ዘፀአት 20:1-26
ዘፀአት 20:1-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ይህን ቃል ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ፤ “ከእኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ። “በላይ በሰማይ ከአለው፥ በታችም በምድር ከአለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ከአለው ነገር የማናቸውንም ምስል ለአንተ አምላክ አታድርግ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኀጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ አምላክ ነኝና። “የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና። “የሰንበትን ቀን ትቀድሳት ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛዋ ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ናት፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ አህያህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርስዋ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛዋ ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል፤ ቀድሶታልም። “አባትህንና እናትህን አክብር፤ መልካም እንዲሆንልህ፥ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድርም ዕድሜህ እንዲረዝም። “አትግደል። “አታመንዝር። “አትስረቅ። “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። “የባልንጀራህን ሚስት፥ የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ እርሻውንም፥ ሎሌውንም፥ ገረዱንም፥ በሬውንም፥ አህያውንም፥ ከብቱንም ሁሉ ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማንኛውንም አትመኝ።” ሕዝቡም ሁሉ ነጐድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ሁሉ ፈርተው ርቀው ቆሙ። ሙሴንም፥ “አንተ ከእኛ ጋር ተናገር፤ ነገር ግን እንዳንሞት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አይናገር” አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ፥ “እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ፥ ኀጢአትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በእናንተ ያድር ዘንድ መጥቶአልና አትፍሩ” አላቸው። ሕዝቡም ርቀው ቆሙ፤ ሙሴም እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጨለማው ቀረበ። እግዚአብሔር ሙሴን አለው፥ “ለያዕቆብ ቤት ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ በል፦ እኔ ከሰማይ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ አይታችኋል። የብር አማልክትን አታምልኩ፤ የወርቅ አማልክትንም አታምልኩ። የዕንጨትና የድንጋይ አምላክንም አታምልኩ፤ እንዲህ ያለ አምላክን ለእናንተ አታድርጉ። ከአፈርም መሠዊያ ሥራልኝ፤ የሚቃጠለውንና የደኅንነት መሥዋዕትህን፥ በጎችህንም፥ በሬዎችህንም ሠዋበት፤ ስሜን ባስጠራሁበት ስፍራ ሁሉ ወደ አንተ መጥቼ እባርክሃለሁ። የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ ጠርበህ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና። ኀፍረተ ሥጋህ በእርሱ እንዳይገለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።
ዘፀአት 20:1-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር እነዚህን ቃሎች ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፤ “ከግብጽ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም ከምድር በታች ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩ ነገሮች በማናቸውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። አትስገድላቸው ወይም አታምልካቸውም፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር የሚጠሉኝን ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ ልጆቻቸውን የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ ነኝ፤ ለሚወድዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺሕ ትውልድ ፍቅርን የማሳይ ነኝ። የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አታንሣ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚያነሣውን በደል አልባ አያደርገውምና። የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ አክብረው። ስድስት ቀን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አከናውን። ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። በዚያ ቀን አንተም ሆንህ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህ ሆነ ሴት አገልጋይህ፣ ወይም እንስሳትህ፣ ወይም በደጅህ ያለ መጻተኛ ምንም ሥራ አትሠሩም። እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን፤ ባሕርንም በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ በስድስት ቀን ፈጥሮ፣ በሰባተኛው ቀን ዐርፏልና። ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም። አባትህንና እናትህን አክብር፤ አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም። አትግደል። አታመንዝር። አትስረቅ። በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የርሱ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትመኝ።” ሕዝቡም መብረቁንና ነጐድጓዱን የተራራውን መጤስና የመለከቱን ድምፅ ባዩና በሰሙ ጊዜ በፍርሀት ተንቀጠቀጡ፤ በርቀትም ቆሙ፤ ሙሴን፣ “አንተ ራስህ ተናገረን፤ እኛም እናደምጥሃለን፤ እግዚአብሔር እንዲናገረን አታድርግ፤ አለዚያ መሞታችን ነው” አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ፣ “አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር ፍርሀት ከእናንተ ጋራ ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ መጥቷል” አላቸው። እግዚአብሔር ወዳለበት ጥቅጥቅ ወደ ሆነው ጨለማ ሙሴ ቀርቦ ሳለ፣ ሕዝቡ በርቀት ቆመው ነበር። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ለእስራኤላውያን ይህን ንገራቸው፤ ‘ከሰማይ ሆኜ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል፤ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሯችሁ፤ ከብር ወይም ከወርቅ ለእናንተ አማልክትን አታብጁ። “ ‘የጭቃ መሠዊያን ሥራልኝ፤ በርሱም ላይ የሚቃጠልና የኅብረት መሥዋዕትን ከበጎችህ፣ ከፍየሎችህና ከቀንድ ከብቶችህ ሠዋልኝ፤ ስሜ እንዲከበር በማደርግበት ቦታ ሁሉ ወደ አንተ እመጣና እባርክሃለሁ። ከድንጋይ መሠዊያ የምትሠራልኝ ከሆነ፣ ከጥርብ ድንጋይ አትሥራ፤ መሣሪያ የነካው ከሆነ ታረክሰዋለህና። ወደ መሠዊያዬም በደረጃ አትውጣ፤ አለዚያ ኀፍረተ ሥጋህ ይገለጣል።’
ዘፀአት 20:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ይህን ቃል ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢያት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና። የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም። አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም። አትግደል። አታመንዝር። አትስረቅ። በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ። ሕዝቡም ሁሉ ነጎድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ባዩ ጊዜ ተርበደበዱ፥ ርቀውም ቆሙ። ሙሴንም፦ አንተ ተናገረን እኛም እንሰማለን፤ እንዳንሞት ግን እግዚአብሔር አይናገረን አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ፦ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ፥ ኃጢያትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በልባችሁ ይሆን ዘንድ መጥአልና አትፍሩ አለ። ሕዝቡም ርቀው ቆሙ፥ ሙሴም እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጨለማው ቀረበ። እግዚአብሔር ሙሴን አለው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በል፦ እኔ ከሰማይ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ አይታችኋል። በአጠገቤ ምንም አታድርጉ፤ የብር አማልክት የወርቅም አማልክት ለእናንተ አታድርጉ። የጭቃ መሰዊያ ሥራልኝ፥ የሚቃጠለውንና የደኅንነት መሥዋዕትህን በጎችህንም በሬዎችህንም ሠዋበት፤ ስሜን በማሳስብበት ስፍራ ሁሉ ወደ አንተ መጥቼ እባርክሃለሁ። የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ ብረት በነካው ድንጋይ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና። ኃፍረተ ሥጋህ በእርሱ እንዳይገለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።
ዘፀአት 20:1-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ለሕዝቡ ተናገረ፥ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በባርነት ከምትኖርባት ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ፤ “ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ፤ “በሰማይም ሆነ በምድር ወይም ከምድር በታች ባለው ውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች የማንኛውንም ዐይነት ምስል ጣዖት አድርገህ አትሥራ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ እጅግ ቀናተኛ ስለ ሆንኩ ተቀርጾ የተሠራውን ማንኛውም ጣዖት አታምልክ፤ አትስገድለትም፤ እኔ የሚጠሉኝን ሁሉ እቀጣለሁ፤ ዘራቸውንም ሁሉ እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ እበቀላለሁ። ለሚወዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ሁሉ ግን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ዘለዓለማዊ ፍቅሬን አሳያቸዋለሁ። “የአምላክህን የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አታንሣ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚያነሣውን ሁሉ ሳይቀጣው አያልፍም። “የሰንበትን ቀን አክብር፤ ቀድሰውም፤ ሥራህን ሁሉ የምታከናውንባቸው ስድስት ቀኖች አሉልህ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ቀን ነው፤ በዚያን ቀን ማንም ሰው ሥራ አይሥራ፤ አንተም ሆንክ ልጆችህ፥ አገልጋዮችህም ሆኑ እንስሶችህ፥ በአገርህ ውስጥ የሚኖሩ መጻተኞችም ቢሆኑ ምንም ሥራ አትሥሩበት። በስድስት ቀን እግዚአብሔር ሰማይን፥ ምድርን፥ ባሕርንና በእነርሱ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም። “አባትህንና እናትህን አክብር፤ ይህን ብታደርግ እኔ በምሰጥህ ምድር የረዥም ዘመን ዕድሜ ይኖርሃል። “አትግደል፤ “አታመንዝር፤ “አትስረቅ፤ “በማንም ሰው ላይ በሐሰት አትመስክር፤ “የሌላውን ሰው ቤት አትመኝ፤ ሚስቱን፥ አገልጋዮቹን፥ ከብቱን፥ አህዮቹንም ሆነ ማናቸውንም ንብረቱን ሁሉ አትመኝ።” ሕዝቡም የነጐድጓዱንና የእምቢልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ፥ እንዲሁም መብረቁ ሲብለጨለጭና ተራራው ሲጤስ ባዩ ጊዜ በፍርሃት በመንቀጥቀጥ ርቀው ቆሙ፤ እነርሱም ሙሴን “አንተ ተናገረን፤ እናዳምጥሃለን፤ እግዚአብሔር ቢናገረን ግን እንሞታለን ብለን እንፈራለን” አሉት። ሙሴም “አይዞአችሁ፥ አትፍሩ፤ እግዚአብሔር በዚህ ሁኔታ ወደ እናንተ የመጣው ሊፈትናችሁና እርሱን በመፍራት ኃጢአት ከመሥራት ርቃችሁ እንድትኖሩ ነው” ሲል መለሰላቸው። ሕዝቡ ግን ርቀው ቆሙ፤ ሙሴ ብቻውን እግዚአብሔር ወዳለበት ጥቅጥቅ ወደ ሆነው ደመና ተጠጋ። እግዚአብሔር ሙሴን ለእስራኤላውያን እንዲነግር እንዲህ ሲል አዘዘው፥ “እኔ እግዚአብሔር ከሰማይ እንዴት እንደ ተናገርኳችሁ አይታችኋል፤ እኔን ብቻ አምልኩ እንጂ፥ ከብርና ከወርቅ ጣዖቶች ሠርታችሁ አታምልኩ፤ ለእኔ ከጭቃ የተሠራ መሠዊያ አብጁልኝ፤ በእርሱም ላይ ከበጎቻችሁ፥ ከፍየሎቻችሁና ከከብቶቻችሁ መርጣችሁ የሚቃጠልና የአንድነት መሥዋዕት አድርጋችሁ ሠዉበት፤ ስሜ እንዲታሰብበት በወሰንኩት ስፍራ ሁሉ ወደ እናንተ መጥቼ እባርካችኋለሁ፤ ለእኔ የድንጋይ መሠዊያ ማበጀት ብትፈልጉ ከጥርብ ድንጋይ የተሠራ አይሁን፤ የብረት መሣሪያ ቢነካው ታረክሱታላችሁ፤ ኀፍረተ ሥጋችሁ በእርሱ ላይ እንዳይገለጥ በመወጣጫ መሰላል አትውጡ።
ዘፀአት 20:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔርም እነዚህን ቃሎች ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ ጌታ አምላክህ እኔ ነኝ። “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። በላይ በሰማያት ካለው፥ በታች በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም አምሳል፥ የተቀረጸ ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም፤ እኔ ጌታ አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፥ ለሚወድዱኝ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ ነኝ። “የጌታ የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ ጌታ ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ሳይቀጣው አያልፍም። “እንድትቀድሰው የሰንበትን ቀን አስታውስ። ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፥ ተግባርህንም ሁሉ ፈጽም፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለጌታ አምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህ፥ ሴት ልጅህ፥ ወንድ ሠራተኛህ፥ ሴት ሠራተኛህ፥ ከብትህ፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ መጻተኛ ሁሉ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ ጌታ በስድስት ቀናት ሰማያትንና ምድርን፥ ባሕርን፥ እና በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ ጌታ የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም። “ጌታ አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም፥ አባትህንና እናትህን አክብር። “አትግደል። “አታመንዝር። “አትስረቅ። “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት፥ ወንድ ሠራተኛውን፥ ሴት ሠራተኛውን፥ በሬውን፥ አህያውን፥ የባልንጀራህ የሆነውን ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።” ሕዝቡም ሁሉ ነጎድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ፈሩ ተንቀጠቀጡም፥ ርቀውም ቆሙ። ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “አንተ ተናገረን እኛም እንሰማለን፤ ነገር ግን እንዳንሞት እግዚአብሔር አይናገረን።” ሙሴም ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ ሊፈትናችሁ፥ ኃጢአትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በልባችሁ እንዲሆን እግዚአብሔር መጥቷልና።” ሙሴ እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጨለማው ሲቀርብ ሕዝቡ ግን ርቀው ቆሙ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፥ ‘እኔ ከሰማይ ከእናንተ ጋር እንደተነጋገርሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል። ከእኔ ጋር የብር አማልክትን አትሥሩ፥ የወርቅ አማልክትንም ለእናንተ አትሥሩ። ከአፈርም መሠዊያ ሥራልኝ፥ የሚቃጠለውንና የሰላም መሥዋዕትህን በጎችህንም በሬዎችህንም ሠዋበት፤ ስሜን በማሳስብበት ስፍራ ሁሉ ወደ አንተ መጥቼ እባርክሃለሁ። የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ በተጠረበ ድንጋይ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና። ኃፍረተ ሥጋህ በእርሱ ላይ እንዳይገለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።’”