ኦሪት ዘፀአት 20
20
ዐሠርቱ ትእዛዛት
(ዘዳ. 5፥1-21)
1እግዚአብሔርም ይህን ቃል ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ 2“ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ፤
3“ከእኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ።
4“በላይ በሰማይ ከአለው፥ በታችም በምድር ከአለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ከአለው ነገር የማናቸውንም ምስል ለአንተ አምላክ አታድርግ። 5አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኀጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ 6ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ አምላክ ነኝና።
7“የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና።
8“የሰንበትን ቀን ትቀድሳት ዘንድ አስብ። 9ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ 10ሰባተኛዋ ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ናት፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ አህያህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርስዋ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ 11እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛዋ ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል፤ ቀድሶታልም።
12“አባትህንና እናትህን አክብር፤ መልካም እንዲሆንልህ፥ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድርም ዕድሜህ እንዲረዝም።
13“አትግደል።
14“አታመንዝር።
15“አትስረቅ።
16“በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።
17“የባልንጀራህን ሚስት፥ የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ እርሻውንም፥ ሎሌውንም፥ ገረዱንም፥ በሬውንም፥ አህያውንም፥ ከብቱንም ሁሉ ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማንኛውንም አትመኝ።”
የሕዝቡ መፍራት
(ዘዳ. 5፥21-33)
18ሕዝቡም ሁሉ ነጐድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ሁሉ ፈርተው ርቀው ቆሙ። 19ሙሴንም፥ “አንተ ከእኛ ጋር ተናገር፤#ዕብ. “እኛም እንሰማለን” የሚል ይጨምራል። ነገር ግን እንዳንሞት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አይናገር” አሉት። 20ሙሴም ለሕዝቡ፥ “እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ፥ ኀጢአትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በእናንተ ያድር ዘንድ መጥቶአልና አትፍሩ” አላቸው። 21ሕዝቡም ርቀው ቆሙ፤ ሙሴም እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጨለማው#ግእዙ “ወደ ብርሃን ገባ” ይላል። ቀረበ።
መሠዊያውን የሚመለከት ሕግ
22እግዚአብሔር ሙሴን አለው፥ “ለያዕቆብ ቤት ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ በል፦ እኔ ከሰማይ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ አይታችኋል። 23የብር አማልክትን አታምልኩ፤ የወርቅ አማልክትንም አታምልኩ። የዕንጨትና የድንጋይ አምላክንም አታምልኩ፤ እንዲህ ያለ አምላክን ለእናንተ አታድርጉ።#“የዕንጨትና የድንጋይ አምላክን አታምልኩ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በዕብ. የለም። 24ከአፈርም መሠዊያ ሥራልኝ፤ የሚቃጠለውንና የደኅንነት መሥዋዕትህን፥ በጎችህንም፥ በሬዎችህንም ሠዋበት፤ ስሜን ባስጠራሁበት ስፍራ ሁሉ ወደ አንተ መጥቼ እባርክሃለሁ። 25የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ ጠርበህ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና። 26ኀፍረተ ሥጋህ በእርሱ እንዳይገለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 20: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ