ በዓል በሚከበርባቸው በሰባቱ ቀኖች ውስጥ እርሾ የነካው እንጀራ አትብሉ፤ ለእኔ ልትሰግዱ በምትመጡበት ጊዜ መባ ሳትይዙ አትምጡ። #ዘፀ. 12፥14-20፤ ዘሌ. 23፥6-8፤ ዘኍ. 28፥17-25።
16“የምድራችሁን ሰብል በምትሰበስቡበት ጊዜ የመከር በዓል አክብሩ፤ #ዘሌ. 23፥15-21፤39-43፤ ዘኍ. 28፥26-31።
“ከወይን ተክሎቻችሁና ከፍራፍሬ ዛፎቻችሁ ፍሬ በምትሰበስቡበት ጊዜ በዓመቱ መጨረሻ የዳስ በዓል አክብሩ፤ 17በዓመት ሦስት ጊዜ እነዚህ በዓላት በሚከበሩባቸው ቀኖች ወንዶች ሁሉ ወደ እኔ ወደ አምላካቸው ይምጡ።
18“እንስሳ በምትሠዉልኝ ጊዜ እርሾ የነካው እንጀራ መባ አድርጋችሁ አታቅርቡ፤ በእነዚህ በዓላት የሚሠዉት እንስሶች ስብ ለሚቀጥለው ቀን አይትረፍ።
19“በየዓመቱ ከምታመርቱት ምርት መጀመሪያ የደረሰውን በኲራት ወደ እኔ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጡ። #ዘፀ. 34፥26፤ ዘዳ. 14፥21፤ 26፥2።
“የበግን ወይም የፍየልን ግልገል በእናቱ ወተት አትቀቅል።
የተስፋ ቃሎችና መመሪያዎች
20“በመንገድህ እንዲጠብቅህና እኔ ወዳዘጋጀሁልህ ምድር በሰላም እንዲያስገባህ በፊትህ የሚሄድ መልአክ እልካለሁ፤ 21የሚነግርህን በማዳመጥ ለእርሱ ታዘዝ፤ በእርሱም ላይ አታምፅ፤ ለእርሱ ሙሉ ሥልጣን የሰጠሁት ስለ ሆነ የምትፈጽመውን ዐመፅ እየተመለከተ ይቅርታ አያደርግልህም። 22ለእርሱ ብትታዘዝና እኔ ያዘዝኩህንም ሁሉ ብትፈጽም ጠላቶችህን እጠላለሁ፤ ተቃዋሚዎችህንም እዋጋለሁ፤ 23መልአኬም ፊት ፊትህ በመሄድ ወደ አሞራውያን፥ ሒታውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ከነዓናውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ይወስድሃል፤ እኔም እነርሱን አጠፋቸዋለሁ። 24ለእነርሱ አማልክት በመንበርከክ አትስገድ፤ አታምልካቸው፤ ሃይማኖታዊ ልማዶቻቸውንም አትከተል፤ አማልክታቸውን አጥፋ፤ ለእነርሱ ቅዱሳን የሆኑትን የድንጋይ ዐምዶቻቸውንም አፈራርስ፤ 25ለእኔ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ብትሰግድ በቂ ምግብና ውሃ በመስጠት እባርክሃለሁ፤ በሽታህንም ሁሉ አስወግዳለሁ። 26በምድርህ ፅንስ የሚያስወርዳት ወይም መኻን ሴት አትኖርም፤ ዕድሜህንም አረዝመዋለሁ።
27“አንተን የሚቃወሙህ ሁሉ እኔን እንዲፈሩ አደርጋለሁ፤ በአንተ ላይ ጦርነት በሚያስነሡ ሕዝቦች ላይ ሁከት አመጣለሁ፤ ጠላቶችህ ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲሸሹ አደርጋለሁ፤ 28በጠላቶችህ ላይ ሽብር እልክባቸዋለሁ። አንተም ወደ ፊት ስትሄድ ሒዋውያንን፥ ከነዓናውያንንና ሒታውያንን ከፊትህ አባርራለሁ። #23፥28 ሽብር፦ ወይም “ተርብ” 29ሆኖም በአንድ ዓመት ውስጥ እንዲጠፉ አላደርግም፤ ይህን ካደረግሁ ምድሪቱ ሰው አልባ ትሆናለች፤ አራዊትም ይበዙብሃል፤ 30ስለዚህ በዚህ ፈንታ በቊጥር በዝተህ ምድሪቱን እስክትወርስ ድረስ ጥቂት በጥቂት አስወጣልሃለሁ። 31የምድርህንም ወሰን ከቀይ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፥ ከምድረ በዳው እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ እንዲሰፋ አደርጋለሁ፤ በምድሪቱ የሚኖሩትን በእጅህ እጥላለሁ፤ ከፊትህም ታሳድዳቸዋለህ። #23፥31 ቀይ ባሕር፦ እዚህ ላይ የሚያመለክተው የቀይ ባሕርን ሰሜን ምሥራቅ ክፍል እንደ መሆኑ በአሁኑ ጊዜ በዐቃባ የባሕር ሰላጤነት የታወቀው ነው። 32ከእነርሱም ሆነ ከአማልክታቸው ጋር ምንም ዐይነት ስምምነት አታድርግ፤ 33እነዚያ ሕዝቦች በአገርህ እንዲኖሩ አትፍቀድላቸው፤ የምትፈቅድላቸው ከሆነ ግን ኃጢአት በመሥራት እኔን እንድትበድል ያደርጉሃል፤ ለአማልክቶቻቸውም ብትሰግድ ለሞት የሚያደርስ ወጥመድ ይሆንብሃል።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 23: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997