ኦሪት ዘጸአት 22
22
የንብረት አጠባበቅ ሕግ
1“አንድ ሰው አንድ በሬ ወይም አንድ በግ ሰርቆ ቢያርድ ወይም ቢሸጥ ስለ አንድ በሬ አምስት በሬዎች፥ ስለ አንድ በግ አራት በጎች ይክፈል።
2-3ሌባው የሰረቀውን ይመልስ፤ የሚከፍለው ቢያጣ በባሪያነት ይሸጥ፤ የሰረቀው እንስሳ ላምም ቢሆን፥ አህያም ቢሆን፥ ወይም በግ ቢሆንና በሕይወት በእጁ ቢገኝ ለያንዳንዱ እንስሳ እጥፍ ዋጋ ይክፈል።
“አንድ ሌባ ቤት ሰብሮ ሲገባ ቢያዝና ተመትቶ ቢገደል ተከላካዩ ለደሙ ተጠያቂ አይሆንም። ሌባው ሰብሮ የገባው ፀሐይ ከወጣ በኋላ ሆኖ ተመትቶ ቢገደል ግን ተከላካዩ ለደሙ ተጠያቂ ይሆናል።
4የሰረቀው እንስሳ ላምም ቢሆን፥ አህያም ቢሆን፥ ወይም በግ ቢሆንና በሕይወት ቢገኝ ለያንዳንዱ ዕጥፍ ዋጋ ይክፈል።
5“አንድ ሰው እንስሶቹ በመስክ ወይም በወይን ተክል ቦታ አሰማርቶ ሳለ እንስሶቹ ወደ ሌላ ሰው እርሻ ገብተው ሰብሉን ቢበሉት ከራሱ ማሳ ወይም የወይን ተክል ቦታ ከሚያገኘው ምርት ካሣ ይክፈል።
6“አንድ ሰው በእርሻው ውስጥ እሳት ቢያቀጣጥልና እሳቱ በቊጥቋጦ ተላልፎ ወደ ሌላው ሰው እርሻ በመዛመት በማደግ ላይ ያለውንም ሆነ ታጭዶ የተከመረውን እህል ቢያቃጥል፥ እሳቱን ያቀጣጠለው ሰው ካሣ ይክፈል።
7“አንድ ሰው የሌላውን ሰው ገንዘብ ወይም የከበረ ዕቃ በዐደራ ለመጠበቅ ተስማምቶ ከቤቱ ተሰርቆበት ሌባው ቢገኝ እጥፍ አድርጎ ይክፈል። 8ሌባው ካልተገኘ ግን ዕቃውን በዐደራ የተቀበለው ሰው የእግዚአብሔር አገልጋዮች በሆኑ ዳኞች ፊት ቀርቦ የዚያን ሰው ንብረት አለመስረቁን በመሐላ ያረጋግጥ።
9“ስለ ከብት፥ ስለ አህያ፥ ስለ በግ ስለ ልብስና ወይም ስለ ማንኛውም የጠፋ ዕቃ ሁለት ሰዎች ቢካሰሱ፥ ስለ ንብረቱ ባለቤትነት የተጣሉት ሁለቱ ሰዎች የእግዚአብሔር አገልጋዮች በሆኑ ዳኞች ፊት ይቅረቡ፤ እግዚአብሔር በደሉን በዳኞቹ አማካይነት የሚገለጥበት ሰው፥ ለተበደለው ሰው ዕጥፍ አድርጎ ይክፈል።
10“አንድ ሰው የሌላውን ሰው አህያ፥ ላም፥ በግ ወይም ማንኛውንም እንስሳ በዐደራ ቢያስቀምጥና እንስሳው ቢሞት ወይም ቢሰበር ወይም ተዘርፎ ቢወሰድ፥ ምስክር ከሌለው፥ 11ያ ሰው የእግዚአብሔር አገልጋዮች ወደሆኑት ዳኞች ዘንድ ይሂድ፤ የሰውዬውን እንስሳ አለመስረቁንም በመሐላ ያረጋግጥ፤ እንስሳው ያልተሰረቀ ከሆነ የእንስሳው ባለቤት ካሳ አይጠይቅ፤ እንስሳው የጠፋበትም ሰው ካሳ አይክፈል። 12እንስሳው የተሰረቀ ከሆነ ግን ለባለቤቱ ይመለስለት፤ 13እንስሳውን አውሬ በልቶት ከሆነ ሰውየው የአውሬውን ትራፊ ለማስረጃ ያቅርብ፤ አውሬ ስለ ገደለውም እንስሳ ካሳ አይክፈል።
14“አንድ ሰው ከሌላው ሰው እንስሳ በውሰት ወስዶ ባለቤቱ በሌለበት እንስሳው ቢሞት ወይም ቢሰበር በውሰት ለሰጠው ሰው ካሳ ይክፈል፤ 15ነገር ግን ይህ የሆነው ባለንብረቱ ባለበት ከሆነ ሰውየው ካሳ መክፈል የለበትም፤ በኪራይ መልክ የወሰደው ከሆነ የተከፈለው ገንዘብ ጒዳቱን ያካክሳል።
የሥነ ምግባርና የእምነት ኅጎች
16“አንድ ሰው አንዲት ልጃገረድን አታሎ ክብረ ንጽሕናዋን ቢደፍር ማጫ ሰጥቶ ያግባት፤ 17የልጅትዋ አባት ሊድርለት ባይፈቅድ ግን ከአንድ ልጃገረድ ማጫ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የገንዘብ ካሣ ለልጅትዋ አባት ይክፈል። #ዘዳ. 22፥28-29።
18“አስማት የምታደርግ መተተኛ ሴት ብትኖር በሞት ትቀጣ፤ #ዘዳ. 18፥10-11።
19“ከእንስሳ ጋር ተገናኝቶ የሚረክስ ሰው በሞት ይቀጣ። #ዘዳ. 20፥15-16፤ ዘዳ. 27፥21።
20“ለእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ለሌላ ለማንኛውም አምላክ መሥዋዕት የሚያቀርብ በሞት ይቀጣ።
21“እናንተም በግብጽ ምድር መጻተኞች ስለ ነበራችሁ መጻተኛውን በመጨቈን አታጒላሉ፤ #ዘፀ. 23፥9፤ ዘሌ. 19፥33-34፤ ዘዳ. 24፥17-18፤ 27፥19። 22ባልዋ የሞተባትን መበለት ወይም አባትና እናት የሞቱበትን ድኻ ዐደግ አታጒላሉ። 23ይህን ብታደርጉ ወደ እኔ ሲጮኹ እኔ እግዚአብሔር ጩኸታቸውን በእርግጥ እሰማለሁ። 24በእናንተም ላይ ተቈጥቼ በጦርነት እንድታልቁ አደርጋለሁ፤ ሚስቶቻችሁ ባል አልባ፥ ልጆቻችሁም አባት አልባ ሆነው ይቀራሉ።
25“በድኽነት ከሚኖሩት ሕዝቤ መካከል ለአንዱ እንኳ ገንዘብ ብታበድር፥ እንደ ገንዘብ አበዳሪ በመሆን ወለድ ጨምሮ እንዲከፍልህ አትጠይቀው። #ዘሌ. 25፥35-38፤ ዘዳ. 15፥7-11፤ 23፥19-20። 26ልብሱን በመያዣ ስም የወሰድክበት ሰው ቢኖር ፀሐይ ከመጥለቅዋ በፊት መልስለት። 27ብርድ የሚከላከልበት ሌላ ምንም ልብስ ስለሌለው ምን ለብሶ ሊያድር ይችላል? እኔ መሐሪ ስለ ሆንኩ እርሱ ወደ እኔ ቢጮኽ እሰማዋለሁ። #ዘዳ. 24፥10-13።
28“በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል አትናገር፤ የሕዝብህንም መሪ አትስደብ። #22፥28 በእግዚአብሔር፦ ወይም “በፈራጆች” #ሐ.ሥ. 23፥5።
29“የእህልህን፥ የወይን ጠጅህንና የወይራ ዘይትህን በኲራት ለእኔ አቅርብ፤
“በኲር ሆነው የተወለዱትን ወንዶች ልጆችህን ለእኔ አቅርብ። 30ከቀንድ ከብቶችህ፥ ከበጎችህም በኲር ሆነው የሚወለዱትን ለእኔ አቅርብ፤ ይኸውም በኲር ሆኖ የተወለደ ወንድ ሁሉ ለሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቈይ፤ በስምንተኛው ቀን ለእኔ ታቀርበዋለህ።
31“እናንተ ለእኔ የተለያችሁ ሰዎች ትሆኑልኛላችሁ፤ ስለዚህ አውሬ በሜዳ የገደለውን የማንኛውንም እንስሳ ሥጋ አትብሉ፤ ለውሾች ጣሉት። #ዘሌ. 17፥15።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 22: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997