ኦሪት ዘጸአት 24
24
እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባውን ቃል ኪዳን አጸና
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተ ራስህ፥ አሮን፥ ናዳብ፥ አቢሁና ከእስራኤል መሪዎች ሰባ የሚሆኑት ጭምር እኔ ወዳለሁበት ተራራ ውጡ፤ በሩቅ ሳላችሁም ተንበርክካችሁ ስገዱ፤ 2ሙሴ ብቻ ወደ እኔ ይቅረብ፤ እነርሱ ግን አይቅረቡ፤ ሕዝቡም ከአንተ ጋር አይውጣ።”
3ሙሴም ሄዶ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዓት ሁሉ ለሕዝቡ ነገረ፤ ሕዝቡም በአንድነት “እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ እናደርጋለን” ሲል መለሰ። 4ሙሴም የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ሁሉ ጻፈ፤ በማግስቱም ጠዋት በማለዳ በተራራው ሥር መሠዊያ ሠራ፤ ለእያንዳንዱም የእስራኤል ነገድ አንድ የድንጋይ ዐምድ አኖረ፤ 5የሚቃጠል መሥዋዕት ወስደው ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ወጣቶች ወንዶችን ላከ፤ እነርሱም ወይፈኖችን የአንድነት መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። 6ሙሴም ከእንስሶቹ ደም ከፊሉን ወስዶ በገበቴ ውስጥ አኖረው፤ እኩሌታውንም በመሠዊያው ፊት ረጨው። 7ከዚህ በኋላ የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ድምፁን ከፍ በማድረግ ለሕዝቡ አነበበ፤ ሕዝቡም “ለእግዚአብሔር እንታዘዛለን እርሱ ያዘዘውንም ሁሉ እንፈጽማለን” አሉ።
8ከዚህ በኋላ ሙሴ በገበቴ ያለውን ደም ወስዶ በሕዝቡ ላይ በመርጨት “ይህ እንግዲህ እግዚአብሔር እነዚህን ሁሉ ትእዛዞች በሰጣችሁ ጊዜ ከእናንተ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የሚያጸናበት ደም ነው” አለ። #ማቴ. 26፥28፤ ማር. 14፥24፤ ሉቃ. 22፥20፤ 1ቆሮ. 11፥25፤ ዕብ. 9፥19-20፤ 10፥29።
9ሙሴ፥ አሮን፥ ናዳብ፥ አቢሁና ከእስራኤልም መሪዎች ሰባዎቹ ወደ ተራራው ወጡ፤ 10የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ በእግሮቹ ሥር ከብሩህ ሰንፔር የተሠራና የሚያበራ ሰማይ የሚመስል ወለል ነበር። 11እግዚአብሔር የእስራኤል መሪዎች የሆኑትን እነዚህን አረጋውያን ሰዎች አልቀሠፈም፤ ይልቁንም እግዚአብሔርን አይተው በፊቱ በሉ፤ ጠጡም።
ሙሴ በሲና ተራራ ላይ
12ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እኔ ወዳለሁበት ወደ ተራራው ወጥተህ በዚያ ቈይ፤ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችንም እሰጥሃለሁ፤ በእነርሱም ላይ ለሕዝቡ መመሪያዎች ይሆኑ ዘንድ እኔ የጻፍኳቸው ትእዛዞችና ኅጎች ይገኛሉ።” 13ሙሴና አገልጋዩ ኢያሱ ተዘጋጁ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ፤ 14ሙሴም ለመሪዎቹ “እንደገና ወደ እናንተ ተመልሰን እስክንመጣ በዚህ ቈዩን፤ አሮንና ሑርም እነሆ፥ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ ስለዚህም በመካከላችሁ ጥልና ክርክር ያለበት ሰው ቢኖር ወደ እነርሱ ይሂድ” አላቸው።
15ሙሴም ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ተራራውንም ደመና ሸፈነው፤ 16የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ዐረፈ፤ ደመናውም ተራራውን ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው። 17በተራራው ጫፍ ላይ የተገለጠው የእግዚአብሔር ክብር በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ እንደሚባላ እሳት ይታይ ነበር። 18ሙሴም ወጥቶ በተራራው ላይ ወዳለው ደመና ውስጥ ገባ፤ እዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየ። #ዘዳ. 9፥9።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 24: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997