እግዚአብሔርም ይህን ቃል ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ፤ “ከእኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ። “በላይ በሰማይ ከአለው፥ በታችም በምድር ከአለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ከአለው ነገር የማናቸውንም ምስል ለአንተ አምላክ አታድርግ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኀጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ አምላክ ነኝና። “የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና። “የሰንበትን ቀን ትቀድሳት ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛዋ ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ናት፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ አህያህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርስዋ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛዋ ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል፤ ቀድሶታልም። “አባትህንና እናትህን አክብር፤ መልካም እንዲሆንልህ፥ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድርም ዕድሜህ እንዲረዝም። “አትግደል። “አታመንዝር። “አትስረቅ። “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። “የባልንጀራህን ሚስት፥ የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ እርሻውንም፥ ሎሌውንም፥ ገረዱንም፥ በሬውንም፥ አህያውንም፥ ከብቱንም ሁሉ ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማንኛውንም አትመኝ።” ሕዝቡም ሁሉ ነጐድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ሁሉ ፈርተው ርቀው ቆሙ። ሙሴንም፥ “አንተ ከእኛ ጋር ተናገር፤ ነገር ግን እንዳንሞት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አይናገር” አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ፥ “እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ፥ ኀጢአትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በእናንተ ያድር ዘንድ መጥቶአልና አትፍሩ” አላቸው። ሕዝቡም ርቀው ቆሙ፤ ሙሴም እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጨለማው ቀረበ። እግዚአብሔር ሙሴን አለው፥ “ለያዕቆብ ቤት ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ በል፦ እኔ ከሰማይ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ አይታችኋል። የብር አማልክትን አታምልኩ፤ የወርቅ አማልክትንም አታምልኩ። የዕንጨትና የድንጋይ አምላክንም አታምልኩ፤ እንዲህ ያለ አምላክን ለእናንተ አታድርጉ። ከአፈርም መሠዊያ ሥራልኝ፤ የሚቃጠለውንና የደኅንነት መሥዋዕትህን፥ በጎችህንም፥ በሬዎችህንም ሠዋበት፤ ስሜን ባስጠራሁበት ስፍራ ሁሉ ወደ አንተ መጥቼ እባርክሃለሁ። የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ ጠርበህ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና። ኀፍረተ ሥጋህ በእርሱ እንዳይገለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።
ኦሪት ዘፀአት 20 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 20:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች